ትራምፕ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲያጤን ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ጉዳይን በድጋሚ እንዲመለከት እንደሚጠይቁ ተናገሩ።
ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት ባለፈው ሳምንት ከፍተኛው ፍርድ ቤቱ በአሜሪካ የተወለዱ ልጆች ዜግነት የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ነው።
ውሳኔው 150 ዓመታት ባስቆጠረው ፖሊሲ ላይ ገደብ እንዲጣል ትራምፕ ያስተላለፉትን ፕሬዚደንታዊ ትዕዛዝ ውድቅ አድርጓል።
ይህንን ተከትሎም ትራምፕ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በድጋሚ እንዲሰማ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።
ትራምፕ ረቡዕ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ፣ " ይህንን ውሳኔያቸውን ካልለወጡ የፍትሕ እርምጃው አሜሪካን ያጠፋታል" ብለዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ዓይነት ጥያቄን የሚቀበል ቢሆንም ውሳኔ ባሳለፈበት ጉዳይ ድጋሚ ችሎትን እምብዛም አይፈቅድም።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያሳለፈበትን ጉዳይ ለመጨረሻ ጊዜ በድጋሚ የሰማው ከ60 ዓመታት በፊት ነው።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው የተረታ አካል አቤቱታውን በ25 ቀናት ውስጥ እንዲያቀርብ ይፈቅዳል።
ሆኖም ጉዳዩ በድጋሚ እንዲሰማ ዘጠኝ አባላት ያሉት አብዛኞቹ ዳኞች መፍቀድ አለባቸው።
ፍርድ ቤቱ በመወለድ በሚገኝ ዜግነት ላይ ሰኔ 30 ያሳለፈው ውሳኔ የፕሬዚደንቱን የኢሚግሬሽን አጀንዳ ወደ ኋላ የመለሰ ነው።
የማኅበረሰብ መብት ተሟጋች ቡድኖች ግን ውሳኔውን በበጎ ተቀብለውታል።
በስድስት ድጋፍ እና በሦስት ተቃውሞ በተላለፈው ውሳኔ ዳኛ ጆን ሮበርት በ14ኛው የተሻሻለው ሕገ መንግሥት መሠረት በሕገ ወጥ መንገድም ሆነ ጊዜያዊ ነዋሪ ከሆኑ ወላጆች በአሜሪካ የሚወለዱ ልጆች በመወለድ የአሜሪካ ዜጋ መሆናቸውን አረጋግጧል።
ትራምፕ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች እና አንዳንድ ጊዜያዊ ጎብኝዎች "በቁጥጥሬ ሥር አይደሉም፤ በመሆኑም ከእነርሱ የሚወለዱ ልጆች በመወለድ የሚገኝ ዜግነት ለማግኘት ብቁ አይደሉም" ሲሉ በፕሬዚደንታዊ ትዕዛዛቸው ይህንን መብት ለመገደብ ፈልገው ነበር።
ሆኖም ዋና ዳኛውን ጀስቲስ ሮበርትን ጨምሮ አምስቱ ዳኞች የትራምፕ ትዕዛዝ 14ኛውን የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ይጥሳል ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
ዳኛ ብሪት ካቫኖህም በተናጠል ባጋሩት ጽሑፍ የትራምፕ ትዕዛዝ የፌደራል ሕግን ይጥሳል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
ትራምፕ ግን ውሳኔው ከተላለፈ በኋላም በመወለድ የሚገኝ መብት እንዲቀር በሕግ መታገላቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።
አሜሪካ በተሻሻለው 14ኛው ሕገ መንግሥት መሠረት ከአውሮፓውያኑ 1868 ጀምሮ በአገሪቷ ለሚወለዱ ሁሉም ሕፃናት ዜግነት ትሰጣለች።















