ኢትዮጵያ አዲስ ከገነባችው የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ ምን ያህል ታተርፋለች?

ፋብሪካው በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም እንዳለው ተገልጿል
የምስሉ መግለጫ, ፋብሪካው በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም እንዳለው ተገልጿል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በአዲስ አበባ፣ ቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም እንዳለው ተገልጿል።

ፋብሪካው ኢትዮጵያን "በውድ ማዕድናት ማጣሪያ ረገድ ቀጣናዊ ማዕከል ለማድረግ" እንደሚያስችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ዱባይ በሚገኘው ሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ ስምምነት የተገነባው ይህ የወርቅ ማጣሪያ "ከአፍሪካ አንደኛው ነው" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከቢቢሲ ኒውስ ዴይ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ፋብሪካው አሁን ላይ ባለው አጠቃላይ አቅም "በዓመት 600 ቶን ወርቅ" ማጣራት ይችላል።

በትርፍ ረገድም፤ "በዛሬ [መስከረም 3/ 2019 ዓ. ም.] የገበያ ዋጋ በ4,160 ዶላር ብናሰላው ፋብሪካው 100% ሙሉ አቅሙን ሲጠቀም በዓመት እስከ 80 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል" ሲሉ ገልጸዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገራት የምትልከው 5.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወርቅ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስከረም 30/2019 ዓ. ም. ፋብሪካው ሥራ መጀመሩን ይፋ ሲያደርጉም አምና 5.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወርቅ ወደ ውጭ መላኩን ጠቅሰው "ይህ የማጣራት አቅም ከዚያ በፊት ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ቢያንስ 10 ቢሊዮን ሊሆን ይችላል" ሲሉ አስረድተዋል።

ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)
የምስሉ መግለጫ, ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)

ዶ/ር ብሩክ እንደገለጹት፤ የሚገኘው አጠቃላይ ገቢ የሚወሰነው በኢትዮጵያ ባለው ፍላጎት ብቻ ሳይሆን "ወርቃቸው በኢትዮጵያ እንዲጣራ የሚልኩት" አገራትንም ታሳቢ ይደረጋሉ።

ሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ ኩባንያ 49 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ 51 በመቶ ትርፍ ያገኛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ወርቅ በማጣራት "እሴት የተጨመረበት ምርት ወደ ገበያው ማስገባት" ተቋሙ የሚገኘው ጥቅም አካል እንደሆነ ዶ/ር ብሩክ ተናግረዋል።

የሚገኘው ገንዘብ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንደሚገባ እና ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ መድኃኒት እና ሌሎችም አስፈላጊ ግብዓቶችን ለመግዛት እንደሚውል አክለዋል።

"ብሔራዊ ባንክ ከወርቅ ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ በውጭ ምንዛሪ ገበያ ያቀርበዋል። አሁን ላይ 140 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጨረታ ለግል ባንኮች ቀርቧል። ይህም ከወርቅ ኤክስፖርት የተገኘ ነው" ሲሉም አስረድተዋል።

የአፍሪካ መንግሥታት የአህጉሪቱን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በአገር በቀል ጥቅም ላይ ለማዋል የወርቅ እና የሌሎችም የከበሩ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካዎች መክፈትን አማራጭ አድርገዋል።

ማዕድናትን በአገር ውስጥ በማጣራት ተጠቃሽ ከሆኑ የአፍሪካ አገራት መካከል ጋና አንዷ ስትሆን፤ አምስት ወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካዎች አሏት።

ሌላዋ ወርቅ በማጣራት የምትታወቀው ዛምቢያ አራት ፋብሪካዎች፣ ኡጋንዳ ደግሞ ሦስት ፋብሪካዎች ገንብተዋል።

በቅርቡ ቡርኪና ፋሶ የአገሪቱን የመጀመሪያ የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ አስገንብታለች። በማዕድናት የበለጸጉ የአፍሪካ አገራት ወርቅን አጣርቶ በመላክ የተሻለ የገበያ ዋጋ ያገኛሉ።

50 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት የኢትዮጵያው ፋብሪካ በአገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት ለመጨመር እንዲሁም የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ፣ ቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ
የምስሉ መግለጫ, በአዲስ አበባ፣ ቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባው የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ሥራ አስጀምረዋል
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

‎ኢትዮጵያ የገነባችው ፋብሪካው ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ የማሳደግ፣ የሥራ ዕድል የመፍጠር እንዲሁም የወርቅ እሴትን ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

አንድ ኪሎ ወርቅ ከኢትዮጵያ ሲላክ "እንደ ወርቅ አይወሰድም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ መጀመርያ ማጣራት ተደርጎ ከዚያ ውስጥ "ቢበዛ 70 በመቶው" ወርቅ እንደሚባል ተናግረዋል።

"እንደ ቆሻሻ የሚደፋው" 30 በመቶው "ብር ሊሆን ይችላል" ሲሉን የሚኖረውን ጥቅም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ አቅም ያለው የወርቅ ማጣሪያ እንደገነባች የተናገሩት ዐቢይ፤ ከብዙ የአፍሪካ አገራት "ማዕድናት እየመጡ ሊጣራ ይቸላል" ብለዋል።

ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባውን የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ጨምሮ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት የሚያደርጋቸው ኢንቨስትመንቶች የአገሪቱን የኤክስፖርት አቅም እንደሚያሳድጉ ዶ/ር ብሩክ ቢቢሲ ኒውስ ዴይ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

የወርቅ ማጣሪያው ፋብሪካ በይፋ ሥራ ሲጀምር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግርም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ "ጥሬ እየላኩ የበሰለ ማስገባት የምታቋርጥበት ዘመን ይሆናል" ሲሉም ገልጸዋል።

ይህ "የወጪ ንግዳችን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተጽዕኖ ይኖረዋል. . . በወርቅ ላይም ከእጥፍ ያላነሰ የዋጋ ጭማሪ" ይኖራል ሲሉ አክለዋል።

የመንግሥት ኢንቨስትመንቶች የግሉን ዘርፍ የሚሸፍኑ አይሆኑም ወይ? የሚል ጥያቄ ከቢቢሲ የቀረበላቸው ዶ/ር ብሩክ "የግሉን ዘርፍ የሚሸፍን አይደለም፤ ገበያ እየፈጠርን ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

"መንግሥት ገበያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ብቻ መፍታት አለበት ብለን አናምንም። ስህተቶችንም ማረም አንድ ነው፤ የግሉ ዘርፍ ባልገባበት መስክ ገበያ መፍጠር ሌላው ነው" በማለትም ተናግረዋል።

ኢንቨስትመንቱ በቀጥታ "የውጭ ኢንቨስተሮችን የሚያመጣ" እንደሆነም አክለዋል።

"አብዛኞቹ ኢንቨስትመንቶቻችን ከአገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ናቸው። ስለዚህ የግሉን ዘርፍ እየሸፈንን ነው ብለን አናምንም። እንዲያውም ገበያውን እያሰፋን ነው" ብለዋል።

አሁን ላይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ጦርነት በማንሳት ባለ ሃብቶች ምን ያህል በኢትዮጵያ ላይ መተማመን ይችላሉ? የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸዋል።

ዶ/ር ብሩክ ሲመልሱ "ይህንን በትልቁ አውድ ውስጥ መመልከት ያስፈልጋል። በአንድ አህጉር ወይም በየትኛውም የዓለም ክፍል ኢንቨስት ሲደረግ የሚታየው ከምን አንጻር ነው? ኢትዮጵያ ደኅንነቷ የተጠበቀ የሚሆነው ከምን አንጻር ነው? ኢትዮጵያ ደኅንነቷ የተጠበቀ የማይሆነው ከምን አንጻር ነው?" ብለዋል።

በዓለም አቀፍ አውድ "ደኅንነቱ የተጠበቀ" የሚለው አገላለጽ "አንጻራዊ" እንደሆነ ጠቅሰው "የራሳችን ጉዳዮች አሉብን፤ ኢንቨስትመንት እና ኢንቨስተሮችን በመጠበቅ ግን የላቅን ሆነን ተገኝተናል" ሲሉ ተናግረዋል።

ኢንቨስተሮች አሁን ላይ ያለውን ሳይሆን በቀጣይ አምስት እና አሥር ዓመታት የሚፈጠረውን እንደሚመለከቱ የጠቀሱት ዶ/ር ብሩክ "በኢትዮጵያ ሙሉ እምነት አሳድረው ነው ገንዘባቸውን ኢንቨስት የሚያደርጉት፤ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብዬ አምናለሁ" በማለትም አስረድተዋል።