ሶማሊላንድ በግብፅ የተመሠረተውን ጥምረት በመቃወም ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Madaxtooyada JSL/fb
የኢትዮጵያን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል የትኛውንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት እና ጥምረትን እንደምትቃወም ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ተናገሩ።
አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ በአሜሪካ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ሲመለሱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶችን በማንሳት ተናግረዋል።
ከጎረቤታቸው ኢትዮጵያ ጋር ባላቸው ትብብር ከፍተኛ መተማመን እንዳላቸው ያመለከቱት ፕሬዝዳንቱ "የኢትዮጵያን መረጋጋት እና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል የትኛውንም ጣልቃ ገብነት እንቃወማለን" በማለት አጋርነታቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ለሶማሊላንድ የምክር ቤት አባላት፣ የጦር መሪዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሌሎች ቁልፍ ሰዎች በተገኙበት ባደረጉት ንግግር በቅርቡ በግብፅ አማካይነት የተመሠረተውን የአፍሪካ ቀንድ አገራት ጥምረትንም ተችተዋል።
ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በግብፅ በተካሄደው የሶማሊያ፣ የኤርትራ እና የሱዳን መሪዎች በተሳተፉበት ስብሰባ ላይ አገራቱ ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊላንድ ጥቅም አንጻር ተቃራኒ የሆነ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል።
አገራቱ የአባሎቻቸውን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንደሚደግፉ በመግለጽ በተዘዋዋሪ ከሶማሊያ ተነጥላ ነጻ አገርነቷን ያወጀችውን ሶማሊላንድን የሚመለከት ሃሳብ ሰንዝረዋል።
ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ በነጻ አገርነት የቆየችው ሶማሊላንድ ባለፈው ዓመት በእስራኤል እውቅና ያገኘች ሲሆን፣ በቅርቡም ፕሬዝዳንት ትራምፕ አገርነቷን የሚደግፍ ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት አብዲራህማን የግብፅን እና የአፍሪካ ቀንድ አቋም ከመተቸታቸው ባሻገር "ቀጣናውን የሚመለከት የትኛውም ውሳኔ ከሶማሊላንድ ተሳትፎ ውጪ ሊደረግ አይገባም" በማለት አስጠንቅቀዋል።
ጨምረውም አገራቸው ከጎረቤት አገራት ጋር በሰላም እና በመልካም ጉርብትና የመኖር ፖሊሲ እንደምትከተል ጠቅሰው፣ ነገር ግን "በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ለመግባት ለሚሞክር አገር ተገቢው ምላሽ" እንደሚሰጠው አስጠንቅቀዋል።
ሶማሊላንድ ይህንን አቋሟን ይፋ ያደረገችው የኢትዮጵያ ጎረቤት ሆኑት ሱዳን፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ከረጅም ጊዜ ባላንጣዋ ጋር ጥምረት ፈጥረው በአባይ ወንዝ ላይ በምታካሂደው ልማት እና የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የሚቃረን የአቋም መግለጫ ካወጡ በኋላ ነው።
በተጨማሪም የአራቱ አገራት የአቋም መግለጫ ሶማሊላንድ ለዓመታት ስትታገልለት የነበረው የአገርነት እውቅናን የማግኘት ፍላጎት የሚቃወም ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከጉባዔው በኋላ ባወጣው መግለጫ ከአባይ ወንዝ እና ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዙ መልክዓ ምድራዊ እና ታሪካዊ እውነታዎች በፖለቲካ ትርክቶች እና በኃይል እርምጃዎች ሊቀየሩ አይችሉም በማለት የአራቱን አገራት አቋም እንዳማትቀበለው አስታውቃለች።
በግብፅ ኤል አልአሚን የባሕር ዳርቻ ከተማ ይፋ በተደረገው የአራቱ አገራት የአቋም መግለጫ ላይ አገራቱ በጋራ ለመቆም ስምምነት ከደረሱ በኋላ ሶማሊያ አቋሟን አስታውቃለች።
በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ውዝግብ በተነሳበት ጊዜ የሶማሊያው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐሰን ሞሐመድ አሊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በተፈጠረው ውጥረት አገራቸው "ገለልተኛ" አቋም እንደምትይዝ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ እና ከሶማሊላንድ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊላንድ ጋር በፈረመች በት ጊዜ ከፍተኛ ውዝግብ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህም ሳቢያ ሶማሊያ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቴን ጥሳ ከግዛቴ አካል ጋር ስምምነት ፈርማለች በማለት ከኤርትራ እና ከግብፅ ጋር የጋራ ስምምነት ፈጥራ ነበር። ነገር ግን በቱርክ አሸማጋይነት አለመግባባቱ ተፈትቶ ሁለቱ አገራት ሰላም አውረድዋል።




































