ጋና በሕዝብ ማመላሻዎች ላይ የሚሰብኩ ፓስተሮችን በእስር የሚቀጣ ሕግ ለምን አወጣች?

በጋና ዋና ከተማ አክራ የሚገኘው የኒዮፕላን መናኸሪያ የጠዋቱ ግርግር ከመጀመሩ በፊት በክርስቲያኖች የአምልኮ እና የዝማሬ ድምጽ ይሞላል።
ተሽከርካሪዎች ተጓዦችን ወደየመዳረሻቸው ለመውሰድ ሲዘገጃጁ ለወንጌል ስብከት የሚያሟሙቁ ክርስቲያኖች ተሰባስበው ይፀልያሉ።
ቦአቴንግ ቢስማርክ ጀምስ በመናኸሪያው ከበሮ እየተደለቀ፣ አምልኮ እና ዝማሬ እየተካሄደ 13 ምዕመናን፣ ዘጠኝ ወንዶችን እና አራት ሴቶችን፣ በመምራት በጋና ውስጥ ወደሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ለሚጓዙ አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎች ይፀልያል።
ጋና የአደባባይ ስብከት በብዛት የሚካሄድባት አብዛኛው ሕዝቧ ክርስቲያን የሆነባት አገር ናት።
በረጅም ርቀት አውቶቡሶች ላይ፣ ፓስተሮች ወንጌልን ሲሰብኩ ማየት እና መስማት የተለመደ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ከሹፌሩ አጠገብ ባለው ከፍ ያለ ቦታ ላይ ቆመው፣ ሌሎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን እያነበቡ ኃጢአተኞች ከፍ ባለ ድምፅ ንስሐ እንዲገቡ ይጠራሉ። ጉዞው ረዥም ቢሆን እንኳ ስብከታቸውን አያቋርጡም።
ምዕመናን አንዳንድ ጊዜ የሰባኪዎቹን ጥረት ለመደገፍ ገንዘብ ይሰጣሉ።
ነገር ግን ጋና ይህንን የሚያስቆም አዲስ ሕግ አውጥታለች።
በሕዝብ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ሲሰብክ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ ስምንት ወር በሚደርስ እስራት ወይንም እስከ 52 ዶላር ድረስ እንደሚቀጣ ሕጉ ይደነግጋል።
ሕጉ አክሎም ይህንን ተላልፎ የተገኘ ግለሰብ የገንዘብም የእስርም ቅጣት በተመሳሳይ ጊዜ ሊቀጣ እንደሚችል አስፍሯል።
በግንቦት ወር በፓርላማ የፀደቀው እና ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ተግባራዊ መሆን የጀመረው አዲሱ ሕግ ተሽከርካሪዎች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ መስበክን እና ቁሳቁሶችን መሸጥን መከላከል ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ይህም ተሳፋሪዎችን የሚረብሽ፣ ደኅንነት እና ምቾታቸውን የሚነሳ መሆኑን አስቀምጧል።
የ61 ዓመቱ የጎስፕል ላይት ቤተክርስቲያን ፓስተር የሆኑት ቦአቴንግ ከ2023 ጀምሮ ከኒዮፕላን መናኸሪያ በሚወጡ የንግድ ተሽከርካሪዎች ላይ ሲሰብኩ ቆይተዋል።
"እሁድ ዕለት ሁሉም ሰው ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ ስለማይችል በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ እሰብካለሁ። ከኃጢአታቸው ንስሐ በመግባት ነጻ እንዲወጡ የወንጌሉ መልዕክት የሚያስፈልጋቸው ብዙ ተሳፋሪዎች አሉ። በአንዳንድ አውቶቡሶች ላይ ሕሙማን ተፈውሰው ያውቃሉ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቦአቴንግ ካህን መሆናቸውን የሚያሳይ ልብስ ለብሰው ተሳፋሪዎችን በሚጭኑ አውቶቡሶች መካከል ይንቀሳቀሳሉ። ከዚያም ወደ ጋና ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ወደሆነችው ኩማሲ በሚጓዘው አውቶቡስ ላይ ይሳፈራሉ።
ቢቢሲ ሕጉን ላለመጣስ አውቶብሱ ከመነሳቱ በፊት አነጋገሯቸዋል።
አንዳንድ ተጓዦች መልዕክቱን ሲያስተላልፍ በቅርበት ያዳምጣሉ። ሌሎች ደግሞ ችላ በማለት፣ ስልኮቻቸውን በመነካካት ስልክ ለመደወል ወይም እርስ በርስ ለመጨዋወት ይሞክራሉ።
"አንዳንድ ተሳፋሪዎች በመልዕክቴ በጣም ተደስተዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ መልዕክቱን በቤተክርስቲያን ውስጥ ሰምተው እንደማያውቁ ይናገራሉ፤ ነገር ግን በስብከቴ አማካኝነት አሁን የምናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖሩን ያውቃሉ" ብለዋል።

አዲሱ ሕግ የሕዝብ አስተየየትን ለሁለት ከፍሏል።
ተቺዎች በተሽከርካሪዎች ላይ መስበክ አሽከርካሪውን ሊያዘናጋው ስለሚችል ችግር የሚፈጥር እና የደኅንነት ስጋት መሆኑን ይናገራሉ። ደጋፊዎቹ ደግሞ ወንጌልን መስበክ የአንድ ክርስቲያን ግዴታ እንደሆነ እና በአምልኮ ነፃነት ስር መታየት እንዳለበት ይከራከራሉ።
ቼሪ ሎኮ ተብላ እንድትጠራ የጠየቀችው በ30ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ አንዲት ሴት በሰላም መጓዝ እንደምትመርጥ ተናግራለች።
''ችግር የሚፈጥሩ ስለሆኑ አልወደውም። አንዳንዶቹ ሳያውቁት ምራቅ ይተፉብሃል፣ በተለይም ከእነሱ ብዙም ሳይርቅ ተቀምጠህ ከሆነ፣ እና በጫጫታ እና በምራቅ ረገድ ችግር ይፈጥራሉ። በሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ውስጥ ባለሁበት ጊዜ ሁሉ ሰላሜን እወዳለሁ።''
በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት በተሠራጨ አንድ ቪዲዮ ላይ፣ በሚኒባስ ውስጥ ያለ አንድ ተሳፋሪ በቁጣ አንድ ፓስተር እንዳይሳፈር ሲከላከል ታይቷል።
"ውረድ፣ ውረድ ብዬሃለሁ" እያለ ሲጮህ ተደምጧል።
ነገር ግን በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ሃይማኖተኞች ከሚገኙባቸው አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ጋና፣ በሕዝብ ማመላለሻ ወንጌልን መስበክ ቤተክርስቲያን የማይሄዱ ሰዎችን ለመድረስ አስፈላጊ መንገድ መሆኑን የሚያምኑ ሰዎች አሉ።
ወደ ኩማሲ የምትጓዘው በርኒስ ናርቴይ ፓስተሮች መስበክ ሊፈቀድላቸው ይገባል ትላለች፤ አክላም ይህ መሆን ያለበት በተሳፋሪዎች ፈቃድ ብቻ መሆኑን ትናገራለች።
"ስብከቱ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ይረዳል። ለምሳሌ፣ አንድ ሰው አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እያለፈ ከሆነ፣ የፓስተሩ መልዕክት ለግለሰቡ አዲስ ተስፋ ሊሰጠው ይችላል" ትላለች።
ቦአቴንግ በሕጉ እንደተደናገጡ እና የወንጌል ሰባኪዎች ነፃነት እንዲሰጣቸው እንደሚፈልግ ተናግሯል።
"በጣም ተጨንቀናል፤ ምክንያቱም እዚህ ያሉት አብዛኛዎቹ ፓስተሮች ተሳፋሪዎች በሚሰጧቸው የገንዘብ ስጦታ አማካኝነት ቤተሰቦቻቸውን ስለሚደጉሙ በወንጌል ሥርጭት አገልግሎቱ ላይ የተደገፉ ናቸው" ይላሉ።
"መንግሥት ከአክራ የሚወጡ አውቶቡሶች ላይ እንድንሰብክ ሊፈቅድልን ይገባል" ሲሉ አክለዋል።
ለቦአቴንግ፣ ስብከት የአገልግሎት ጥሪ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ የገቢ ምንጭም ነው።
"የልጆቼን ትምህርት መክፈል ችያለሁ። የመጨረሻ ልጄ ዩኒቨርሲቲ ጨርሷል፣ እና ግማሹ የገንዘብ ክፍያ የተገኘው በስብከት ካገኘሁት ገንዘብ ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጋና ሕገ መንግሥት የሃይማኖት ነፃነትን ቢያረጋግጥም እነዚህ መብቶች ግን የሕዝብ ደኅንነትን ከግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው።
በጋና በሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ላይ መስበክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከለከለው በአውሮፓውያኑ 2012 ሲሆን፣ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ግለሰቦች እስከ 30 ቀናት በሚደርስ እስራት ይቀጡ ነበር።
ነገር ግን ሕጉም በማስፈጸም ረገድ መንግሥት ክፍተቶች ስለነበሩበት በአውቶቡሶች ላይ መስበክ ቀጥሏል። አዲሱ ሕግ እገዳውን የሚጥሱ ሰዎችን ቅጣት ከፍ አድርጓል።
የድምጽ ማጉያ የሚጠቀሙ ሰባኪዎች በጋና የጭነት መኪናዎች መናኸሪያ፣ መናፈሻዎች እና ገበያዎች ውስጥ የሚሰብኩ ቢሆንም ሕጉ ግን አይመለከታቸውም።
የጋና የክርስቲያን ምክር ቤት ቢቢሲ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም፤ ነገር ግን በጋና ውስጥ ካሉት ትላልቅ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ በሆነው ኢንተርናሽናል ሴተራል ጎስፕል ቤተክርስቲያን ውስጥ አገልጋይ የሆኑት ቄስ ሄኖክ ፖል ሄይስ አዲሱ ሕግ የሃይማኖት ነፃነትን የሚጥስ እንዳልሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፓስተሮች ሕጉን እንዳይጥሱ በማሳሰብ መልዕክታቸውን ለማሠራጨት ሌሎች መንገዶችን መፈለግ እንዳለባቸው ተናግሯል።
"ተመሳሳይ መልዕክት በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሊደርስ የሚችልበት አማራጭ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ አለ" ብለዋል።
ለቦአቴንግ እና ለሌሎች በየመናኸሪያው ለሚሰብኩ ግን አዲሱ ሕግ የአገልግሎታቸውን መንገድ በመቀየር፣ አስፈላጊ የገቢ ምንጭን በመተው ወይም ሕግን በመጣስ መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ይጥላቸዋል።



































