የእነ ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ምክር ቤት ከአሁን በኋላ "በተቋቋመበት አደረጃጀት" እንደማይቀጥል አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, amn
በእነ ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ የሚመራው እና በትግራይ ክልል የሽግግር ሂደቶችን ለማመቻቸት ሲንቀሳቀስ የነበረው "የትግራይ ሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት" ከአሁን በኋላ "በተቋቋመበት አደረጃጀት" እንደማይቀጥል አስታወቀ።
ምክር ቤቱ የማይቀጥለው፣ ፌደራል መንግሥት በክልሉ ቀጣይ የሽግግር ተግባራትን የማከናወን ተግባርን "ራሱ ሊይዘው በመወሰኑ" እንደሆነ የምክር ቤቱ የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ከበደ አሰፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ፣ አሁን በትግራይ ክልል የሚታየው "ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድል" እንዲገኝ የበኩሉን መወጣቱን ዛሬ አርብ ጥቅምት 6/2019 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስገንዝቧል።
ግንቦት 2018 ዓ.ም. የተመሠረተው ይህ ምክር ቤት ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተለዩ እና የተቃረኑ ፖለቲከኞች እንዲሁም የትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የያዘ ነበር። የምክት ቤቱ አባል ከሆኑት ስምንት ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ (ስምረት) ከምክር ቤቱ አባላት አንዱ ነው።
ከህወሓት በተለዩ አመራሮች የተመሠረተው ሌላኛው ፓርቲ ወለዶ ትግራይ እንዲሁም አረና ትግራይ ለዴሞክራሲ እና ሉዓላዊነት (አረና) እና ትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲዎችም ይጠቀሳሉ።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ "ከአስር በላይ የሲቪል ማኅበራት፣ የሚዲያ አካላት እና የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተደራዳሪ ግለሰቦችም" የምክር ቤቱ አባል እንደነበሩ መግለጫው ያስረዳል።
በምክር ቤቱ ሥር የተቋቋሙ ኮሚቴዎችን የሚመሩት ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ናቸው።
ይህ ሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት እስካሁን ሲንቀሳቀስበት በነበረው አደረጃጀት እንደማይቀጥል ያሳወቀው፣ የፌደራል መንግሥት ዛሬ አርብ ጥቅምት 6/2019 ዓ.ም. ትግራይ ክልልን ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚመራ ባለአደራ አስተዳደር ማቋቋሙን ካስታወቀ ከሰዓታት በኋላ ነው።
"በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስከሚቋቋም ድረስ" የሚቆየውን ይህ ባላአደራ አስተዳደር አራት ዋና አስፈጻሚዎች የተሾሙለት ሲሆን ለመቀለ ከተማ ከንቲባም ተሰይሟል።
የሰላም እና ለውጥ ምክር ቤቱ በዛሬው መግለጫው፣ "በተሠራው የተቀናጀ ሥራ፤ ወንጀለኛው የፖለቲካ እና ወታደራዊ ኃይል ከሥልጣን ተወግዶ" በፌደራል መንግሥት የባለ አደራ አስተደዳር ሹመት መሰጠቱን ጠቅሷል።
ምክር ቤቱን "ትግራይ ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን በኃይል ተቆጣጥሮ የነበረውን የወንጀለኞች ስብስብ በማጋለጥ፤ አሁን የተገኘው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድል እንዲገኝ የበኩላችንን ተወጥተናል" ብሏል።
በክልሉ "የሰላም፣ መረጋጋት እና ሽግግር ወቅቱ የተሳካ ይሆን ዘንድ በተናጠል እና በተደራጀ መንገድ" ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጸው ምክር ቤቱ የነበረበት አደረጃጀት ግን እንደማይቀጥል አስታውቋል።
ምክር ቤቱ እንደማይቀጥል ያወጀው፣ ፌደራል መንግሥት በክልሉ ቀጣይ የሽግግር ተግባራትን የማከናወን ተግባርን "ራሱን ሊዘይዘው በመወሰኑ" እንደሆነ የምክር ቤቱ የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ከበደ አሰፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪው "የሰላም እና የማረጋጋት እንዲሁም ጊዜያዊ አስተዳደር የማቋቋም ስራውን ፌደራል መንግሥት ራሱን ሊዘይዘው በመወሰኑ ምክንያት የዚህ ጊዜያዊ ስብስብ ቀጣይነት አላስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ማብቃቱን ማወጅ [አስፈልጓል]" ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በቀጣይ በፌደራል መንግሥቱ የሚከናወኑ ተግባራትን "በየአደረጃጀታቸው በጋራም በተናጥልም እንደሚደግፌ" ከበደ አስረድተዋል።
ይህ አቋም በምክር ቤቱ መግለጫ ላይም ተጠቅሷል። መግለጫው "በተቋቋመበት አደረጃጀት የማይቀጥል ሲሆን" አባላቱም "የቆሙለት ዓላማና የራሳቸውን አሰራር ተጠቅመው ፤ የሃገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ፤ ስራቸውን በየራሳቸው መንገድ የሚቀጥሉ ይሆናል" ሲል ቀጣይ እርምጃቸውን ምን እንደሚሆን አስረድቷል።
ትግራይ ክልል ከመስከረም አጋማሽ አንስቶ በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው።
ከትግራይ ኃይሎች በወጡት ወታደራዊ አዛዦች የሚመራው የትግራይ ሠላም ኃይል ከፌደራል መንግሥት ጎን ተሰልፏል።
በእስካሁኑ ውጊያ መዲናዋ መቀለን ጨምሮ የተለያዩ የክልሉ ዋና ከተማዎች በፌደራል መንግሥት እና አጋሮቹ ቁጥጥር ስር ሆነዋል።



































