በኬንያ በኢቦላ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር ሰባት ደረሰ

በናይሮቢ ሆስፒታል የመከላከያ ልብስ የሚለብስን ባልደረባ የምታግዝ ነርስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የኬንያ ጤና ሚኒስቴር አራት አዳዲስ ሰዎች በኢቦላ ቡንዲቡግዮ ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን አስታወቀ።

እስካሁን ድረስ በኬንያ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ወደ ሰባት ከፍ ብሏል።

የኬንያ ጤና ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠው ግለሰቦች መካከል ሦስቱ በአገሪቱ የመጀመሪያውን የኢቦላ ታማሚ ያከሙ የጤና ባለሙያዎች መሆናቸውን ገልጿል።

አራተኛው ግለሰብ በኢቦላ ተይዞ የሞተው ግለሰብ ዘመድ መሆኑን ጨምሮ አስታውቋል።

እንደ አገሪቱ የጤና ሚኒስቴር መግለጫ ግለሰቡ መስከረም 26/2019 ዓ.ም. ጀምሮ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ነበር።

ቅዳሜ ዕለት መግለጫ የሰጡት የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር ፓትሪክ አሞጽ የሕክምና ባለሙያዎቹ ሁለት ወንድ እና አንድ ሴት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የ29፣ 35 እና 32 ዓመት ናቸው የተባሉት የሕክምና ባለሙያዎቹ የመጀመርያውን ታማሚ መስከረም 23 እና መስከረም 24 ካከሙ በኋላ የበሽታው ምልክቶች እንደታየባቸው ተናግረዋል።

እንደ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ የሕክምና ባለሙያዎቹ ከመስከረም 29 ጀምሮም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ነበሩ።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኬንያ አራት አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን የገለጸችው አርብ ዕለት ሦስተኛ በቫይረሱ የተያዘ ግለሰብ ማግኘቷን ባስታወቀች ማግስት ነው።

በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው የ65 ዓመት ሴት ከመጀመርያው ታማሚ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው ናቸው ተብሏል።

ግለሰቧ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ከገቡ በኋላ የበሽታውን ምልክት በማሳየታቸው ምርመራ እንደተደረገላቸው እና በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡ ተገልጿል።

በኬንያ አንድ ግለሰብን የገደለው ኢቦላ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከተከሰተው እና ከ9000 በላይ ሰዎች ከተያዙበት እና ከ4300 በላይ ሰዎች ከሞቱበት ጋር የተገናኘ ነው።

ላለፉት ሰባት ዓመታት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይኖር የነበረው ኬንያዊ በአገሪቱ በኢቦላ የሞተ የመጀመሪያው ሰው ነው።

የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና ክትትል ኃላፊ ጂን ኬስያ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ግለሰቡ የታመመው ከወር በፊት ሲሆን፤ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተለያዩ ሆስፒታሎች ሕክምና ሲሰጠው ነበር።

ሟቹ መጀመሪያ ላይ በመኪና ኡጋንዳ፣ ካምፓላ ገብቶ ወደ ናይሮቢ ደግሞ በአውሮፕላን ገብቷል።

ከግለሰቡ ጋር ግንኙነት የነበራቸው 130 ሰዎች መለየታቸውን የኬንያ ጤና ሚኒስቴር አስታውቆ 128ቱ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ማስቀመጡን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ አክሎም ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበረውን በሙሉ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ማስገባቱን ጠቅሶ፣ ወደ ማኅበረሰቡ ተሰራጭቷል ብሎ እንደማያምን ገልጿል።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተስፋፋው የኢቦላ ዓይነት ክትባት ያልተገኘለት ቡንዲቡግዮ ዝርያ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት አዲስ የተቀሰቀሰውን የኢቦላ ዝርያ የሚከላከል ክትባት ለማግኘት ወራቶችን ሊፈጅ እንደሚችል ገልጿል።

'ቡንዲቡጊዮ' የተባለውን የኢቦላ ዝርያ ለመቆጣጠር ሁለት ክትባቶች በእጩነት የቀረቡ ቢሆንም እስካሁን የትኛውም ክትባት የክሊኒካል ሙከራ እንዳልተካሄደበት የድርጅቱ አማካሪ ዶ/ር ቫሴ ሙርቲ ተናግረዋል፡፡

ኢቦላ እ.አ.አ በ1976 በዛሬዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ከሌሊት ወፎች እንደመጣ ይታመናል፡፡

ለሰዎች በሽታ የሚያመጡ አራት የኢቦላ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተደጋጋሚ የተከሰተው ዝርያ የተለመደው ነው።

አገሪቱ አሁን 17ኛውን የኢቦላ ወረርሽኝ እየተጋፈጠች ሲሆን የቡንዲቡጊዮ ዝርያ በአስርተ ዓመታት ውስጥ ያልታየ እና የራሱን ልዩ እክሎች ያመጣ በሽታ ሆኗል።