ከኢትዮጵያ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ካሳ የተጠየቀበት የባቡር መስመር ግንባታ እንዴት በ213 ሚሊዮን ዶላር ተዘጋ?

የፎቶው ባለመብት, AKH Railway Project
በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ በላይ የካሳ ክፍያ ክስ የተመሠረተበት የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጄክት ክስ የመጨረሻ ውሳኔ አገኘ።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ግንባታው በ2013 ዓ.ም. የተቋረጠው ፕሮጄክቱ ከዓመታት የክስ ሂደት በኋላ መስከረም 13/ 2019 ዓ.ም. የመጨረሻ ውሳኔ ማግኘቱን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የባቡር መስመሩን እንዲገነባ ውል ያሰረው 'ያፒ መርከዚ ኢነሳት' የተባለው የቱርክ ኩባንያ ደረሰብኝ ባለው የግንባታ መጓተት፣ ውድመት እና ዝርፊያ ከወለድ ጋር 1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ክስ በለንደን ዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት አቅርቦ ነበር።
በዚህም ማዕከላዊ ኢትዮጵያን ከሰሜን ኢትዮጵያ የሚያገናኘው የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጄክት ያለፉትን አራት ዓመታት በክስ እና ድርድር አሳልፏል።
ከዓመታት የክስ ሂደት በኋላ ተቋራጩ ለደረሰበት ጉዳት 213 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እና ክሱ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ክፍያው እስከሚፈጸምበት ጊዜ ድረስ የሚታሰብ የዘጠኝ በመቶ ወለድ ጋር እንዲከፍል ተወስኖበታል።
የውሳኔው ዝርዝር ምንድን ነው? ኢትዮጵያስ ለምን "ፍትሃዊ ነው" አለች?
የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጄክት 392 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው እና 1.7 ቢሊዮን ዶላር በጀት የተመደበለት ነው።
የባቡር ፕሮጄክቱን ለመገንባት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከቱርኩ 'ያፒ መርከዚ' ኩባንያ ጋር ውል ገብቶ ግንባታው በይፋ በ2007 ዓ.ም. ነበር የተጀመረው።
ግንባታውን በ42 ወራት (በሦስት ዓመት ከአምስት ወር) ለማጠናቀቅ ውል ቢታሰርለትም በፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለአምስት ዓመታት ተጓትቷል።
በ2013 ዓ.ም. የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ከመቀስቀስ ጋር ተያይዞ ደግሞ ግንባታው ተቋርጧል።
ጥር 2014 ዓ.ም. ደግሞ ተቋራጩ 'ያፒ መርከዚ' የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን "ዋና ዋና ግዴታዎቹን አልተወጣም" በሚል ውሉን በተናጠል አፍርሷል።
ተቋራጩ በግንባታ መጓተት፣ በወሰን ማስከበር ችግር እና በኃይል አቅርቦት ችግር እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በደረሰበት ጉዳት እና ዝርፊያ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖረሬሽን ላይ (ከወለድ ጋር) የ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የይገባኛል ክስ መሥርቷል።
ለዓመታት በክርክር ላይ የቆየው ክሱ፤ ባለፈው ወር ባገኘው ውሳኔ የግልግል ፍርድ ቤቱ ኢትዮጵያ 242.8 ሚሊዮን ዶላር እንድትከፍል ወስኖባታል።
ኮርፖሬሽኑ የፈጸመው እና "ያልተሰበሰበ ቅድመ ክፍያ" 29.1 ሚሊዮን ዶላር ተመላሽ እንዲሆንለት ፍርድ ቤቱ መወሰኑን ተከትሎ ለተቋረጩ ወለድን ሳይጨምር 213.7 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ካሳ እንዲከፈለው እንደተወሰነበት የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።
ከዚህም ውስጥ ትልቅ የሆነውን 36.7 በመቶ ድርሻ (89.2 ሚሊዮን) የሚይዘው ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ የደረሰው ጉዳት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቱ ኩባንያው ይገባዋል ብሎ ከበየነለት ካሳ ውስጥ 31.6 በመቶው ለግንባታ መዘግየቱ፣ 27.7 በመቶ ያልተከፈሉ ክፍያዎች 3.8 በመቶ ደግሞ ተቋራጩ ግንባታው በመቋረጡ ምክንያት ላጣው ትርፍ መሆኑን ቢቢሲ ከኮርፖሬሽኑ ያገኘው ሰነድ ያመለክታል።
ኮርፖሬሽኑ እንዲከፍል በተወሰነበት 213.7 ሚሊዮን ዶላር ላይ ክሱ ከተጀመረ አነስቶ ክፍያው እስኪፈጸም ድረስ የሚሰላ በዓመት ዘጠኝ በመቶ ወለድ የሚከፍል ይሆናል።
ቢቢሲ ከኮርፖሬሽኑ ባገኘው ሰነድ መሠረት እንዲከፍል የተወሰነበት ክፍያ የአንድ ቀን ወለዱ 52 ሺ ዶላር በላይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Railway Corporation
'ያፒ መርከዚ' የይገባኛል ክሱን መጀመሪያ ሲመሠርት ትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ገንዘብ ሚንስቴርንም ከምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጋር በጣምራ ከስሶ እንደነበር ውስጠ አዋቂዎች ጠቁመዋል።
ይህም ተቋራጩ የሚወሰንለትን ካሳ ለማስፈጸም "ሰፊ ዕድል" የሚሰጥ እና ተጠያቂነትም በአጠቃላይ የመንግሥት ንብረት እና ሀብቶች ላይ የሚያሳርፍ ነው። የኮርፖሬሽኑ ጠበቆች ክሱ ውል ባሰረው ተቋም ብቻ እንዲወሰን ያቀረቡት "መቃወሚያ" ተቀባይነት በማግኘቱ የክርክር ሂደቱ በሁለቱ ተቋማት ብቻ እንዲወሰን ተደርጓል።
በዚህም ምክንያት በዕዳው "አየር መንገድ ሊያዝ ይችላል፤ መርከብም ሊያዝ ይችላል" በማለት ስለ ክርክር ሂደቱ የሚያውቁ የቢቢሲ ምንጭ ሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከክሱ እንዲወጡ መደረጉ እና ኃላፊነቱን በኮርፖሬሽኑ ሥር እንዲሆን መወሰኑን እንደ "ድል" ይመለከቱታል።
ተቋራጩ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባሉ እና የካሳ ከፍያ የተከፈለባቸው 1,500 በሚሆኑ ተሽከርካሪ እና መሣሪያዎቹን ጨምሮ የንብረቶቹ ስመ ሀብታቸው ወደ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እንዲዞሩ መወሰኑንም ምንጮች አመልክተዋል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የቢቢሲ ምንጭ እነዚህ ንብረቶች "ጉዳት ደርሶባቸው ሊሆን ይችላል፤ በከፊል የሚሠሩ፣ ጥገና የሚፈልጉ. . ." ሊሆኑ እንደሚችሉ አመልክተዋል።
ከክሱ በፊት ለአንድ ዓመት ተደርጓል በተባለ ድርድር የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ፈቃደኛ እንደነበር ምንጮች አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ ተቋራጭ ኩባንያው ወደ ግልግል ፍርድ ቤት መሄድን በመምረጡ ጉዳዩ በድርድር አለመፈታቱን ጠቁመዋል።
ኮርፖሬሽኑ በአገር ውስጥ የሕግ ባለሙያዎች ተወክሎ የተከራከረ ሲሆን፣ ውሳኔውንም "ፍትሐዊ" አድርገው መመልከታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ያላመንባቸው፤ ያልተቀበልናቸው ነገሮች ውድቅ ተደርገዋል" በማለት ምንጮች ተቋራጩ ያቀረባቸው የማይካዱ ሁኔታዎች በመሆናቸው የፍርድ ቤቱ ውሳኔን ኮርፖሬሽኑ እንደሚቀበል ገልጸዋል።
የካሳ ክፍያው ቀነ ገደብ እንዲሁም የአከፋፈል ሁኔታ በሁለቱ ወገኖች ስምምነት መሠረት እንደሚከፈልም አክለው ተናግረዋል።
የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጄክት ከመቋረጡ በፊት የግንባታ አፈፃፀሙ 92 በመቶ የነበረ ቢሆንም፤ በሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም እንደ መሬት መንሸራተት ባሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት እንደደረሰበት ታውቋል።
ቢሆንም ግን ከግንቦት 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በራሱ አቅም ግንባታውን መቀጠሉን አስታውቋል።
"በስርቆት፣ በዘረፋ፣ በጦርነት እንዲሁም በመሬት መንሸራተት ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሶበታል። የጥገና ሥራ ባለመሠራቱም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ክፍሎች አሉ" ሲሉ የቢቢሲ ምንጭ ሁኔታውን ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጄክትን ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት እንደሚፈጅበትም ገልጿል።
ግንባታውን ለመፈፀም የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን 1.2 ቢሊዮን ዶላር 'ከክሬዲት ስዊዝ' እንዲሁም 300 ሚሊዮን ዶላር ከቱርክ ኤግዚም ባንክ ተበድሯል።
ፕሮጀክቱ 10 ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን፤ በርካታ ዋሻዎች፣ ድልድዮች፣ የኃይል መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች፣ እንዲሁም የጥገና ማዕከልን የያዘ ነው።

































