ትራምፕ የሙስና ክስ የቀረበባቸውን የአሜሪካ አምባሳደር እንዲለቁ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በግሪክ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ኪምበርሊ ጊልፎይል ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መጠየቁን ዋይት ሐውስ አስታወቀ።
የቀድሞ የፎክስ ኒውስ አቅራቢ የሆኑት አምባሳደሯ የትራምፕ ለጋሽ ከሆኑ ግለሰብ ገንዘብ ጠይቀዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ ምክንያት ትችት በርትቶባቸው ሰንብተዋል።
ማክሰኞ ዕለት ትራምፕ አምባሳደር ጊልፎይል መልካም ሥራ መሥራታቸውን ጠቁመው፤ ነገር ግን በግሪክ ከዚህ በኋላ እንደማይቆዩ ተናግረዋል።
"የማነበውን ነገር እየወደድኩት አይደለሁም" ብለዋል።
ጊልፎይል የቀረበባቸውን ክስ ውሸት ነው በማለት ራሳቸውን ለመከላከል ቃል ገብተዋል።
አዲሷ የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ኬቲ ዘካራያ በአጭሩ መግለጫቸው ጊልፎይል ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንዲለቅቁ መጠየቃቸውን አስታውቀዋል።
"ለቡድኑ ጥሩ አበርክቶ ነበረች፤ መልካሙን ሁሉ እንመኝላታለን" ብለዋል።
የ57 ዓመቷ የካልፎርኒያ ገዢ ጋቨን ኒውሰም የቀድሞ ባለቤት የሆኑት ኪምበርሊ ጊልፎይል በአቴንስ ልዑክ ሆነው መጀመሪያ የታጩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ዳግም ከመምጣታቸው ከአንድ ወር ቀደም ብሎ እ.አ.አ ታኅሳስ 2024 ነበር።
በዚህ ወቅት እጮኛዋ ከነበሩት የትራምፕ ልጅ ዶናልድ ትምፕ ጁኒየር ጋር መለያየታቸው ተዘግቧል።
ማክሰኞ ዕለት ረዘም ባለ የኤክስ ልጥፋቸው ጊልፎይል ፕሬዝዳንት ትራምፕን አመስግነው ሁሌም ቢሆን ታማኝ ደጋፊ እንደሚሆኑ እና ምንም ስህተት እንዳልሰሩ ገልፀዋል።
"ስሜን፣ ዝናዬን እና ታማኝነቴን በብርቱ እከላከላለሁ" ብለዋል። አምባሳደሯ አክለውም "የአስርት ዓመታት የሕዝብ አገልግሎቴን ሐሰተኛ ክስ እንዲሸፍነው አትፍቀዱ" ብለዋል።
የአምባሳደርነት ዘመናቸው ባለፈው ሣምንት ይፋ በሆነው ተገቢ ያልሆነ ባህሪያቸው ጥላ አጥልቶበታል።
መጀመሪያ በዎል ስትሪት ጆርናል ሪፖርት የተደረገ እና በኋላ በቢቢሲ የታየው የመልዕክት ልውውጦች ጊልፎይል ኤሪክ ዲተርስ ከተባሉ የረጅም ጊዜ የትራምፕ አጋር ገንዘብ ሲጠየቁ እና ሲማፀኑ ያመለክታል።
ጠበቃዎቻቸው የመልዕክቶቹን ትክክለኛነት ያጣጣሉ ሲሆን፤ አምባሳደር ከመሆናቸው በፊት ለሰሩት የንግግር እና የማማከር ሥራ ክፋያ ነው የጠየቁት ብለዋል።
ወል ስትሪት ጆርናል ያገኘው የድምፅ ቅጂ ጊልፎይል ከታዋቂ የግሪክ ባለሃብት ያላቸውን ግንኙነት እና ቅንጡ ሽርሽሮች እና በግል አውሮፕላኖች ያደረጉትን በረራም ሲያሞካሹ ተደምጠዋል።
እንደ ጋዜጣው ከሆነ ኪምበርሊ ጊልፎይል ለአቴንስ ባለሥልጣናት አሜሪካ የግሪክን መንግሥት መገልበጥ እንደሚችል ተናግረዋል።
ባለፈው ሣምንት በአቴንስ ጉብኝ ሲያደርጉ ከአምባሳደሯ ጋር የታዩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በክሱ ደስተኛ አለመሆናቸው ተዘግቧል።
ጊልፎይል ከሥራቸው እንዲለቁ ተጠይቀዋል መባሉን ተከትሎ ኤሪክ ዲተርስ ለቢቢሲ "ለአሜሪካ ዲፕሎማሲ ትልቅ ቀን ነው" ብለዋል።
ለንግግር እና ማማከር ሥራ ክፍያ ነበረባቸው በሚል በአምባሳደሯ ጠበቆች በኩል የቀረበውን ዲተርስ "ሙሉ ለሙሉ ውሸት" ነው በማለት ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
ጊልፎይል የዶናልድ ትራምፕ የረጅም ዘመን የፖለቲካ አጋር ሲሆኑ፤ ከልጃቸው ጋርም ዓመታትን የዘለቀ የፍቅር ግንኙነት ነበራቸው።
ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ከልጃቸው ጋር የረጅም ዓመት ግንኙነት ቢኖራቸውም አምባሳደሯ እንደ ቤተሰብ አባል እንዳልነበሩ ተናግረዋል።




































