እንቅልፋችንን ሳንጨርስ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ የምንነቃው ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እኩለ ሌሊት ላይ በድንገት ከእንቅልፍዎ ከነቁ በኋላ መልሰው ለመተኛት ተቸግረው ያውቃሉ?
ኢንተርኔት ላይ የሚገኙ መረጃዎች ሌሊት ከስምንት እስከ ዘጠኝ ባለው ሰዓት ውስጥ የምንነቃው በተለያዩ ምክንያቶች እንደሆነ ያስረዳሉ። ጭንቀት፣ ሆርሞኖች፣ መንፈሳዊ ምክንያቶች ወይም ከፍተኛ የጤና ስጋት ይጠቀሳሉ።
ይህ ጉዳይ ዋነኛ ውይይት ርዕስ ቢሆንም የእንቅፍል ባለሙያዎችን ግን ሌሊት ላይ መንቃት ያልተለመደ ነገር አለመሆኑን ያስረዳሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም የእንቅልፍ ፊዚዮሎጂስት የሆኑት ስቴፋኒ ሮሚሼቭስኪ፤ "የሚነገረን አንድ ወጥ የሆነ እንቅልፍ እንደሚያስፈልገን ነው። ነገር ግን በእንቅልፍ ሕክምና ውስጥ ሌሊት ላይ መንቃት እጅግ የተለመደ መሆኑን እናውቃለን" ይላሉ።
ሰዎች እንቅልፍ የሚወስዳቸው እየተደጋገመ በሚመጣ የ90 ደቂቃ ዑደት ነው። በእነዚሁ ዑደቶች ወቅት ቀላል ወይም ከባድ እንቅፍል ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።
እንቅልፍ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት፤ ጤናማ አዋቂ ሰዎች በአንድ ሌሊት ከሁለት እስከ አራት ጊዜ ይነቃሉ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ነቅተው የሚቆዩት ለተወሰኑ ሴኮንዶች ሲሆን፣ ብዙ ሰዎችም ነቅተው እንደነበር አያስታውሱም።
በሌሊቱ የመጀመሪያ አጋማሽ የሚኖረን እንቅልፍ ጥልቅ የሚባል ነው። ንጋት አካባቢ ላይ የሚኖር እንቅልፍ በአንጻሩ ቀለል ስለሚል ትንሽ እንቅስቃሴዎች ጭምር ሊቀሰቅሱን ይችላሉ።
ይህም በርካታ ሰዎች ወደ ንጋት በተጠጉ ሰዓታት ያጋጠማቸውን ከእንቅልፍ መንቃት ማስተዋል ይችላሉ ማለት ነው። ምክንያት በእነዚህ ሰዓታት የሚኖረው እንቅልፍ ቀላል የሚባለው ዓይነት ነው።
በሕንድ ሙምባይ በሚገኘው 'ኧርቪ ማይንድ ክሊኒክ' ሳይካትሪትስት የሆኑት ዶ/ር ሪሻብ ቨርማ፤ "ሰዎች በመደበኛነት ከምሽቱ 4 ወይም 5 ሰዓት አካባቢ የሚተኙ ከሆነ፣ ከሌሊቱ 8 እስከ 9 ሰዓት ያለውን ጊዜ ለሰውነታቸው ወሳኝ ነጥብ ይሆናል። አብዛኛው ጥልቅ የሚባለው እንቅልፍ በዚህ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል" ሲሉ ያብራራሉ።
ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ችግሩ የሚጀምረው፤ አንድ ሰው ሙሉ በሙሉ ሲነቃ እና አእምሮው እንቅልፍ እየወሰደው እንዳልሆነ ማሰብ ሲጀምር ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንዳንድ ሰዎች ለምን በድጋሚ መተኛት አይችሉም?
ወደ ንጋት በሚጠጉት የሌሊቱ ሰዓታት ሰውነት ቀስ በቀስ ለቀጣዩ ቀን መዘጋጀት ይጀምራል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ንቁ ለመሆን የሚረዳው 'ኮርቲሶል' የተባለው ሆርሞን እየጨመረ ይመጣል።
በመደበኛ ሁኔታ ውስጥ ይህንን ሁኔታ አናስተውለውም። አእምሮ መንቃትን ከክስተት ጋር አያይዞ በሚያይበት ጊዜ ግን ኮርቲሶል እንዲጨምር ምክንያት ይሆናል፤ ይህም በድጋሚ መተኛትን ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
የእንቅልፍ ፊዚዮሎጂስቷ ሮሚሼቭስኪ "መንቃትን እንደተገነዘብክ ወዲያውኑ የሚጀምር ሂደት አለ። በድንገት መንቃትን አዎንታዊ ካልሆነ ነገር ጋር ማያያዝ ትጀምራለህ። ለዚያም መልሰህ ለመተኛት ግፊት ያጋጥምሃል" ይላሉ።
"ለመተኛት ብዙ ግፊት ባሳደርክ ቁጥር፣ ይበልጥ ንቃትን ትጨምራለህ፤ ይህም እንቅልፍን ይበልጥ የማራቅ ዕድል አለው" ሲሉም ያክላሉ።
ይሁን እንጂ፣ አንድ ሰው ቋሚ በሆነ ውጥረት እና ጭንቀት የተሞላበት ሕይወት የሚገፋ ከሆነ፣ ቀድሞውኑ ሰውነቱ ውስጥ ያለው የኮርቲሶል መጠን ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ተፈጥሯዊ መሆን የነበረበት ከእንቅፍ የመንቃት ዑደት እንደ "ማስጠንቀቂያ" ምልክት ሊታይ እና እንቅልፍን ሊያስተጓጉል ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብዙ ሰዎች በንጋት ሰዓት ላይ የሚኖሯቸው ሀሳቦች ውል ያላቸው አለመሆናቸውም ሌላኛው ችግር ነው።
የቀላል እንቅልፍ ዑደት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ስሜታዊነትን የሚቆጣጠረው የአዕምሮ ክፍል ይበልጥ ንቁ ይሆናል። በአንጻሩ ከፍተኛ ምክንያታዊነት ያለው እና ችግርን መፍታት የሚችለው ክፍል ደግሞ የንቁነት መጠኑ እንደሚቀንስ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በእንቅልፍ ወቅት የትንፋሽ መቋረጥን እንደሚያመጣው 'ስሊፕ አፕኒያ'፣ እግር የመንቀጥቀጥ ህመም እንዲሁም ታይሮይድ የመሳሰሉ የጤና እክሎችም በድጋሚ መተኛትን አስቸጋሪ ሊያደርጉት ይችላሉ።
የኑሮ ዘይቤያችንም ችግሩን ሊያባብስ ይችላል። ምሽት ላይ በከባዱ መመገብ ወይም ከግማሽ ቀን በኋላ ከመጠን ያለፈ ስኳር እና ካፌን መጠቀምም ሰውነት እንቅልፍን ለማምጣት የሚለቅቃቸውን ምልክቶች ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ።
አልኮል መጠጣትም ራሱን የቻለ ችግር ነው።
ኒውሮሎጂስቱ ዶ/ር ፕራሻንት ማክሂጃ "አልኮል በፍጥነት እንቅልፍ እንዲወስደን ሊያደርግ ይችላል። በሚቀጥሉት ሦስት እና አራት ሰዓታት ጉበት ሥራውን ሲጀምር ግን እንደ አነቃቂ መሆን ይጀምራል። በተለይም ቀለል ወዳለው የንጋት እንቅልፍ መሻገር በሚኖርብን ጊዜ እንቅልፍን ያቋርጣል" በማለት ያስረዳሉ።
ይህ ችግር ለምን ሴቶች ላይ ይበረታል?
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ቁጥር ሌሊት ላይ ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ።
ምንም እንኳ ሴቶች ከወንዶች በመጠኑ የሚበልጥ የእንቅልፍ ጊዜ ቢኖራቸውም፤ በእንቅልፍ መታወክ የመቸገር ዕድላቸው እንደሚጨምር ጥናቶች አሳይተዋል።
ከወር አበባ ጋር የተያያዘ የሆርሞን ለውጥ፣ እርግዝና እንዲሁም ማረጥ የዚህ ምክንያት ሆነው ይጠቀሳሉ።
ይሁን እንጂ ብዙም ትኩረት የማይሰጠው ሴቶች ላይ የሚደርስ ማኅበራዊ ጫና በራሱ እንቅልፋቸውን ሊያውክ እንደሚችል የእንቅልፍ ፊዚዮሎጂስቷ ሮሚሼቭስኪ ይናገራሉ።
"በአሁኑ ጊዜ የቤተሰባቸው ብቸኛ የገቢ ምንጭ የሆኑ ሴቶች አሉን። እንዲያም ሆኖ አሁንም ወላጅ፣ አሁንም ዋና ተንከባቢ ናቸው…አሁንም እነዚህን የማይታዩ ከባድ ሸክሞችን ለመቋቋም እየሞከሩ ነው" ብለዋል።
በሌላ በኩል በርካታ ሴቶች ሥራ እና የመንከባከብ ኃላፊነቶቸቻውን ከተወጡ በኋላ ለማረፍ እንዲሁም ለመዝናናት ዕድል የሚያገኙበት ብቸኛው አጋጣሚ እንቅልፍ ስለሆነ ወደ መኝታ መሄድን እንደሚያዘገዩትም ባለሙያዋ ያክላሉ።
"ሴቶች የምጠይቃቸውን ነገሮች ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ የሌላቸው መሆኑ የእንቅልፍ ሕክምና ውስጥ እንዳለ ባለሙያ የሚያጋጥመኝ ችግር ነው" በማለት ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወደ እንቅልፍ መመለስ
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ ጭራሹኑ ከእንቅፍል አለመንቃትን ግብ ማድረግ የለብንም። ነገር ግን ከእንቅልፍ የምንነቃበት ጊዜ የማይታወስ እንዲሆን እንዲሁም በተፈጥሮ ወደ እንቅልፍ መመለስ እንዲቀልለን ለማድረግ ጤናማ የእንቅልፍ ልምዶችን ማጠናከር ይኖርብናል።
ከመኝታ ሰዓት ልምዶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ከጠዋት የሚጀምር ጤናማ ልምድ መገንባት አስፈላጊ መሆኑንም ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በየዕለቱ የምንነሳበት ቋሚ ሰዓት ማበጀት፣ እንደነቁ ወዲያውኑ ራስን ለብርሃን ማጋለጥ እንዲሁም አካልን ማንቀሳቀስ የሰውነትን ውስጣዊ ሰዓት ለማስተካከል እና በምሽት ጠንካራ የእንቅልፍ ፍላጎት እንዲኖር ለማድረግ ይረዳል።
ሲደክምዎት እና እንቅልፍዎ ሲመጣ ብቻ ወደ አልጋ መሄድም የሚመከር ልምድ ነው።
ሮሚሼቭስኪ "የመተኛት ሰዓትን በራስ ሲወስኑ እና እንቅልፍ ሳይመጣ ወደ አልጋ በሚሄዱበት ሰዓት አእምሮ የተረጋጋ እንዲሆን ይጠብቃሉ። አእምሮ የሚያደርገው ግን ተቃራኒውን ነው። እንቅልፍ ስላልመጣ እና ወደ ሰውነት የገቡ አንቂ ነገሮች ስላልጠፉ መነቃቃት ይጀምራል" ሲሉ ያብራራሉ።
ሌሊት ላይ ከእንቅልፍ ሲነቁ ትኩረትዎን ሰዓቱ ላይ ማድረግ እንዲሁም ስልክዎን መነካካት ምን ያህል እንቅልፍ እንደቀሚቀርዎት እንዲሚያስቡ ስለሚያደርግ የአእምሮ ጨንቀት ይጨምራል።
ለ20 ደቂቃ ያህል ከነቁ ወደ ሌላ የቤትዎ ክፍል መሄድ እና በደብዛዛ ብርሃን ውስጥ የሆነ ነገር ማድረግ ወደ እንቅልፍ ለመመስ ሊረዳ ይችላል። ወደ አልጋ መመለስ ያለብዎ በድጋሚ እንቅልፍዎ ሲመጣ ብቻ ነው።
በተደጋጋሚ ሌሊት ላይ የሚነቁ፣ መልሰው ሳይተኙ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ከሆነ ወይም ስሜትዎ፣ ሥራዎ ወይም የዕለት ተዕለት ኑሮዎት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ከሆነ ወደ ባለሙያ መሄድ ሊኖርብዎት ይችላል።
ሰዎች መቀየር የሚችሉት ትልቁ ጉዳይ፤ እንቅልፍ ፍጹም እንዲሆን አለመጠበቅ ነው። ይልቁን ከሁኔታው ጋር እንዲላመድ ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ሮሚሼቭስኪ "ፍጹም ለማድረግ መሞከር ስንታመም፣ የሰዓት ለውጥ ሲኖር፣ በእርግዝና፣ በማረጥ ጊዜ እና የሆርሞን ለውጦች ሲኖሩ ማድረግ ያለበትን እንዳይሠራ እያስቆምነው ነው" ይላሉ።



































