በእርግዝና ወቅት መንታዎችን ከልዩ ሕመም የሚታደገው ፈር ቀዳጅ ሕክምና

የፎቶው ባለመብት, Brioney Garrett
በቅድመ እርግዝና ወቅት መንታዎች የሚገጥማቸውን ከባድ እና ልዩ ሕመም ከፍተኛ የድምፅ ማዕበል በመጠቀም ማከም እንደሚቻል በጥናት ተለየ።
ከአንድ መንታ ሕፃን ወደ ሌላው የሚተላለፈው ደም እኩል ያለመሆን እክል አንደኛው ሕፃን አካለ መጠኑ አነስተኛ እና ሌላው ደግሞ ትልቅ መሆን በሕይወት መትረፋቸውን አደጋ ላይ ያስቀምጣል።
ቢሮኒ ጋሬት በእርግዝናዋ ወቅት በለንደን ሐኪሞች የችግሩ ምንጭ ቀዶ ሕክምና ሳያስፈልግ የደም መተላለፍን ከመዝጋታቸው በፊት መንታ ልጆቿ አደጋ ውስጥ ነበሩ።
የዓለም የመጀመሪያው የሆነውን ሕክምና ተከትሎ ናንሲ እና ማርጎ ጤናማ ሆነው ተወልደዋል። አሁን አራት ዓመት የሆናቸው መንታዎቹ ትምህርት በቅርቡ ይጀምራሉ።
በጥናቱ ሙከራ ከተሳተፉ 10 ሰቶች ውስጥ ግማሹ ተጨማሪ ሕክምና አስፈልጓቸዋል። ከ20 መንታ ሕፃናት ውስጥ 12ቱ ሕክምናውን ተከትሎ በሕይወት መትረፋቸውን የአሜሪካ የማህፀን እና ፅንስ ጆርናል ዘግቧል።
ኩዊን ሻርሌት እና ቸልሲ ሆስፒታል አጥኝዎች ልዩ የጤና እክሉን ያለ ቀዶ ሕክምና፤ በእናት ሆድ መርፌ ወይም ቴሌስኮፕ ሳያሳርፉ በማከማቸው "በጣም ደስተኞች" መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የሕክምና ዘዴው በሰፊው ከመቅረቡ በፊት ውጤታማ ሕክምና መሆኑን ለማሳየት በተጨማሪ ነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ ትልቅ ጥናት አስፈላጊ ነው።
ቢሮኒ ልጆቿን "ተዓምራዊ መንታዎቼ" ትላቸዋለች።
"በጣም ከበድ ሁኔታ ውስጥ ነበርን እና ይህን አልረሳውም" ትላለች።
"ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችሉ እንደነበር ሁሌም አብሮኝ አለ። በየቀኑ በረከቴን አስባለሁ።"
ከመንታ መንታ የደም ዝውውር እክል የእንግዴ ልጅ በሚጋሩ ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ ተመሳሳይ መንታዎችን ያጠቃል። በዩናይትድ ኪንግደም በየዓመቱ ከ300 እስከ 400 የሚሆኑ እርግዝናዎች ላይ ይከሰታል።
በሕፃናት ላይ ያልተመጣጠነው የደም ዝውውር ከፍተኛውን መጠን በሚያገኘው ሕፃን ላይ ከመጠን ያለፈ ፈሳሽ የሚፈጥር እና አንደኛው ሕፃን ላይ አነስተኛ ፈሳሽ በመፍጠር ሁለቱንም አደጋ ላይ ይጥላል።
የተለመደው ሕክምና እናት ሆድ ላይ መርፌ በመላክ ፈሳሹን መምጠጥ አሊያም ሌዘርን በመጠቀም የደም ቱቦን መዝጋት ነው።
ለብሮኒ ሕክማናው ቀጥታ እና 20 ደቂቃዎችን የፈጀ ነው። በልዩ ሁኔታ የተነደፈው ማሽን በእንግዴ ልጁ ላይ የድምፅ ማዕበል ስራውን ሲሰራ በጀርባዋ ተኝታ ነበር።
"በጣም ፈጣን ነበር እና ምንም ህመም አልነበረውም" ትላለች።
ብሮኒ እና ከዩኬ እና ከአውሮፓ የመጡ ሌሎች ነፍሰ ጡር ሴቶች በቅድመ እርግዝናቸው ወቅት እክሉ በመታየቱ በጥናቱ ተሳትፈዋል።
የኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን የፅንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ክርስቶፈር ሊስ ጥናቱ "በጣም ተስፋ ሰጪ ነው" ብለዋል።
"በሰፊ ጥናት ይህ የሚሰራ ከሆነ ከባድ ሕክምና ማድረግ ለሚጠበቅባቸው በርካታ ሰቶች ተስፋ ይሰጣል" ሲሉ ተናግዋል።















