በእርግጥ አርጀንቲና በዓለም ዋንጫ አድልዎ እየተደረገላት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ አሸናፊነቱን በዘንድሮው ውድድርም ለማስጠበቅ የቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው።
እስካሁን በተጫወቷቸው ሁለት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች የገጠሟቸውን ኬፕ ቨርዴ እና ግብጽን ያለ ችግር እንደሚያሸንፉ ተጠብቆ ነበር። ነገር ግን ሁለቱንም ጨዋታዎች 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ያሸነፉት በከባድ ትግል ነው።
አርጀንቲናዎች ግብፅ ላይ የተቀናጁት ድል ደግሞ ውዝግብ አስነስቷል። ግብፅ ከውድድሩ የተሰናበተችበትን ከአርጀንቲና ጋር የተካሄደ ጨዋታ የመሩት ዳኞች እንዲባረሩ ለፊፋ ጥያቄ አቅርባለች።
ግብፅ፤ ለአርጀንቲና እና ለቡድኑ ኮከብ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ አልድዎ ተደርጓል ስትል ክስ አሰምታለች።
ዋና አሰልጣኙ ሆሳም ሃሰን ከጨዋታው በኋላ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ "ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ" እንደተስተናገዱ እና "ኢ- ፍትሐዊነት እንደደረሰባት" ተናግረዋል። ፊፋ አድልዎ እንዳለበት ጭምር በማንሳት ከስሰዋል።
"ምናልባት የዓለም ሻምፒዮኖቹ ውድድሩ ውስጥ እንዲቆዩ ይፈልጉ ይሆናል። ምናልባት ሜሲ እየተጫወተ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ" ሲሉም ተደምጠዋል።
ቢቢሲ፤ አርጀንቲና እንድታሸንፍ እየተደረገ እንደሆነ በሚቀርበው ሴራ ውስጥ እውነታ ይኖር እንደሆነ ለማረጋገጥ ጉዳዩን መርምሯል።
የግብፅ ክስ እውነታ አለው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግብፅ ማክሰኞ ምሽት ባጋጠማት የ3 ለ 2 ሽንፈት ብስጭት ውስጥ ልትሆን እንደምትችል መረዳት ቀላል ነው።
ጨዋታው ለመጠናቀቅ 11 ደቂቃዎች እስከሚቀሩት ድረስ 2 ለ 0 ስትመራ የነበረችው አፍሪካዊት አገር፤ ይህንን ውጤት ማስጠበቅ ብትችል በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩብ ፍጻሜ ታልፍ ነበር።
አርጀንቲና ጨዋታቸውን ከእግር እስከ ራስ ገልብጣ አቻ ከሆነች እና አሸናፊ ያደረጋትን ግብ በጭማሪ ሰዓት ካስቆጠረች በኋላ ይህ ሁሉ ከሽፏል።
ግብፅ ጨዋታው ላይ ከአጠራጣሪነት የዘለለ ነገር እንዳለ ትናገራለች። ከውድድሩ የወጡት በፈረንሳዊው ዳኛ ፍራንሷ ሌቴክሲየር እና ባልደረቦቹ "ከባድ የዳኝነት ስህተቶች" እንዲሁም ለአርጀንቲና ባደሉ "መመዘኛዎች" እንደሆነ ትናገራለች።
ፈርኦኖቹ ያስቆጠሩት ግብ በቪዲዮ ረዳት ዳኝነት (ቫር) ውሳኔ ተሽሯል።
ግብፆች አንጀንቲናን አሸናፊ ያደረጋት የመጨረሻው ግብ መሰረዝ እንደነበረበት እና በምትኩም ፍጹም ቅጣት ምት ሊሰጣቸው ይገባ እንደነበረም ይከራከራሉ።
የግብፁ ሞስታፋ ዚኮ አስደናቂ ግብ የተሻረው ወደ ግብ የተቀየረው እንቅስቃሴ ሲጀመር ማርዋን አቲያ የአርጀንቲናውን የሊሳንድሮ ማርቲኔዝን እግር ረግጧል በሚል ነው።
ውሳኔው አወዛጋቢ ነው። ነገር ግን 1 ለ 0 እየመሩ የነበረ ሲሆን ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላም ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዋል። የዚኮ ግብ ባይሻር ኖሮ ጨዋታው ሌላ አቅጣጫ ይይዝ ነበር ለሚለው ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም።
የአርጀንቲናው ኢንዞ ፈርናንዴዝ ኳሱን በጭንቅላት ገጭቶ የመጨረሻውን ግብ ከማስቆጠሩ አስቀድሞ፤ ለግብፅ የፍጹም ቅጣት ምት ሊያሰጡ ይገባ የነበሩ ሁለት አጋጣሚዎች እንደነበሩ ፈርኦኖቹ ይከራከራሉ።
ሃምዲ ፋቲ በአሌክሲስ ማክ አሊስተር እንደተጎተተ በመግለጽ ሜዳው ላይ መድቆ ነበር። ሞሀመድ ሳላህ ደግሞ በጁሊያን አልቫሬዝ እንደተጠለፈ ተሰምቶታል።
የግብፅን ግብ ባስሻረው የማርቲኔዝ እንዲሁም የሞ ሳላህ ሁኔታ በተወሰኑ መልኩ ይመሳሰላል። ሁለቱም የእግር ለእግር ንክኪ ያለባቸው ቢሆኑም ሁለቱም ፍጹም ቅጣት ምት ለማሰጠት በቂ ሆኖ አልተገኙም።
የሳላህ ንክኪ የተፈጠረው ከግብ ሳጥኑ ውጪ ባይሆን ኖሮ ግብፅ የአርጀንቲናን ግብ የማስሻር የተሻለ ዕድል ይኖራት ነበር። በማርቲኔዝ ሁኔታ እንደተደረገው ሁሉ ቫር የሚዳኘው ተፈጽሟል የተባለው ጥፋት እንጂ ፍጹም ቅጣት ምትን አይደለም።
ውሳኔው አከራካሪ ነው? አከራካሪ ስለመሆኑ ጥርጥር የለም። ነገር ግን ለሜሲ አድልዎ ተደርጓል ለማለት የሚያስችል ማረጋገጫ ነው ለማለት ግን አስቸጋሪ ነው።
ቀጣዩ የፈረንሳይ ጨዋታ የሚዳኘው በአርጀንቲናዊ ዳኞች ነው
ፈረንሳይ እና ሞሮኮ ዛሬ ሐሙስ ሌሊት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።
በዚህ የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋና ዳኛ፣ ሁለት ረዳቶች፣ አራተኛው ዳኛ እና ተጠባባቂው ዳኛ በሙሉ ከአንድ አገር የተውጣጡ ናቸው።
ይህች አገር ደግሞ አርጀንቲና ናት።
መጀመሪያ ላይ ከአርጀንቲናዊው ዳኛ ፋኩንዶ ቴሎ ጋር እንዲዳኙ የተመረጡት አራተኛው ዳኛ ከሳዑዲ አረቢያ፤ ተጠባባቂው ደግሞ ከኮሎምቢያ ነበር።
አሁን የሚነሳው ክርክር አርጀንቲና ፈረንሳይ እንድትወድቅ ትፈልጋለች የሚል ነው።
ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜን ለሚመሩት ዳኛ ቴሎ፤ የዛሬው ግጥሚያ በታሪካቸው ከመሯቸው ትልቅ ጨዋታዎች አንዱ ይሆናል። በዚህ ደረጃ ትልቅ ስም ያለው ዳኛ ከፍ ካለ ሙያዊ ሥነ ምግባር ወርዶ ይዳኛል ተብሎ አይጠበቅም።
ነገር ግን ሰዎች ውሳኔዎቹን እንዴት ይቀበሉታል የሚለውም ወሳኝ ነው። በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ አርጀንቲናዊ ዳኛ የፈረንሳይን ጨዋታ እንዲመራ ማድረግ በራሱ ጥሩ ምልከታ የሚሰጠው አይሆንም።
ሜሲ ቀይ ካርድ ሳያገኝ 5 ግቦችን አስቆጥሯል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወደ የዘንድውሮ ዓለም ዋንጫ አጀማመር መለስ ስንል ሜሲ ቀይ ካርድ ሊያገኝ ይችልበት የነበረ ዕድል እንመለከታለን።
ሜሲ ከአልጄሪያው አምበል አይሳ ማንዲ ጋር ለነበረው ትንቅንቅ ቀይ ካርድ ቀርቶ ቢጫ አልተሰጠውም።
ከዚያም የዓለም ዋንጫ አወዛጋቢው ክስተት ባለፈው ሳምንት ተፈጠረ። የአሜሪካው ተጫዋች ፎላሪን ባሎገን ከቦስኒያ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ በተፈጠረ ተመሳሳይ ሁኔታ በቫር ውሳኔ ቀይ ካርድ ተሰጥቶታል።
ባሎገንም ሆነ ሜሲ ንክኪ የፈጠሩት ከተቀናቃኛቸው ባት ጋር ነው።
አሜሪካ ተጨዋቿ ላይ የተጣለውን የአንድ ጨዋታ እገዳ ለማስነሳት ስትጠይቅ ይህ ጉዳይ መከራከሪያ ሆኖ እንደቀረበ ይታመናል።
ሜሲ ቀይ ካርድ አግኝቶ ቢሆን አልጄሪያ ላይ ሁለተኛ እና ሦስተኛውን ጎል አያስቆጥርም ነበር። ሌላ ሁለት ግቦችን ባስቆጠረበት የኦስትሪያ ጨዋታ ላይም አይሰለፍም ነበር፤ ምናልባት ፊፋ ለባሎገን እንዳደረገው ሕጉን ካላገደለት በቀር።
ሜሲ በድጋሚ ዮርዳኖስ ላይ ግብ ባስቆጠረበት ጨዋታም ተሳታፊ ላይሆን ይችል ነበር።
እነዚህን ስንቀንስ ሜሲ በዚህ ውድድር ካስቆጠራቸው ስምንት ግቦች ውስጥ አምስቱ አይኖሩም ነበር ማለት ነው።
ይህ ለሜሲ የተደረገ ልዩ እንክብባኬ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዳኞች ለአርጀንቲና የሰሚጡት ቢጫ ካርድ ከሌሎች ያነሰ ነው?
የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ በስጋት የተሞላ ነው። በዘንድሮው ውድድር 17 ተጫዋቾች ከግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ውጪ ለመሆን አንድ ቢጫ ካርድ ብቻ ይቀራቸዋል።
አርጀንቲና በአንጻሩ ያንን ያህል ከባድ የሚባል እንቅፋት የለባትም። ከእንግሊዝ ወይም ከኖርዌይ ጋር የሚኖረውን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ያለመሳተፍ ስጋት የተደቀነበት ጎንዛሎ ሞንቲኤል ብቻ ነው።
የእንግሊዝ አሰልጣኝ ቶማስ ቱቼል እንዳሉት ቁልፍ ተጫዋቾቻቸው ጁድ ቤሊንግሃም እና ዴክላን ራይስን ጨምሮ አራት ተጨዋቾቻቸው ቢጫ አግኝተዋል።
ጥቂት ቢጫ ካርድ ያላት ኖርዌይም ቢጫ ያገኘባት አንቶኒዮ ኑሳ ብቻ ነው።
ይህንን ለመረዳት አንድ ቡድን ምን ያህል 'አደገኛ' ጨዋታ ሲያደርግ እንደነበር መመልከት ያስፈልጋል። ያላቸው ቢጫ ካርድ ከሰሩት ጥፋት ጋር ተመጣጣኝ ነው ወይ? የሚለውም አጠያያቂ ነው።
የአርጀንቲና ተጫዋቾች ለሚሰሯቸው 19.7 ጥፋቶች አንድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
ከአርጀንቲና ጋር ሲወዳደር ከፍ ያለ የጥፋት እና የቢጫ ካርድ ጥምርታ ያላቸው ሦስት ሀገራት ብቻ ናቸው። ቼክ ሪፐብሊክ (37.0)፣ ኖርዌይ (24.0) እና ቱኒዚያ (27.0) አላቸው።
አሁንም በውድድሩ ላይ ካሉት ቡድኖች መካከል እጅግ እየተቀጣ ያለው የእንግሊዝ ቡድን ነው። ቡድኖ በየ 7.7 ጥፋቶች አንድ የቢጫ ካርድ ተሰጥቶታል።
አርጀንቲና ከእንግሊዝ የበለጠ ጥፋቶችን ብትሰራም የተሰጣት ማስጠንቀቂያ በግማሽ ያንሳል።
ይህም አርጀንቲና ከሰራችው የጥፋት ብዛት አንጻር አድልዎ እንደተደረገላት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።












