የቀድሞው የወሮበላ ቡድን መሪ የቱፓክ ሻኩር ግድያን በማቀነባበር ወንጀል 40 ዓመት ተፈረደበት

ዱዋን ዴቪስ በላስ ቬጋስ ፍርድ ቤት ክርክር ወቅት
የምስሉ መግለጫ, ዱዋን ዴቪስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የ63 ዓመቱ የቀድሞ የወሮበላ ቡድን መሪ ዱዋን "ኪፍ ዲ" ዴቪስ ቱፓክ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማቀነባበር ወንጀል የ40 ዓመት እስር ተፈረደበት።

በመስከረም ወር ክሱን ለመመለከት የተሰባሰቡ የሕዝብ ፍርድ ሰጪዎች (ጁሪዎች) ታዋቂው የሂፕ ሆፕ ሙዚቀኛ ቱፓክ ሻኩር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 7 1996 በጦር መሣሪያ ተኩሶ በመግደል በተመሰረተበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ አግኝተውታል።

ተከሳሹ ይግባኝ አንደሚጠይቅ ተናግሯል።

አቃቤ ሕግ ዴቪስ መሣሪያውን ባይተኩስም ግድያውን የፈጸመው ቡድን መሪ ነበር በማለት ተከራክረዋል። ግለሰቡ በጻፈው የግል ማስታወሻ ላይ ግድያው የተፈጸመበትን መሣሪያ መስጠቱን አምኗል።

ዴቪስ ላይ የተላለፈው ፍርድ የድምጻዊው አድናቂዎች ለ30 ዓመታት ገዳዩ ማን እንደሆነ ለማወቅ የነበራቸውን መሻት ያሳካ ነው።

አቃቤ ሕግ ማርክ ዲጊያኮሞ ማክሰኞ ዕለት የፍርድ ውሳኔው በሚሰጥበት ወቅት ዴቪስ ለዓመታት "በአደባባይ ሲሸልል " እና በሻኩር ግድያ ላይ ስለነበረው ሚና ደረቱን ነፍቶ ሲናገር "በዓለም ላይ መጠነ ሰፊ ተጽዕኖ" አለኝ ሲል ነበር ብለዋል።

የሻኩር እህት፣ ሴኪዋ ሻኩር ለፍርድ ቤቱ "ቱፓክን ለረጅም ጊዜ ማጣት ቤተሰቤን አሽመድምዶታል" ብላለች

"በጣም ብዙ ተስፋዎች ነበሩት፣ የተሻለ ዓለም ለማምጣትም ፍላጎት ነበረው" ስትል ወንድሟ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለመርዳት ዕቅድ እንደነበረው ገልጻለች።

ሴኪዋ ሻኩር ዳኛው ለዴቪስ ከፍተኛውን ቅጣት እንዲወስኑ ጠይቃ የነበረ ሲሆን ዴቪስ እስር ቤት ውስጥ እንደሚከርም "ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ያደረግከውን ነገር እዚያ ሆነህ ታሰላስለዋለህ" ስትል ተናግራለች።

የሻኩር ወንድም ሞሪስ ሻኩርም በበኩሉ የፍርድ ቤቱ ዳኛ "ረዥሙን ቅጣት" እንዲጥልበት ጠይቀዋል።

ዳኛ ካርሊ ኪርኒ ተከሳሹ ዴቪስ የሚናገረው ነገር ካለ ጠይቀው "ደህና ነኝ። በዚህ ጉዳይ ላይ ይግባኝ እንደምጠይቅ እርግጠኛ ነኝ" ሲል መልሷል።

ኪርኒ ፍርዱን ከመስጠታቸው በፊት "የቤተሰብን አባል ሕይወት መንጠቅ የለብህም፤ ሕይወቱን፣ የወደፊት ተስፋውን በሙሉ ነጥቀህ መውሰድ አትችልም። በተለይም ያ ሰው ቱፓክ ሻኩር ሲሆን። ዓለም ስለ እሱና ስለ ሞቱ ፈጽሞ አልረሳውም።"

በግድያ ችሎት ላይ የታየ የ1996 የራፐር ቱፓክ ሻኩር (በስተግራ) እና የማሪዮን "ሱጅ" ናይት ፎቶ
የምስሉ መግለጫ, በግድያ ችሎት ላይ የታየ የ1996 የራፐር ቱፓክ ሻኩር (በስተግራ) እና የማሪዮን "ሱጅ" ናይት ፎቶ
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ የራፕ ድምጻውያን አንዱ የነበረው ቱፓክ በሙያው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት በ25 ዓመቱ ነበር የተገደለው። አርቲስቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ75 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎችን ሸጧል።

የ 'ሳውዝ ሳይድ ኮምፕተን ክሪፕስ' የጎዳና ላይ ወሮበላ ቡድን መሪ የነበረው ዴቪስ፣ ሻኩርን የገደለውን ጥይት በቀጥታ ባይተኩስም፣ የወንድሙ ልጅ ኦርላንዶ አንደርሰን እንዲተኩስ ማዘዙን እና ሽጉጡን ማቅረቡን በማንሳት ዐቃቤ ሕጎች በችሎቱ ላይ ተከራክረዋል።

ከግድያው ከጥቂት ሰዓታት በፊት በላስ ቬጋስ ከሻኩር እና ከራፐሩ የቡድን አባላት ጋር የተፈጠረውን ፀብ ተከትሎ ዴቪስ ግድያውን ለመፈፀም ማቀዱን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ጉዳዩ ላለፉት 30 ዓመታት በአሜሪካ በጣም ከሚታወቁ ያልተፈቱ ጉዳዮች አንዱ ሆኖ የቆየ ሲሆን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሴራዎችም አስነስቷል።

የሻኩር ግድያ የተፈፀመው በኢስት ኮስት እና በዌስት ኮስት የራፕ ትዕይንቶች መካከል ከፍተኛ ፉክክር በነበረበት እንዲሁም በሂፕ-ሆፕ ውስጥ ሥር በሰደዱት በብሌድስ እና ክሪፕስ የወሮበላ ቡድኖች መካከል ግጭት በነበረበት ወቅት ነው።

እአአ በ2008፣ በመድረክ ስሙ ኖቶሪየስ ቢ.አይ.ጂ. በመባል የሚታወቀውን ራፐር ክሪስቶፈር ዋላስ ሞትን በተመለከተ ፖሊስ ባደረገለት ምስጢራዊ ቃለ ምልልስ ወቅትም በሻኩር ሞት ላይ ስለነበረው ሚና ተናግሮ ነበር።

ዴቪስ በ2019 ባሳተመው 'ኮምፕተን ስትሪት ሌጀንድ' የተባለ መጽሐፉ ላይ ባሰፈረው ማስታወሻም እንዲሁ ስለተጫወተው ሚና የበለጠ ማብራሪያ ሰጥቷል። ይህም በስምምነታቸው መሠረት በምስጢር ተይዞ ነበር የቆየው።

ነገር ግን በመጽሐፉ ይፋ ያደረገው እውነታ እና የሚዲያ ቃለ ምልልሶቹ፣ ምንም ዓይነት የወንጀል ክስ እንዳይቀርብበት ያደረገውን እና ከባለሥልጣናት ጋር የፈፀመውን ስምምነት ውድቅ አድርገውታል። የግድያ ክስ ችሎት ላይ ከፖሊስ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል ፍርድ ቤቱ ወስኗል።