የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ቢሯቸው ውስጥ በተቋቋመው ሐሰተኛ ተቋም ላይ ምርመራ እንዲደረግ አዘዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ቦላ ቲኑቡ ቢሯቸው ውስጥ እንደተቋቋመ በገለጹት ሐሰተኛ የመንግሥት ተቋም ላይ ምርመራ እንዲደረግ አዘዙ።
'ፕሬዚደንሻል ፎሪን ኢንተርቬንሽን ፕሮሞሽን ካውንስል (ፒኤፍአይፒሲ) የሚል ስም የያዘው ተቋም፤ በ950 ሺህ ዶላር የሕዝብ ገንዘብ እንደተመሠረተ ፕሬዚደንቱ ገልጸዋል።
መንግሥት የማያውቀው ይህ ምክር ቤት እንዲቋቋም በፕሬዚደንቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፌሚ ግባጃ ቢያሚላ እንደተፈረመ ተደርጎ የወጣው ደብዳቤም ሐሰተኛ መሆኑ በፖሊስ ምርመራ ተረጋግጧል።
ፖሊስ የተቋሙ ዳይሬክተር እንደሆነ አድርጎ ራሱን ያቀረበውን አዴኒይ አዴይሚ ማቲውን በማስመሰል፣ በማጭበርበር እና ሌሎች ተያያዥ ወንጀሎችጠርጥሮ እየፈለገው ነው።
አዴይሚ ከመሰወሩ በፊት ጥፋተኛ እንዳልሆነ እና ለሕይወቱ እንደሚሰጋ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።
ተቋሙ በሕጋዊ መንገድ መመስረቱን የገለፀው አዴይሚ ፍርድ ቤት ቀርቦ ስሙን እንደሚያድስ ቃል ገብቷል።
ጨምሮም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሹመቱ ሒደት ወቅት ጉቦ እንደጠየቁ እና በኋላ ላይ የምክር ቤቱን ገንዘብ ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ነበር ሲል ከስሷል።
የፕሬዚደንቱ ቢሮ የቀረቡትን እነዚህን ክሶች አስተባብሏል።
አዴይሚ ተቋሙ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ሲባል እአአ በ2024 መቋቋሙን ጠቅሷል።
ሆኖም የተደረገ ስምምነት ስለመኖሩ የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም።
ተቋሙ ሦስት ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ቃላቸውን እንዲሰጡ በፖሊስ ተጠይቀዋል።
ፕሬዚደንት ቦላ ቲኑቡም ማክሰኞ ዕለት ገለልተኛ የሆነው የሙስና እና ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች ኮሚሽን በተቋሙ ላይ ምርምራ እንዲያካሂድ እና በ30 ቀናት ውስጥ ሙሉ ሪፖርት እንዲያቀርብ አዝዘዋል።
ተቋሙ በመዲናዋ አቡጃ በርካታ የመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በሚገኙበት ትልቅ ሕንፃ ውስጥ ቢሮ እንደነበረው እና በናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ የተከፈቱ አካውንቶች እንዳሉት ቢቢሲ ማወቅ ችሏል።
ሆኖም የገንዘብ ጽሕፈት ቤት ተቋሙ በማዕከላዊ ባንኩ ምንም ዓይነት ተንቀሳቃሽ ሒሳብ እንደሌለው እና ምንም ዓይነት ገንዘብ ወይም ደመወዝ አለመቀበሉን ገልጿል።
በአቡጃ ለሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበው የክስ መዝገብ እንደሚያሳየው አዴይሚ እና ሌሎች ሁለት ተከሳሾች ሐሰተኛ የሆነውን ምክር ቤት ለማቋቋም ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም፣ በስሙ በርካታ የባንክ አካውንቶችን በመክፈት እንዲሁም መንግሥት ለማያውቀው ተቋም እውቅና በመፈለግ ተከስሰዋል።
ሐሰተኛ ተቋሙ ሕጋዊነትን ለማግኘት ያስቻለውን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲሁም በመንግሥት አሰራር ውስጥ ያለው ክፍተት እንዲመረመር ፕሬዚደንቱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ቲኑቡ የፕሬዚደንታዊ ቢሮ እና የፌደራል ተቋማት አሰራር ከማጭበርበር ፣ ማስመሰል እና ይፋዊ ማንነትን ያለአግባብ ከመጠቀም፣ የሕዝብ አገልግሎት ደካማ ጎንን ከመበዝበዝ ሊጠበቁ ይገባል ብለዋል።
ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘም በሕጉ መሠረት ቅጣት እንደሚጠብቀው ፕሬዚደንቱ አክለዋል።
የሲቪል ማበሕረሰቦች፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከፍተኛ የሕግ ባለሙያዎችም ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።















