ማዱሮ በኒው ዮርክ በቀረቡባቸው አዳዲስ ከማሰቃየት ጋር የተያያዙ ክሶች ጥፋተኛ አይደለሁም አሉ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/Jane Rosenberg
ማዱሮ በኒው ዮርክ በቀረቡባቸው አዳዲስ ከማሰቃየት ጋር የተያያዙ ክሶች ጥፋተኛ አይደለሁም አሉ።
የቬንዙዌላ የቀድሞ መሪ ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው ሲሊያ ፍሎሬስ ሐሙስ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው፣ ስቅይት ለመፈፀም በማሴር በቀረበባቸው አዲስ ክስ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ገለፁ።
የአሜሪካ መንግሥት ማዱሮን የከሰሰው ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ሽብርተኝነት፣ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እና ከጦር መሣሪያ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች የነበረ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ደግሞ በማዱሮ እና በፍሎሬስ ላይ አዳዲስ ክሶችን ጨምሯል።
በጥር ወር በአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ ተይዘው ወደ ኒው ዮርክ የተወሰዱት ማዱሮ እና ባለቤታቸው አሁንም እዚያው በእስር ላይ ይገኛሉ።
ጥንዶቹ የቀረቡባቸውን ክሶች ውድቅ በማድረግ ጥፋተኛ አይደለንም ብለዋል። በተጨማሪም የመንግሥት መሪዎች የሚያገኙት የሕግ ከለላ እንደሚመለከታቸው በመግለጽ ክሱ እንዲሰረዝ ጠይቀዋል። ችሎቱ ለአውሮፓውያኑ ሰኔ 2027 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ባለፈው ሳምንት በቀረበው አዲስ የክስ ሰነድ ላይ የመንግሥት ዐቃቤያን ሕግ፣ ማዱሮ እና ፍሎሬስ "በኃይል የሚፈፀም የጭቆና ሥርዓት በመፍጠር እንዲቀጥል አድርገዋል" ሲሉ ከሰዋቸዋል። በዚህም "በሺዎች የሚቆጠሩ ቬንዙዌላውያን" ተገድለዋል፣ ወከባ እና ስቅየት ደርሶባቸዋል ሲሉም በክሳቸው አመልክተዋል።
ኒኮላስ ማዱሮ የአሜሪካ መንግሥት ያቀረበባቸውን አዳዲስ ክሶች ውድቅ በማድረግ፣ "የቀረቡብኝን የሐሰት ክሶች እና የሐሰት ምስክርነቶች አልቀበልም" ብለዋል።
"ይህንን ሰነድ ሙሉ በሙሉ አልቀበለውም" ሲሉም ማዱሮ በአስተርጓሚ አማካይነት ለፍርድ ቤቱ በስፓኒሽ ተናግረዋል።
ዳኛው አልቪን ሄለርስታይን ማዱሮን አቋርጠው፣ ፍርድ ቤቱ ማዱሮ ጥፋተኛ አይደለሁም ማለታቸውን እንደሚመዘግብ ገልፀዋል።
የቀድሞው የቬኔዙዌላ ፕሬዚዳንት የሰጡትን ቃል ተከትለው ባለቤታቸው ፍሎሬስም እንዲሁ "እኔ ሙሉ በሙሉ ንፁህ ነኝ፤ ጥፋተኛ አይደለሁም" በማለት ክሱን አስተባብለዋል።
የእስረኛ ልብስ ለብሰው ፍርድ ቤት የቀረቡት ማዱሮ እና ፍሎሬስ ያላቸው ቁመና በብሩክሊን የእስር ቤት ቆይታቸው ወቅት ክብደታቸው ስለመቀነሱ ያሳያል።
በክስ ሰነዱ እንደተጠቀሰው፣ ተፈፅመዋል ከተባሉት የማሰቃያ ዘዴዎች መካከል "በኤሌክትሪክ ንዝረት ማሰቃየት፣ ማፈን፣ መድፈር፣ ሰዎች በግዳጅ ራቁታቸውን እንዲሆኑ ማድረግ፣ ለረጅም ጊዜ ለብቻ ማግለል፣ ማስራብ፣ ለቅጣት በሚውሉ የእስር ክፍሎች ማቆየት እና ሥነ ልቦናዊ ስቅየት መፈፀም" የሚሉት ይገኙበታል።
አሜሪካ፣ ማዱሮ "በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ" ስቅየት እንዲፈፀም ፈቃድ ሰጥተዋል ስትልም ከሳለች። በዚህ ሂደት የአሜሪካ ዜጎችም ለስቅየት መዳረጋቸው በክሱ ተካቷል።
ማዱሮ ከዚህ ቀደም የቀረቡባቸውን ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር የተያያዙ ክሶች፣ የቬንዙዌላን የነዳጅ ሀብት ለመቆጣጠር የታቀዱ መሣሪያዎች ናቸው ብለው ነበር።
የማዱሮ እና የባለቤታቸው ጠበቆች፣ ማዱሮ የሉዓላዊ አገር መሪ በመሆናቸው ያለመከሰስ ሕጋዊ ከለላ አላቸው ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን አሜሪካ ማዱሮን በኃይል ይዛ መውሰዷም ሕገወጥ ነው በማለት ሞግተዋል።



































