ፊፋ፤ አይሾውስፒድ በአርጀንቲና ደጋፊ ተፈጸመበት የተባለውን የዘረኝነት ጥቃት መመርመር ጀመረ

አይሾውስፒድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዓለም እግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ የሆነው ፊፋ ታዋቂው አሜሪካዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ አይሾውስፒድ ላይ የአርጀንቲና ደጋፊ ሰንዝሮታል ስለተባለው የዘረኝነት ጥቃት ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተካታዮች ያሉት አሜሪካዊው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ ላይ የዘረኝነት ጥቃት ደርሶበታል የተባለው ባለፈው ሳምንት አርብ ሰኔ 26/2018 ዓ.ም. በተካሄደው የአርጀንቲና እና የኬፕ ቬርዲ ጨዋታ ወቅት ነው።

በዩቲብ 57 ሚሊዮን እንዲሁም በቲክቶክ ላይ 53 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት አይሾውስፒድ፤ አሜሪካ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ የዓለም ዋንጫ ግጥሚያዎችን በቀጥታ እያስተላለፈ ይገኛል።

ይህ ታዋቂ የማኅበራዊ ሚዶያ ይዘት ፈጣሪ ባለፉት ጨዋታዎች ወቅት ከፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እንዲሁም የቀድሞው የባርሴሎና እና የኤሲ ሚላን ተጫዋች ዝላታን ኢብራሂሞቪችን ጭምር በመጋበዝ ለተከታዮቹ ዝግጅቶችን አቅርቧል።

በትክክለኛ ስሙ ዳረን ጄሰን ዋትኪንስ ጁኒየር በመባል የሚታወቀው የ21 ዓመቱ አይሾውስፒድ፤ አርጀንቲና ኬፕ ቬርዲን 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ባሸነፈችበት ጨዋታ ወቅት የኬፕ ቬርዲን ማሊያ ለብሶ በስታዲየሙ ውስጥ ተገኝቶ ነበር። በወቅቱም ከአንድ የአርጀንቲና ደጋፊ ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተው ታይቷል።

በሁለቱ መካከል የተደረገው የቃላት ልውውጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ሥርጭቱ ላይ የተላለፈ ሲሆን ይህንን ተከትሎም ውዝግቡ ሲካረር መታየቱን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ማያሚ ውስጥ በሚገኘው በሀርድ ሮክ ስታዲየም የተካሄደውን ጨዋታ በቀጥታ ሲያስተላልፍ በነበረው አይፒሾውስፒድ አርጀንቲናዊው ደጋፊ በስፓኒሽ ቋንቋ ከቆዳ ቀለሙ ጋር በተያያዘ የዘረኝነት ቃላት መሰንዘሩን ተነግሯል።

ይህንንም ክስ ተከትሎ የዓለም እግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ ባለፈው አርብ የጥሎ ማለፍ ጨዋታው በተደረገበት ስታዲየም ውስጥ ስላጋጠመውን ክስተት እንዲያውቅ መደረጉን እና "አስቸኳይ ምርመራ መጀመሩን" አስታውቋል።

ፊፋ ክስተቱ የዘረኝነት ጥቃት መሆኑን ከማመልከት ውጪ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጥ "የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር አንድነትን፣ ብዘሃነትን እና መከባበርን ለማጉላት" የሚካሄድ መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።

"ውድድሩ ከዓለም ዙሪያ ባህሎችን እና ማኅበረሰቦችን በአንድነት የሚያሰባስብ ሲሆን፣ እነዚህን እሴቶች የሚቃረን ተግባር የሚፈጽም ማንኛውም ሰው በጨዋታዎቹ ሜዳ ቦታ አይኖረውም" በማለት ዘረኝነትን እንደማይታገስ ገልጿል።

በአይሾውስፒድ ላይ ተፈጽሟል የተባለው ጥቃት የተሰማው ፈረንሳያዊው ተጫዋች ኪሊያን ምባፔ በፓራጓይ የምክር ቤት አባል ላይ ተመሳሳይ ክስ ካሰማ በኋላ ነው።

ሴሌስቴ አማሪላ የተባሉ የፓራጓይ ምክር ቤት አባል የአገራቸው ብሔራዊ ቡድን በፈረንሳይ ተሸንፎ ከውድድሩ መሰናበቱን ተከትሎ በፈረንሳያዊው የፊት መስመር ተጫዋች ላይ በኤክስ ገጻቸው ያሰፈሩት ፅሑፍ ቁጣን ቀስቅሷል።

ግለሰቧ የኪሊያን ምባፔን የትውልድ አገር እና ትምህርቱን በመጥቀስ ዘረኛ አስተያየት ከሰነዘሩ በኋላ ተጫዋቹ ጽሁፉ የምክር ቤት አባሏ ያሉበትን ኃላፊነት የማይመጥን "አስጸያፊ" በማለት ምላሽ ሰጥቷል።

የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ግለሰቧ የሰነዘሩት አስተያየት "ፍጹም አስነዋሪ እና ተቀባይነት የሌለው" በማለት የወንጀል ክስ እንደሚከፍት አስታውቋል።