በጋምቤላ ከተማ የሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ጥቃት እና ሁከት

ጋምቤላ ከተማ የሚገኝ ሃውልት የቆመበት እና በዙሪያው የውሃ ፋውንቴን ያለው አደባባይ
የምስሉ መግለጫ, ጋምቤላ ከተማ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በጋምቤላ ከተማ ባለፉት ጥቂት ቀናት በተፈፀሙ ጥቃቶች የሰዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጮች ተናገሩ።

በተደጋጋሚ ግጭቶች እና ጥቃቶችን ያስተናገደችው የጋምቤላ ከተማ ረቡዕ ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም. ከፍተኛ ሁከት እና አለመረጋጋት ሰፍኖባት እንዳሳለፈች እና ዛሬም የተኩስ ድምጾች መሰማታቸውን ሦስት የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለተፈጠረው ሁከት መንስዔ የሆነው ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ሌሊት በተለምዶ አዲስ ሰፈር በመባል በሚታወቀው የከተማው 04 ቀበሌ በተፈፀመ ጥቃት አራት ሲቪሎች መገደላቸው መሆኑን ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪዎች ገልፀዋል።

የማክሰኞውን የአራት ሰዎች ግድያ ተከትሎ በተፈፀመው ሁከት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን የሆስፒታል ምንጮች ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከክልሉ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

የጋምቤላ ፖሊስ ረቡዕ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ፣ በክልሉ ዋና ከተማ በሌሊት ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት በተፈፀመ ጥቃት የሰው ሕይወት ማለፉን አስታውቋል።

የክልሉ ፖሊስ የከተማዋን ጸጥታ ለማስጠበቅ እና ዜገችን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ገልጾ "ላልተወሰነ ጊዜ" ከምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ የሚቆይ የሰዓት እላፊ አውጇል።

አክሎም በጋምቤላ ከተማ የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ "በጥብቅ" መከልከሉንም አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ማክሰኞ ሌሊት ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት ከተገደሉት አራቱ ሰዎች ውስጥ ሦስቱ ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ አንዷ ደግሞ ጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል ከደረሰች በኋላ በማግስቱ ሞታለች።

ከሟቾቹ ውስጥ ሦስቱ ሴቶች ሲሆኑ አንዱ ወንድ እንደሆነ አንድ የሆስፒታሉ አመራር አባል ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ዕድሜያቸው በግምት ከ30 እስከ 35 የሚሆኑት "ሦስቱ ሞተው ነው የደረሱት" ያሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የሆስፒታሉ ምንጫችን፣ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት የነበረችው የ16 ዓመት ታዳጊ በቀጣዩ ቀን "ረፋድ 5 ሰዓት ከ30 አካባቢ ሕይወቷ አልፏል" ብለዋል።

ሁሉም በጥይት ተመትተው መገደላቸውን የሚናገሩት የሆስፒታሉ አመራር "ቤተሰብ መሆናቸውን ባላውቅም ጥቃቱ የተፈፀመባቸው አንድ ቤት ውስጥ እንዳሉ መሆኑ ነው የተነገረን" ሲሉ አክለዋል።

ካነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች አንዱ፣ ታጣቂዎቹ "ቡና እየጠጡ ያሉ ሰዎችን ነው ማታ ገብተው ገድለው የሄዱት" ብለዋል።

ከማክሰኞው ግድያ በፊትም ሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች አልፎ አልፎ የተለመዱ መሆናቸውን የተናገሩት አስተያየት ሰጪው፣ ከሦስት ቀናት በፊት 2 ሰዎች ተገድለው እንደነበር አስታውሰዋል።

ሁለቱ ሟቾች ባልና ሚስት እንደሆኑ እና ታጣቂዎቹ ሱቃቸውን አስከፍተዋቸው በጥይት ገድለዋቸው እንደሄዱ ተናግረዋል።

'የታጠቀው ከታጠቀ ጋር አይደለም እየገጠመ ያለው። ምንም የማያውቀው ምስኪኑ ነው ዋጋ እየከፈለ ያለው።"

ታጣቂዎቹን ሲገልጿቸው "ጫካ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው፤ ድንገት ወደ ከተማው እየገቡ ጥቃት እየፈፀሙ ይወጣሉ" ያሉት ግለሰቡ፣ "ሰው ሞተ ሲባል ብቻ ነው የምንሰማው" ሲሉ ሁኔታውን ይገልፃሉ። የታጣቂዎቹ ፍላጎት ምን እንደሆነ እንደማያውቁ የተናገሩት እኚሁ አስተያየት ሰጭ፣ የጥቃቱ ዒላማዎች በተለምዶ "ሐበሻ" በመባል የሚታወቁ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሄደው ኑሮአቸውን ጋምቤላ ያደረጉ ነዋሪዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በየጊዜው ይፈፀማሉ ባሏቸው ጥቃቶች ከሞት በተጨማሪ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም መኖራቸውን ገልፀዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ደግሞ፣ አልፎ አልፎ "ሌሊት ሌሊት ሰው እየተገደለ ይገኛል" ያሉ ሲሆን ገዳዮቹ ማንነታቸው እንደማይታወቅ ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት፣ በታጣቂዎች የሚፈፀሙ ግድያዎች የተለመዱ ሲሆን፣ ማክሰኞ ዕለት የተፈፀመው የአራት ሲቪሎች ግድያ ግን በትናንትናው ዕለት በጋምቤላ ከተማ የሌሎች ሰዎችን ሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ያስከተለ ሁከት እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።

ሁከቱ የተቀሰቀሰው የሟቾችን አስከሬን ይዘው እና አጅበው የሚመለሱ ሰዎች፣ ቁጣቸውን ለመግለፅ "ድንጋይ በመወርመር" የጀመሩት እንቅስቃሴ አገርሽቶ ወደተለያዩ እርምጃዎች ከተቀየረ በኋላ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትናንት ረቡዕ ከጠዋቱ 3 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ በነበረው ሁከት የተገደሉ ሦስት ሰዎችን ሆስፒታል ሄደው መመልከታቸውን ካነገርናቸው መካከል የሆኑት አንዲት የከተማዋ ነዋሪ ገልፀዋል።

በስልክ ስናናግራቸው እዚያው ሆስፒታል እንደነበሩ የነገሩን አስተያየት ሰጪዋ፣ ከሟቾቹ ሁለቱ የክልሉን ፖሊስ መለዮ የለበሱ የፀጥታ አባላት ሲሆኑ አንዱ ሲቪል መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም አንዲት አዛውንት ቤታቸው እንዳሉ የሁከቱ ተሳታፊ በሆኑ ሰዎች መገደላቸውን እና አንድ ሌላ ግለሰብም መገደሉን ስለማረጋገጣቸው የተናገሩት አስተያየት ሰጪዋ፣ አምስት ሰዎች የሁከቱ ሰለባ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የሆስፒታል ምንጮች በትናንቱ ሁከት የተገደሉ አምስት ሰዎች ወደ ሆስፒታል መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

ከአምስቱ ሟቾች አራቱ ጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል ሞተው የደረሱ መሆናቸውን የተናገሩት የሆስፒታሉ ምንጭ፣ ከእነዚህም አንዷ የ60 ዓመት አዛውንት መሆናቸውን እና ሕይወታቸው ያለፈው በስለት በተፈፀመባቸው ጥቃት እንደሆነ ተናግረዋል። ሌሎቹ በጥይት የተገደሉ እንደሆኑም የተናገሩ ሲሆን፣ ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተከታተሉ ያሉ መኖራቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።

አንዱ ሟች ደግሞ ጋምቤላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ፓል ኪር ተናግረዋል። በተጨማሪም ሦስት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ሆስፒታሉ ገብተው ሕክምና ሲከታተሉ እንደነበሩ ጠቅሰው ከመካከላቸው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት አንድ ታካሚ ለተሻለ ሕክምና ወደ ጅማ ሆስፒታል መላኩን ገልፀዋል።

የማክሰኞው ጥቃት በተፈፀመበት አዲስ ሰፈር ውስጥ ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 5/2019 ዓ.ም ጠዋት ላይም የተኩስ ድምጾች ይሰሙ እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎች አመልክተዋል።

በከተማዋ በነበረው ሁከት አምስት በሚሆኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም የግለሰቦች ቤትና ንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ከትናንት ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ከተማዋ የገቡ ሲሆን፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ሁኔታውን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት የቢቢሲ ምንጮች፣ ምንም እንኳን አንጻራዊ መረጋጋት ቢኖርም በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የሰዎች እንቅስቃሴ እንደሌለ መታዘባቸውን ገልፀዋል።

በከተማዋ ያሉ የንግድ እና ሌሎች ተቋማት ዝግ እንደሆኑም ምንጮቻችን አክለው ተናግረዋል።

ቢቢሲ ስለጥቃቱ እና በከተማዋ ስላለው ሁኔታ ከመንግሥት አካላት መረጃ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡጁሉ ኡዶል በተደጋጋሚ ደውለንላቸው አልመለሱም። በፅሁፍ ላቀረብንላቸው ጥያቄም ምላሽ አልሰጡም።

ሆኖም በእሳቸው የሚመራው የክልሉ ፖሊስ ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ በጋምቤላ ከተማ "በሌሊት ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት በተፈፀመ ጥቃት የዜጎች ሕይወት ማለፉን" ገልጿል። ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ለሕግ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን የገለፀው ኮሚሽኑ፣ በከተማዋ የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስ ለመቆጣጠር ለማኅበረሰቡ የድጋፍ ጥሪ አቅርቧል።

ከምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ በጋምቤላ ከተማ የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ "በጥብቅ" መከልከሉንም በመግለጫው አስታውቋል።

የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ደግሞ፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሁሉም ቀበሌዎች የማረጋጋት ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፆ፣ በስጋት ምክንያት ቀያቸውን የለቀቁ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።

በከተማው የሚገኙ የንግድ ተቋማትም ወደ ሥራቸው እንዲመለሱም አስተዳደሩ አሳስቧል።