በአርጀንቲና የተሸነፈችው ግብፅ "ኢፍትሐዊነት" እና ለሜሲ አድልዎ ታይቷል ስትል ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መደበኛው የጨዋታው ሰዓት ሊጠናቀቅ 12 ደቂቃ እስከሚቀረው ድረስ ግብፆች በታሪካቸው ትልቁ የሆነውን የዓለም ዋንጫ ድል ለመጎናጸፍ ጫፍ ላይ ነበሩ።
በአትላንታ ስታዲየም በተካሄደው የማክሰኞ ምሽቱ ጨዋታ ግብፆች አርጀንቲናን 2 ለ 0 እየመሩ ነበር። አፍሪካዊቷ አገር ግብፅ ይህንን ጨዋታ ካሸነፈች ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜን ትቀላቀል ነበር።
ጨዋታው ግን በፍጥነት ሌላ አቅጣጫ ያዘ። በአስከፊ ሁኔታም ከግብፅ ቁጥጥር ውጪ ሆነ።
ክርስቲያን ሮሜሮ 79ኛው ደቂቃ ላይ ለአርጀንቲና የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠረ። ከአራት ደቂቃ በኋላ ደግሞ የእግር ኳሱ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ሁለት አቻ ያደረጋቸውን ግብ ከመረብ አሳረፈ።
ኤንዞ ፈርናንዴዝ በጭማሪ ሰዓት ሁለተኛ ደቂቃ ላይ ጭንቅላት ገጭቶ ያስቆጠራት ግብ ደግሞ ደጋፊዎችን ያስፈነደቀውን የአርጀንቲና ድል እርግጥ አደረገችው።
የግብፅ ብሔራዊ ቡድን ያስቆጠረው ግብ በቪዲዮ ረዳት ዳኝነት (ቫር) ከተሻረ በኋላ ተስፋ የቆረጠ እና የተበሳጨ ሆኖ ታይቷል። ግቡ የተሻረው የግብፁ አማካይ ማርዋን አቲያ ኳስ ይዞ መንቀሳቀስ ሲጀመር የሊሳንድሮ ማርቲኔዝን እግርን በትንሹ በመርገጡ ነበር።
ግብፅ እየመራች በነበረበት ወቅት፣ አማካዩ ማርዋን አቲያ የጨዋታው እንቅስቃሴ ሲጀምር የሊሳንድሮ ማርቲኔዝን እግር በትንሹ በመርገጡ ጥፋት ተሰጥቶ የቪዲዮ ረዳት ዳኛ (VAR) በሞስታፋ ዚኮ የተቆጠረውን ሁለተኛ ግብ ከሻረ በኋላ፣ ግብፅ ሙሉ በሙሉ ተስፋ የቆረጠች እና የተበሳጨች ሆናለች።
አርጀንቲና አሸናፊ ያደረጋት ግብ ከማስቆጠሯ ጥቂት ሰከንዶች በፊት ደግሞ የፍጹም ቅጣት ምት አካባቢ ውስጥ በሞሐመድ ሳላህ ላይ ጥፋት እንደተሠራበት በመግለጽም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ፈረንሳዊው ዳኛ ፍራንሷ ሌቴክሲየር የጨዋታውን መጠናቀቅ ሲያስታውቁ፤ ብዙዎቹ የግብፅ ተጫዋቾች የተፈጠረውን ባለማመን ሜዳው ላይ ተዘርረዋል።
ከጨዋታው በኋላ ቃለ መጠይቅ የሰጡት የግብፁ አሠልጣኝ ሆሳም ሐሰን ጨዋታው "ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ እንደተስተናገደ" እና "የኢፍትሐዊነት በደል" እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።
ቢቢሲ ስፖርት ስለ ቅሬታው የፊፋን አስተያየት ጠይቋል።
አሠልጣኙ፤ "ሜዳው ላይ እና ከሜዳ ውጪ ጥያቄ የሚነሳባቸው በርካታ ጉዳዮች ነበሩ" ብለዋል። "በዙሪያው በሙሉ አሉታዊ ነገሮች ነበሩ። የተዓማኒነት ጉዳይ ነው፤ ነገሮች የተከናወኑበት መንገድ ተዓማኒነት ይጎድለዋል" በማለት ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ምናልባት የዓለም ሻምፒዮኖቹ ውድድሩ ውስጥ እንዲቆዩ ይፈልጉ ይሆናል። ምናልባት ሜሲ እየተጫወተ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ" ሲሉም ከስሰዋል።
ቀጥለውም፤ "የዓለም ሻምፒዮኖቹ በሁሉም ደረጃ ድጋፍ ተሰጥቷቸዋል። ውጤቱ ላይ ከአርጀንቲና በኩል ጫናዎች ያሉ ይመስላል" ብለዋል።
የትናንቱ ጨዋታ ያልታየበት ነገር አልነበረም። ፍጹም ቅጣት ምት በግብ ጠባቂ ከሽፏል፣ ግብ ተሽሯል፣ ቀይ ካርድ ተሰጥቷል፤ የአርጀንቲናም አስደናቂ ማንሰራራት ታይቶበታል።
የግብፁ ግብ ጠባቂ ሞስታፋ ሾቤር የሜሲን የፍጹም ቅጣት ምት በሚያስደንቅ ሁኔታ በማዳን ቡድኑን ከግብ ታድጎ ነበር። ከዚያ በኋላ ፈርዖኖቹ ያስቆጠሩት ሌላ ግብ ቫር ውሳኔ ተሽሯል።
ሞ ሳህላ ላይ ጥፋት መሥራቱን እየገለጹ የነበሩት ግብፆች በጭማሪ ሰዓት ፈርናንዴዝ ሌላ ግብ ሲያስቆጥርባቸው ንዴታቸው ተባብሷል። ከዳኛው ጋር በተፈጠረ ንትርክም የግብፅ የመጠባበቂያ ወንበር ላይ ከነበሩት አባላት አንዱ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል
አርጀንቲና ሦስተኛውን ግብ ካስቆጠረች በኋላ በእጃቸው ተቃውሟቸውን የገለጹት የግብፁ ዋና አሠልጣኝም የቢጫ ካርድ ተሰጥቷቸዋል።
አሠልጣኙ በእጆቻቸው የኤክስ ምልክት በመሥራት ያሰሙት ተቃውሞ ተጫዋቾች እና አሠልጣኞች ዘረኛ ድርጊት ሲፈጸም ጥቅም ላይ የሚውል ነው።















