በቀጥታ የ'ኤአይ' ድጋፍ በተደረገለት የጭንቅላት ቀዶ ሕክምና ዕጢ የወጣለት የመጀመሪያው ታካሚ

በኤአይ ድጋፍ ዕጢው የወጣለት ሪስ ሂበርት
የምስሉ መግለጫ, የሪስ ሂበርት ዕጢ ዐይነ-ስውርነት ሊያስከትል የሚችል ነበር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተሊጀንስ/ኤአይ) ቀጥታ ድጋፍ የጭንቅላት ቀዶ ሕክምና የተደረገለት የዓለማችን የመጀመሪያው ታማሚ የጭንቅላት ዕጢ በተሳካ ሁኔታ ወጣ።

በምሥራቅ እንግሊዝ ቤድፎርድሻየር ነዋሪ የሆነው የሁለት ልጆች አባት ሪስ ሂበርት፣ ቀዶ ሕክምናው ባይደረግለት የዐይን ብርሃኑን ያጣ እንደነበር የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ባለሙያ ተናግረዋል።

የኤአይ መሣሪያው የተሰጠውን የኦፐሬሽን ቪዲዮ ግብዓት በመተንተን፣ ጠቃሚ ነገር ግን የተደበቁ ስሮችን እና ነርቮችን ከታማሚው አንጎል ውስጥ እንዴት ማለፍ እንዳለባቸው ለቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ምክር ሰጥቷል። ይህም የታማሚው ደኅንነት በተጠበቀ መልኩ ዕጢውን በጥንቃቄ እንዲያወጡ ረድቷቸዋል።

"ከታማሚው ደኅንነት አንጻር፣ ጥቅሙን በደምብ አይቻለሁ። ጭንቅላታችን ውስጥ ጠቋሚ ምልክቶች የሉም" ሲል ሂበርት ተናግሯል።

የ48 ዓመቱ የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊው ሂበርት ከ18 ወራት በፊት፣ ሁልጊዜ በምሳ ሰዓት ሁለት ማይል ድረስ በእግሩ የሚጓዝ ብቁና ጤናማ ሰው ነበር።

ከእነዚህ የእግር ጉዞዎቹ በአንዱ ጉዞ ወቅት ነበር ራሱን ስቶ መንገድ ላይ የተገኘው።

በአእምሮው ላይ የተደረገው የስካን ምርመራ 11 ሚሊሜትር የሆነ ወደ ካንሰር ደረጃ ያልደረሰ ዕጢ በጭንቅላቱ ውስጥ መኖሩን አመለከተ።

ዕጢው፣ በዋናነት ለአንጎል ደም የሚያቀርቡ ወሳኝ የደም ሥሮች እና ዕይታን የሚቆጣጠሩ 'ኦፕቲካል' ነርቮች በሚገኙበት ቅርብ ርቀት ላይ ነው የነበረው።

የሂበርት ዕጢ፣ ዕይታን የሚቆጣጠሩ ነርቮቹን በተጫነ ቁጥር ዕይታውን ያጠበዋል።

ከፍተኛ ድካም እና ብዥታ

ምንም እንኳን አስቸኳይ ቀዶ ሕክምና ባያስፈልገውም፣ ሂበርት ሁኔታዎች እየከፉበት ከፍተኛ ድካም እና ብዥታ እተሰማው መጣ።

"በ18 ዓመታት የጋብቻ ሕይወቴ ሁልጊዜም ከመኝታዬ እንደተነሳሁ ለሚስቴ ቡና አፈላላት ነበር" ይላል ሂበርት። ዕጢው ይህን ሂደት እንዲያቆም እንዲያደርገው እንዳልፈቀደ ተናግሯል።

ከፍተኛ የስሜት እና የሥነ ልቦና ተፅዕኖ እንዲያድርበት አድርጓል። አክሎም "ምንም እንኳን በቅንነት ድጋፍ የሚያደርጉልኝ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም፣ የሰዎች ሸክም መሆን አትፈልግም" ብሏል።

የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች በኤአይ መሣሪያ በመታገዝ የሚደረግ ኦፐሬሽንን በመሞከር የመጀመሪያው ሰው እንዲሆን አማራጭ ሲሰጡት አላቅማማም።

"ታማሚዎች የምርምር ውጤቶችን ለመቀበል ዝግጁ ካልሆኑ ዶክተሮች እንዴት ይማራሉ? ሕክምናውስ እንዴት ያድጋል?" ሲል ያጠይቃል።

የተደረገለት ቀዶ ሕክምና ኢንዶስኮፕ - በዘንግ ቀጭን ካሜራ ወደ ራስ-ቅሉ የመጨረሻ ጥግ ማስገባትን ያካትታል።

በዚህ ሰዓት ዕጢው በአጥንት ንጣፎች ውስጥ ተደብቆ ነው የነበረው።

የሰዎች የአካል ክፍል እንደየሰዉ ስለሚለያይ፣ ዕጢውን ለማውጣት በጣም አስተማማኝ የሆነውን ቦታ መለየት ቀላል አልነበረም።

በመሰል የሕክምና ሂደት የሚያጋጥሙ የተወሳሰቡ ሁኔታዎች መጠን የተለያየ ቢሆንም፣ ዕጢውን ሙሉ በሙሉ ያለማግኘት ዕድል ከ25 አስከ 50 በመቶ ይደርሳል። ዋና የደም-ሥርን የመጉዳት ዕድል ደግሞ ከ0.2 አስከ 2 በመቶ ነው።

የኤአይ መሣሪያ ያስፈለገው በዚህ ምክንያት ነው።

የቀዶ ሕክምናው ሂደት

የኤአይ መሣሪያው በሁለተኛ ስክሪን ላይ በቀጥታ የሚያገኘውን የቪዲዮ ግብዓት ይተነትናል። የቀዶ ሕክምና መሣሪያዎችን ይለያል። ከዚያም ሥሮች እና ነርቮች ሊኖሩ የሚችሉበትን ትክክለኛ ቦታ ይለያል። በዚህ ሂደት ዕጢውን ለማውጣት የተሻለ እና ደኅንነቱ የተጠበቀውን ቦታ ይለያል።

በስልኮች ጋር ካለው ፊትን የመለየት ቴክኖሎጂ ጋር ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን ጠቃሚ እና ብዙ ጊዜ የተደበቁ የአካል ክፍሎችን አቀማመጥ ይረዳል።

ተመራማሪዎች ዕጢ በማስወጣት ሂደት ውስጥ የኤአይ መሣሪያውን ስለሠራው ዘዴ አስቀድመው ያሠለጠኑ ሲሆን ግምገማም አድርገዋል።

"ብዙ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች በሕይወት ዘመናቸው ከሚያዩት እና ከሚተግብሩት በላይ በብዙ ኦፐሬሽኖች ላይ ሠልጥኗል። እናም ሁለተኛ ዐይን እንዳለው ባለሙያ ይሠራል" ሲሉ ሂደቱን ካከናወኑት አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ሃኒ ማርከስ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የኤአይ መሣሪያው እገዛ ብቻ የሚያደርግ ሲሆን ሙሉ ቁጥጥር የሚያደርጉት የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎቹ መሆናቸውን የሕክምና ቡድኑ አስታውቋል።

'ሕይወቴን መልሶልኛል'

"ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ዐይኖቼን ስገልጥ 360 ዲግሪ ማየት የቻልኩ ያህል ነው ተሰማኝ። ለአንድ ዓመት በዚህ ደረጃ ግልጥ ብሎልኝ አላየሁም" በማለት ሂበርት ተናግሯል።

ቀዶ ሕክምናው ከተደረገለት በኋላ ባሉት ስምንት ሳምንታት ውስጥ በየጥቂት ቀናት ዕይታው እተሻሻለ መሄዱን ይገልፃል።

"የመሥራት አቅሜ ተመልሷል፤ ከቀዶ ሕክምናው በፊት የነበሩብኝ ማነቆዎችሁሉ አሁን ተወግደዋል" ሲልም አክሏል።

ያገኘውን ለውጥ በአጭሩ ሲገልፅ "ሕይወቴን መልሶልኛል" ብሏል።

የጤና ምርምር ሚኒስትሩ ጀምስ ፍሪዝ፣ ሂበርት "ሕይወቱን የሚቀይር ቀዶ ሕክምና" ስለተደረገለት ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

"የኤአይ መሣሪያዎች ተገቢው መመሪያ ያስፈልጋቸዋል። ሁልጊዜም የሰዎች ደኅንነት ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን እናረጋግጣለን" ሲሉም ሚኒስትሩ አክለዋል።