በዌስት ባንክ የሚኖሩ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ላይ ጥቃት ፈጸሙ

ተሽከርካሪዎች እና ጭምብል ያጠለቁ ግለሰቦች
የምስሉ መግለጫ, ጭምብል ያጠለቁ ሰፋሪዎች በዲፕሎማቶቹ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት በመፈፀም ተከሰዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ልዑክ በእስራኤል በኃይል በተያዘው ዌስት ባንክ በሚገኙ እና ጭምብል ባጠለቁ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች ጥቃት ደረሰባቸው።

ቤልጂየም በቆንስል ጀኔራሏ እና በሌሎች መልዕክተኞች ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዛ፣ እስራኤል ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትን ለሕግ እንድታቀርብ ጠይቃለች።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በበኩሉ "አስከፊ" ሲል የገለጸውን ጥቃት ያወገዘ ሲሆን በክስተቱ ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ገልጿል።

ሆኖም የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጽ/ቤት "በተፈጠረው ነገር ላይ ጥርጣሬ እንዳለው" እና "እስራኤል ላይ ጥላቻ ለመንዛት የተቀናበረ ዘመቻ አካል" እንደሆነ አመልክቷል።

ጥቃቱ የተከሰተው በርካታ ፍልስጤማውያን እና የዋሽንግተን ፖስት ፎቶግራፍ አንሺ ሄይዲ ሌቪን በዌስት ባንክ በሚገኝ መንደር ውስጥ ሰፋሪዎች ባደረሱባቸው ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸው ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በሌቪን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት "የሚረብሽ እና መጥፎ" ብለውታል።

በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክ ሁካቢም ጥቃቱን አውግዘዋል።

ሁካቢ "ጭምብል ባጠለቁ ፈሪዎች የተፈፀመ አስጸያፊ የሽብር ተግባር" ሲሉ ድርጊቱን ኮንነውታል። የእስራኤል ታማኝ አጋር የሆኑት ኩካቢ ጥቃት አድራሾቹ " በሕጉ መሠረት ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ እና ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተውጣጡት አውሮፓዊያኑ ዲፕሎማቶች ጥቃቱ የደረሰባቸው ቅዳሜ ዕለት በራማላህ አቅራቢያ ወደሚገኘውና በብዛት የክርስትና እምነት ተከታዮች ወደሚኖሩበት ታይቤህ መንደር በሄዱበት ወቅት ነው።

ዲፕሎማቶቹ ወደ መንደሯ ያቀኑት የወይራ ፍሬያቸውን ለመሰብሰብ በሚሞክሩ ፍልስጤማውያን በየቀኑ ማለት በሚቻል መልኩ በእስራኤላዊያን ሰፋሪዎች ጥቃት ከተፈፀመባቸው በኋላ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ለመገምገም ነበር።

በአካባቢው የተቀረጸ ቪዲዮም ጭምብል ያጠለቁ ሰፋሪዎች ዲፕሎማቶቹ ጋር ሲጋጩ አሳይተዋል። በዲፕሎማቶቹ ላይ ድንጋይ እንደተወረወረባቸውም ሪፖርቶች አመልክተዋል።

የቤልጂየም ባለሥልጣናት እንዳሉት የቆንስላው ንብረት የሆነ መኪና መስታዎት የተሰባበረ ሲሆን ፈረንሳዊ ከንቲባ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

የቤልጂየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ፕሬቮት ጥቃቱን አውግዘው፣ እስራኤል በድርጊቲ ተጠያቂ የሆኑትን ግለሰቦች ለፍርድ የማቅረብ ኃላፊነት አለባት ብለዋል።

"ፍልስጤማውያን ይህንን ጥቃት በየቀኑ ይጋፈጣሉ። ሰፋሪዎችም ስለእነርሱ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች እና ዲፕሎማቶችን ኢላማ ያደርጋሉ። የወይራ ፍሬ መሰብሰብ፣ ስለሚፈፅሙት ወንጀል ሪፖርት ማድረግ ፣ ዲፕሎማሲያዊ ግዴታዎችን መወጣት ማንንም ለጥቃት ሊያጋልጥ አይገባም" ሲሉም ተናግረዋል።

የእስራኤል ባለሥልጣናትም አካባቢውን በኃይል እንደተቆጣጠረ ኃይል የፍልስጤማዊያንን ደኅንነት መጠበቅ፣ የዲፕሎማቶችን እና የጋዜጠኞችን ደኅንነት ማረጋገጥ እና ተጠያቂ የሆኑትን ለፍርድ ማቅረብ እንዳለባቸውም ፕሬቮት አክለዋል።

በሰፋሪዎቹ የሚፈፀመው የሕግ ጥሰትም መቆም እንዳለበት ገልጸው፣ ቤልጂየም ለዚህ ጥቃት ተጠያቂ በሆኑ እና እነርሱን በሚደግፉ አካላት ላይ የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ እንዲጥል ግፊት ማድረጓን እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር በበኩላቸው "በአመፀኛ እስራኤላዊያን" ተፈፀመ ያሉትን ጥቃት በጥብቅ አውግዘዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ጥቃት ከደረሰባቸው ዲፕሎማት አገራት ኤምባሲ ጋር እየተነጋገረ እንደሆነም ገልጸዋል።

የዲፕሎማቶቹ ጉብኝት ከእስራኤል መከላከያ ኃይል ጋር በቅንጅት የተደረገ አለመሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ እንዲህ ዓይነት ቅንጅት ቢኖር የጎብኝዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ይቻል ነበር ብለዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት አባላትም ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን ድርጊቱ ሲፈፀም የመከላከያ ኃይል አባላት በሥፍራው እንዳልነበሩ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደሚያመለክት ተናግረዋል።

የኔታንያሁ ጽ/ቤት ግን ስለደረሰው ጥቃት የሚወጡ ሪፖርቶችን ተንተርሶ ውሳኔ ከመስጠት በፊት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚወጡ ምሥሎችም " የክስተቶችን ቅደም ተከተል ወይም ለዚህ ተጠያቂ የሆነው ማን እንደሆነ አያመለክቱም" ብሏል።

ጨምሮም " ክስተቱ ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን እንዲሁም የእስራኤል ፖሊስ እና የፎረንሲክ መርማሪዎች ሐቁን ለማረጋገጥ እና ተጠያቂ የሆኑትን ለመለየት ምርመራ መጀመሩን" ገልጿል።