የሳዑዲ ዜጋ በ'ኦፕን ኤአይ' ቢሮ ዘመናዊ የድምፅ ቅጂ መሣሪያ በመግጠም ተከሰሰ

አቃቢ ሕግ ተጠርጣሪው ሚስጢራዊ መሣሪያውን ሲከታተል የሚያሳይ ምሥል አጋርቷል
የምስሉ መግለጫ, አቃቢ ሕግ ተጠርጣሪው ሚስጢራዊ መሣሪያውን ሲከታተል የሚያሳይ ምሥል አጋርቷል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሳዑዲ አረቢያ ዜግነት ያለው ግለሰብ በካሊፎርኒያ በሚገኘው የ'ኦፕን ኤአይ' ቢሮ ሚስጢራዊ የድምፅ ቅጂ መሣሪያ በመግጠም መከሰሱን የፌደራል አቃቢ ሕግ አስታወቀ።

አብዱልራህማን አልፎዛን የተባለው ግለሰብ በድርጅቱ መሀንዲስ ሠራተኛ ሲሆን፤ የድምፅ ልውውጦችን በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ለመጥለፍ እና ለመጥለፍ በመሞከር የፌደራል ክስ ተመስርቶበታል።

'ኦፕን ኤአይ' በሳን ፍራንሲስኮ ቢሮው "እጅግ ዘመናዊ የድምፅ መቅጃ መሣሪያ" ተደብቆ ማግኘቱን እና ለአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ማሳወቁን አስታውቋል።

ኩባንያው የኤአይ ሞዴሎቹን ተጠቅሞ ባደረገው ማጣራት መሣሪያውን ሠራተኛው መደበቁን ገልጿል።

አቃቢያነ ሕግ መሣሪያው በመፀዳጃ ወረቀት በሥራ አስፈፃሚዎች የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሚገኝ ቴሌቪዥን ውስጥ ተሰክቶ መገኘቱን ተናግረዋል።

የታዋቂው የኤአይ መረጃ መጠየቂያ 'ቻትጅፒቲ" ሰሪ የሆነው 'ኦፕን ኤአይ' በድርጊቱ መረጃዎች እንደተወሰዱ አሊያም እንደተመነተፉ የሚያመላክት ነገር የለም ብሏል።

መሣሪያውን ደብቋል የተባለውን ሠራተኛ ማባረሩንም ገልጿል።

በቀረበው አቤቱታ አልፎዛን በሥራ አስፈፃሚዎች አዳራሽ የድምፅ መቅጃ መሣሪያውን የደበቀው ሚስጢራዊ ንግግሮችን ለማግኘት አስቦ እንደሆነ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ካሽ ፕቴል ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ የተጠርጣሪው ግብ ስለ ኩባንያው የኤአይ ምርት መረጃ ለማግኘት ነው ብለዋል።

አልፎዛን በኦፕን ኤአይ መሃንዲስ በመሆን እ.አ.አ ከሐምሌ 2025 ጀምሮ እየሰራ አንደነበር አቃቢ ሕግ ገልጿል።

የድምፅ መቅጃው ከሣምንታት በፊት በኩባንያው ሠራተኞች መሣሪያው በተገጠመ በሁለት ቀኑ እንደተገኘም አክሎ ተናግሯል።

መሣሪያው በቀላሉ እንዳይከፈት የተቆለፈበት እንደሆነም ተነግሯል።

ኩባንያው የኤአይ ሞዴሎችን በመጠቀም መሣሪያውን ለመረዳት እና ከየት እንደመጣ ለማወቅ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

እንደ ኤፍቢአይ ከሆነ ሠራተኛው በኩባንያው ሚስጢራዊ ቦታዎችን ለመለየት እና የድምፅ መቅጃውን ሚስጢራዊ ስፍራ ላይ ለመደበቅ የኤአይ መሳሪያዎችን ተጠቅሟል።

ተጠርጣሪው ማክሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርቧል። ጠበቃ ይኑረው አይኑረው እስካሁን ግልፅ አይደለም።

አብዱልራህማን አልፎዛን ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ አምስት ዓመት እስር እና 250 ሺ ዶላር ቅጣት ይጠብቀዋል።