ማንቸስተር ሲቲ የፈፀማቸው የሕግ ጥሰቶች እርስዎ በሚደግፉት ቡድን ላይ ምን ያህል ጉዳት አደረሰ?

የማንችስተር ሲቲ አርማ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ማንቸስተር ሲቲ ሦስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን፣ አንድ የኤፍኤ ካፕ እና ሦስት የኢኤፍኤል (ካራባኦ) ካፕ ዋንጫዎችን ማሸነፍ የቻለ ቡድን ለመገንባት "ሐሰተኛ ውሎችን" እንደተጠቀመ ተገልጿል።

ክለቡ ከአውሮፓውያኑ 2009 እስከ 2018 ባለው በዚህ ጊዜ ውስጥ በፕሪሚየር ሊጉ ፈጽሟቸዋል ተብለው ከቀረቡበት 115 ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ክሶች በ114ቱ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ሲቲ ዋንጫዎችን ባሸነፈባቸው በእነዚህ ጊዜያት ለጉዳት የተዳረጉት ታዲያ በሊጉ ሁለተኛ የወጡ ወይም በዋንጫ ፍጻሜዎች የተሸነፉ ቡድኖች ብቻ አይደሉም።

ከሲቲ ሕገ ወጥ ድርጊት ጋር በተገናኘ የቻምፒየንስ ሊግ ቦታ ያመለጣቸው፣ ከሊጉ ለመውረድ የተገደዱ እና የሚገባቸውን የፕሪሚየር ሊግ የገንዘብ ሽልማቶች ያላገኙም ይኖራሉ።

በ2009 እና 2018 መካከል ከሲቲ ውጭ 35 ሌሎች ክለቦች በእንግሊዝ ከፍተኛው ሊግ ተሳትፈዋል።

እነዚህ ክለቦች በሆነ መንገድ በገንዘብ እንደተጎዱ ወይም የሚገባቸውን ገቢ እንዳጡ ሊከራከሩ ይችላሉ።

በእርግጥ ሲቲ የቀረቡበትን ክሶች ውድቅ በማድረግ ይግባኝ አቅርቧል።

ሆኖም እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የስፖንሰርሺፕ ገቢውን በ830 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍ ከማድረግ እንዲሁም ከ90 ሚሊዮን ፓውንድ ተጨማሪ ወጪዎች ጋር ተያይዞ በቀረቡበት ክሶች ሁሉ ጥፋተኛ ተብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፕሪሚየር ሊጉ እንዳለው፣ ማንቸስተር ሲቲ ያገኘውን ከ830 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ምስጢራዊ የገንዘብ ድጋፍ ለመደበቅ ከበርካታ የንግድ አጋሮች ጋር "ሐሰተኛ ውሎችን" አዘጋጅቶ ተፈራርሟል።

ይህ ገንዘብ ሒሳብ ውስጥ ባይገባ፣ የውድድሩ አጠቃላይ ገጽታ ፈጽሞ ሌላ መልክ ይኖረው ነበር።

በ2008 ሼክ ማንሱር ማንቸስተር ሲቲን ሲገዙ፣ የክለቡ ደረጃ አሁን ከሚገኝበት እጅግ የራቀ ነበር።

የእንግሊዝ ትልቁ የእግር ኳስ ውድድር ስያሜውን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ከመቀየሩ በፊት በነበረው የመጨረሻው የ1991-92 የሊግ ውድድር አምስተኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀ በኋላ፣ የማንሱር ባለቤት ከመሆኑ በፊት ሲቲ ያስመዘገበው ከፍተኛው የሊግ ውጤቱ በ2004-05 ያሳካው ስምንተኛ ደረጃ ነበር።

የአቡ ዳቢው ገንዘብ ግን ሌላ ገፅታን አላብሶታል። የፕሪሚየር ሊጉ ገለልተኛ ኮሚሽን "ድብቅ የገንዘብ ድጋፍ ዘዴ" ብሎ በገለፀው አሠራር አማካኝነት ወደ ክለቡ ሕግን የተላለፈ ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰሰ። ይህም በ2008-09 ከስቶክ ሲቲ ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ የነበረውን የሲቲ የስፖንሰርሺፕ ገቢ፣ በአሁኑ ወቅት የማንቸስተር ዩናይትድን ገቢ እስከሚበልጥ ደረጃ አድርሶታል።

በአቡዳቢው ባለፀጋ እጅ ከገባ ወዲህ የሲቲ ዝቅተኛው ውጤት በ2009-10 የውድድር ዘመን አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀበት ነው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በፕሪሚየር ሊጉ ከአራቱ ከፍተኛ ደረጃዎች ውጭ አንድም ጊዜ አጠናቆ አያውቅም።

ቢቢሲ ስፖርት ከሲቲ ድርጊት ጋር በተያያዘ በፕሪሚየር ሊጉ በተሳተፉ ክለቦች ላይ ሊደርስ የቻለውን የገንዘብ ተጽዕኖ፣ ቁጥሮቹን በዝርዝር አስልቶ ገምግሟል።

የሲቲ ድርጊት በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለክለቡ 1.17 ቢሊዮን ፓውንድ ሲያስገኝ በሌሎች ክለቦች ላይ ያሳደረው አጠቃላይ የገንዘብ ተጽዕኖ 799.5 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚደርስ የቢቢሲ ስሌት ያመለክታል።

ከ2009 እስከ 2018 በሊጉ የተሳተፉ 35 ክለቦች ካጡት ገንዘብ ውስጥ 188.2 ሚሊዮን ፓውንድ ከፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሽልማት ይገኝ የነበረ፣ 349.7 ሚሊዮን ፓውንድ ከሊጉ የወረዱ ክለቦች በመውረድ ያጋጠማቸው ወጪ፣ 217.8 ሚሊዮን ፓውንድ ደግሞ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ያመለጣቸው ክለቦች ያጡት የሽልማት ገንዘብ ነው።

በዚህ ጊዜ ውስጥ ሲቲ ካገኘው 1.17 ቢሊዮን ፓውንድ ውስጥ 812.3 ሚሊዮን ፓውንድ ከፕሪሚየር ሊጉ በሽልማት እና ከስርጭት መብት የተገኘ ገቢ፣ 363.4 ሚሊዮን ፓውንድ ከቻምፒየንስ ሊግ፣ 900,000 ፓውንድ ከኤፍኤ ካፕ ድል እና 300,000 ፓውንድ ከሦስቱ የኢኤፍኤል ካፕ ድሎች ያገኘው ነው።

በሲቲ የ9 ዓመታት ሕገ ወጥ ድርጊት ከፍተኛውን ጉዳት ያስተናገደው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ነው። ቶተንሃም 120 ሚሊዮን ፓውንድ እንዳጣ ይታመናል።

ሁል ሲቲ፣ ስዋንሲ፣ ኒውካስትል፣ ሊቨርፑል እና ቼልሲ ደግሞ ቀጣዮቹን እስከ ስድስት ያሉ ደረጃዎች ይይዛሉ።

  • ቶተንሃም፡ 119,904,410 ፓውንድ
  • ሁል ሲቲ፡ 99,003,349 ፓውንድ
  • ኤቨርተን፡ 66,432,752 ፓውንድ
  • ስዋንሲ፡ 63,134,803 ፓውንድ
  • ኒውካስትል፡ 60,476,281 ፓውንድ
  • ሊቨርፑል፡ 52,333,449 ፓውንድ
  • ቼልሲ፡ 45,763,255 ፓውንድ
  • ኖርዊች፡ 43,826,069 ፓውንድ
  • ዊጋን፡ 39,605,000 ፓውንድ
  • በርንሌይ፡ 31,140,969 ፓውንድ
  • አርሰናል፡ 30,855,609 ፓውንድ
  • ቦልተን፡ 26,489,584 ፓውንድ
  • በርሚንግሃም፡ 25,166,636 ፓውንድ
  • ሳውዛምፕተን፡ 20,350,549 ፓውንድ
  • ማንችስተር ዩናይትድ፡ 18,349,716 ፓውንድእንዳጡ የተገመቱ ቀዳሚ 15 ክለቦች ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ክለቡ ጥፋተኛ የተባለባቸውን ክሶች በማስተባበል ያቀረበው ይግባኝ በመታየት ላይ ነው።

ይግባኙ የሚታይበት ጊዜ 12 ሳምንት ሲሆን ታኅሣሥ ወር ላይ ውጤቱ ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ከይግባኙ በኋላ ጥፋተኝነቱ ከተረጋገጠ፣ ከከፍተኛ የነጥብ ቅነሳ ከፕሪሚየር ሊጉ እስከመባረር የሚደርሱ ቅጣቶች ሊጣሉበት እንደሚችሉ ግምቶች ተቀምጠዋል።

በ9 ዓመታት ውስጥ ያሸነፋቸውን ዋንጫዎች መቀማት፣ የገንዘብ ቅጣት እና ለዓመታት ሊቀጥል የሚችል የዝውውር እገዳም በሲቲ ላይ ሊጣሉ ይችላሉ ከተባሉ ቅጣቶች መካከል ናቸው።