የአፍሪካ አገራት ለምንድነው በትራምፕ የእርዳታ ገንዘብ ላይ ፊታቸውን እያዞሩ ያሉት?

 ጋና በመረጃ ጥበቃ ስጋት ምክንያት በአሜሪካ የቀረበውን የ109 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ውድቅ አድርጋለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጋና በመረጃ ጥበቃ ስጋት ምክንያት በአሜሪካ የቀረበውን የ109 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ውድቅ አድርጋለች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ባለፈው ዓመት 'ዩኤስኤአይዲ' የተባለውን ዋነኛ የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታ ተቋምን ያፈረሰው የትራምፕ አስተዳደር፤ አሁን የአፍሪካ አገራት የጤና መዋቅሮቻቸውን መደገፍ እና በሽታዎችን መከላከል እንዲችሉ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያቀረበ ነው።

የአዲሱ የአስተዳደር ስምምነት ግን ቅድመ ሁኔታዎችን ያካተተ ነው። በዚህም የተነሳ ከተወሰኑ የአፍሪካ መንግሥታት ተቃውሞ ገጥሞታል።

ታኅሣሥ ላይ የመጀመሪያው ስምምነት የተፈረመው ከኬንያ ጋር ነበር። ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ፊርማቸውን ባኖሩበት ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት፤ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከሌሎች አገራት ጋርም ስምምነቶች ይፈጸማሉ የሚል ተስፋቸውን ገልጸው ነበር።

"እንደምንፈራረም ተስፋ አደርጋለሁ። [ቁጥሩን] አላውቅም፤ 30፣ 40 ምን ያህል? 50? እንግዲህ ይህ የመጀመሪያው ነው" ብለዋል።

ከኬንያ ጋር የተፈረመው ይህ የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ግን በአክቲቪስቶች ወደ ፍርድ ቤት በመወሰዱ ትግበራው ተጓትቷል። በመጨረሻ ግን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ወር አጽድቆታል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገንዘብ ያባክናል በማለት የከሰሱት የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) እንዲዘጋ ትዕዛዝ ሰጡት ወደ ሥልጣን እንደተመለሱ ነበር። ይህ ውሳኔ የአሜሪካ ድጋፍ ላይ ተመሥርተው በተወሰኑ የአፍሪካ አገራት ሲተገበሩ የነበሩ የጤና ፕሮግራሞች እንዲቋረጡ አድርጓል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያወጣው አዲስ ዓለም አቀፍ የጤና ስትራቴጂ፤ ድጋፍ የሚያገኙ መንግሥታት የአገራቸውን የጤና በጀት በመጨመር ኃላፊነቱን መጋራት እንዳለባቸው ይገልጻል። የዚህ ስትራቴጂ ዓላማ በሂደት ራሳቸውን የሚችሉ ዘላቂ ሥርዓቶችን መገንባት እንደሆነም ያስረዳል።

ለምሳሌ በአጠቃላይ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማግኘት የተፈራረመችው ኬንያ፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከራሷ በጀት 850 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ ለማድረግ ቃል ገብታለች።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ እና ኬንያ በተፈራረሙት ስምምነት መሠረት ዋሽንግተን 1.6 ቢሊዮን ዶላር፤ ናይሮቢ ደግሞ ከ850 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያዋጣሉ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንደ የትራምፕ አስተዳደር ገለጻ፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የለጋሾች እና የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ግንኙነት ጥገኝነት ፈጥሯል። ይህ ሂደት በርካታ ገንዘብ አስተዳደራዊ ሂደት ላይ እንዲባክን እንዳደረገም ይገልጻል። በአንጻሩ የአሁኑ ሥርዓት ይህንን ችግር ይፈታል የሚል ተስፋ አለው።

በሌላ በኩል ግን ይህ አሠራር የዓለም የጤና ድርጅትን ማዕከል በማድረግ ሲተገበር ከነበረው ዓለም አቀፋዊ የትብብር ሞዴል ውጪ የሆነ ሥርዓት እንዲፈጠር አድርጓል። የአሁኑ አሠራር የሚተገበረው የአሜሪካ ስትራቴጂካዊ እና ንግድ ጥቅሞች ካሉባቸው አገራት ጋር በተናጠል በሚፈጸም ስምምነት ነው።

በዚህ መልኩ የተዋቀረው የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ቢያንስ ከ20 የአፍሪካ አገራት ጋር ተፈርሟል። የዚህ አካል የሆኑ የላቲን አሜሪካ እና የካረቢያን አገራት ሲጨመሩ በአጠቃላይ ስምምነቱን የፈረሙት አገራት ቁጥር 32 ይደርሳል።

እንደ ጋና፣ ዚምባብዌ እና ዛምቢያ ያሉ አገራትን ግን የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ ስምምነቱን ሳይፈጽሙ ቀርተዋል።

የዛምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙላምቦ ሃይምቤ፤ አሜሪካ በስምምነቱ አማካኝነት ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቿን ለማሳካት ታደርጋለች ያሉትን ጥረት ተችተዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የጤና ሥርዓት ስምምነቱ የቀረበው ዋሽንግተን ወሳኝ ማዕድናት እንድታገኝ ከሚያስችላት ሌላ ስምምነት ጋር ተያይዞ ነው።

ስለ ጉዳዩ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበለት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፤ ሁለቱ ስምምነቶች በቀጥታ ስለመገናኘታቸው ግልጽ ምላሽ ባይሰጥም፤ ስለ "ቅድሚያ ለአሜሪካ" ስትራቴጂ አብራርቷል።

የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ፤ "የትራምፕ አስተዳደር በግልጽ እንዳስቀመጠው፤ የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታ የአገሪቱን ጥቅሞች ለማስፋት በብልሃት ኢንቨስት የሚደረግ ስትራቴጂካዊ ካፒታል እንጂ ችሮታ አይደለም" ብለዋል።

"አጋሮቻችን እና ድጋፍ ተቀባይ አገራት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የአሜሪካ ስትራቴጂካዊ እና የንግድ ጉዳዮች በቁም ነገር እንዲመለከቷቸው እንጠብቃለን" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ባለፈው ወር ይህ የጤና ፋይናንስን አሜሪካ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ጉዳዮች ጋር የማያያዝ ጉዳይን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ተገኝቷል።

አሜሪካ በደቡብ አፍሪካ ለሚተገበሩ የኤችአይቪ/ኤድስ ፕሮግራሞች የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ እንደምታቋርጥ አስታውቃለች። አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለዚህ እርምጃ በምክንያትነት ያቀረቡት ደቡብ አፍሪካ በቀረቡላት "የፖሊሲ ጥያቄዎች ላይ ግልጽ መሻሻል ማሳየት ባለመቻሏን" ነው።

'አፍሪካነር' ተብለው የሚጠሩት የደቡብ አፍሪካ ነጮች ጉዳይም ከእነዚህ የፖሊሲ ጥያቄዎች አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል። የትራምፕ አስተዳደር በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ነጮች ላይ "ዘር ማጥፋት" እየተካሄደ ነው የሚል ክስ ያቀርባል። ይህ ውንጀላ ግን በሰፊው ውድቅ የተደረገ ነው።

መድኃኒት የያዘ እጅ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ይህንን የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ለመፈረም ሲደራደሩ የነበሩ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ደግሞ ስጋት የገባቸው፤ ውሉ አሜሪካ የአገሪቱን የጤና መረጃዎች እንድታገኝ የሚያስችል በመሆኑ ነው። የታካሚዎች መረጃ እንዲሁም እንደ ቫይረስ፣ ባክቴሪያ እና ፓራሳይት ያሉ በሽታዎችን ከሚፈጥሩ ተህዋስያን ጋር የተያያዙ መረጃዎች በስምምነቱ ተካትተዋል።

የኬንያ ፍርድ ቤት ስምምነቱን አግዶት የነበረው የምሥጢራዊነት ጥበቃ እንዲደረግ የአቤቱታ በመቅረቡ ነበር።

የጋና መንግሥትም ስምምነቱን የተቃወመው በዚሁ ምክንያት እንደሆነ የአገሪቱ የመረጃ ጥበቃ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር አርኖልድ ካቫርፑኦ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የተፈለገው የመረጃ ስፋት እና ጥልቀትን በተመለከተ ስጋቶች ነበሩን" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ "አንዴ መረጃው የጋናን ድንበር ከተሻገረ በኋላ ምን እንደሚደረግ ቁጥጥር የለንም" ሲሉ አብራርተዋል።

ዚምባብዌ በበኩሏ ለአሜሪካ የፋርማሱቲካል ኩባንያዎች ይሰጣሉ የተባሉ የሕክምና መረጃዎች ምክንያት ስምምነቱን ውድቅ እንዳደረገች ገልጻለች።

ከዚምባብዌ በሚወሰደው የበሽታ አምጪ ተዋህስያን መረጃ አማካኝነት የሚሠራ መድኃኒት ወይም ክትባት ለአገሪቱ ሕዝብ ይቀርብ እንደሆነ ማረጋገጫ አለመሆኑን የአገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

በአንጻሩ የዓለም ጤና ድርጅት፤ አባል አገራት መረጃዎችን እንዲያጋሩ እንዲሁም ወደፊት ለሚከሰቱ ወረርሽኞች ከሚፈጠሩ ህክምናዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል የሚያስችል ሥርዓት እንዳለው አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም የአፍሪካ አገራት እንደ ዩኤስኤአይዲ እና የአሜሪካ የኤችአይቪ እና ኤድስ መከላከያ ፕሮግራም በሆነው ፔፕፋርን ባሉ አሠራሮች በኩል የሕክምና መረጃዎችን ያጋሩ ነበር።

አሜሪካ ይህ ዓይነቱን መረጃ እና ናሙናዎች ማጋራት ለቀጣይ ሳይንሳዊ ዕድገት እና ለጋራ ትብብር ቁልፍ እንደሆነ ትሞግታለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም፤ አሁን የተጠየቀው መረጃ ከዚህ ቀደም ለበርካታ ዓመታት ሲጋራ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

አሁን የተቀየረው መረጃው የሚጋራበት ሁኔታ እንደሆነ በዴንማርክ የሮስኪልድ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ጤና አስተዳደር ፒኤችዲ ተመራማሪ የሆኑት ኔልሰን አጎጎ ይናገራሉ።

"የነበረው እኩልነት የሌለበት ግንኙነት ቢሆንም ፖለቲካዊ መቻቻል ነበረበት። የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ከሚደረግ በጎ ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ በመግለጽ ሕዝብን ማሳመን ይቻል ነበር" ይላሉ።

"አሁን ግን በከፍተኛ መጠን ተቀይሯል፤ ምክንያቱም እጅግ ሰጥቶ የመቀበል የበላይነት" ያተኮረ እንደሆነ ያስረዳሉ።

በርካታ የአፍሪካ አገራት ስለ በሽታ አምጪ ተዋህስያን መረጃ ዋጋን የተረዱት ለኮቪድ ወረርሽኝ ክትባት ለማግኘት ፉክክር በተደረገበት ወቅት ነው። በወቅቱ አፍሪካ በቀላሉ ከክትባቱ ተቋዳሽ አልሆነችም።

ሪዚሊየንስ አክሽን ኔትወርክ አፍሪካ (ራና) የተባለው ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አግሪ አሉሶ፤ "እንደ አፍሪካ ካሉን ትልልቅ ዕድሎች አንዱ፤ የዓለም አቀፉን የጤና ደኅንነት ሥነ-ምኅዳር ለመገንባት የሚያግዝ ጠቃሚ መረጃ በእጃችን መገኘቱ ነው ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።

አሜሪካ በቅርቡ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር 270 ሚሊዮን ዶላር ሰጥታለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ በቅርቡ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር 270 ሚሊዮን ዶላር ሰጥታለች

ራና፤ የአሜሪካ ስምምነት በአፍሪካ አገራዊ ወይም ቀጠናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ በመግለጽ የአፍሪካ መሪዎችን የሚያስጠነቅቅ ግልጽ ደብዳቤ ላይ ፊርማቸው ካኖሩ ከ50 በላይ ከሚሆኑ የሲቪል ማኅበራት አንዱ ነው። ደቡብ አፍሪካም ይህንን አቋም ትቀበለዋለች።

የደቡብ አፍሪካው የጤና ሚኒስትር ዶ/ር አሮን ሞትሶአሌዲ፤ "በግልጽ ለመናገር፤ ራሱን የሚያከብር የትኛውም አገር እነዚህን [ሁለት ጥያቄዎች] መቀበል የለበትም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በቀዳሚነት የጠቀሱት፤ የአፍሪካ አገራት "በአካባቢያቸው ማንኛውም ወረርሽኝ ወይም ተላላፊ በሽታ ከተከሰተ [አሜሪካ] የበሽታ አምጪ ተህዋሲያኑን መረጃ" ማግኘቷን ነው።

ሁለተኛው ደግሞ አገራቱ "ሁሌም የጂኖም መረጃም ያቀርቡላቸዋል። አሜሪካ ግን ገንዘብ የምትሰጣቸው ለአምስት ዓመታት ብቻ ነው" ብለዋል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አዲስ የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ባለፉት ሳምንታት፤ በጤና ዲፕሎማሲ ዙሪያ ክርክር ይበልጥ ጨምሮ ታይቷል።

ዴሞክራቲክ ኮንጎ የአሜሪካ የጤና ስምምነት ከፈረሙ የመጀመሪያዎቹ አገራት አንዷ ነች። አሜሪካ እንደምትገለጸው ስምምነቱ ኮንጎ ለወረርሽኙ የምትሰጠውን ምላሽ ለማቀናጀት እገዛ እያደረገ ነው።

የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች እና የቀድሞ የአሜሪካ የጤና ባለሥልጣናትን፤ ዋሽንግተን ለዴሞክራቲክ ኮንጎ እና ለዓለም ጤና ድርጅት የምትሰጠውን እርዳታ መቀነሷ ለበሽታው የሚሰጠው ምላሽ ክፉኛ አዳክሞታል።

ይህንን ወቀሳ ውድቅ የምታደርገው አሜሪካ በበኩሏ፤ በአዲሱ አሠራር አማካኝነት የሚሰጡት ድጋፎች "የተቀናጁ እና ውጤታማ" እንደሆኑ ትገልጻለች። ወረርሽኙን ለመከላከል 270 ሚሊዮን ዶላር መስጠቷንም ትጠቅሳለች።

የትራምፕ አስተዳደር አዲሱ ስምምነት መፈረሙ መንግሥታት ለአገራቸው የጤና አገልግሎት የበለጠ በጀት ያረበታታል የሚል አቋም አለው።

ለሌሎች በአንጻሩ በኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ይህ ዓይነቱ የሁለትዮሸ አካሄድ ለዓለም አቀፍ ጤና የደቀነውን ስጋት አሳይቷል ባይ ናቸው።

ለበርካታ ዓመታት ተላላፊ በሽታዎችን መቆጣጠር ላይ የሠሩት እንዲሁም የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል የቀድሞ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ኬቪን ዲኮክ "የሁለትዮሽ ግንኙነቶች የጋራ የሆኑ ተግዳሮቶችን ችላ ይላሉ" በማለት ያስረዳሉ።

"ከጅምሩ ዓለም አቀፍ ጤና ማለት ድንበር ተሻጋሪ እና አንድ አገርን ብቻ የማያሰጋ ነው። የዓለም አቀፍ ጤና ችግሮች ዓለም አቀፋዊ አካሄድ ይፈልጋሉ። የትኛውም አገር ብቻውን ሊፈታው አይችልም" ብለዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በመጀመሪያው የስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ ደስታቸውን ገለጹ ወራት ቢቆጠርም፤ አፍሪካ ውስጥ የሁለትዮሽ ስምምነቱን ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ አሁንም አከራካሪ ሆኖ ቀጥሏል።

በቅርቡ ታንዛኒያ ስምምነቱን ፈርማለች። በርካታ የአፍሪካ አገራት ግን አመስግነው ፊታቸውን ማዞር መርጠዋል። የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ጤና ስትራቴጂዋን በአዲስ መልክ ለማዋቀር የጀመረችው ጉዞ ምን ያህል ርቀት እንደሚሄድ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።