በፈረንሳይ በተካሄደ አመጽ የተቀላቀለበት ተቃውሞ ሕንጻዎች ሲቃጠሉ ከ1,000 በላይ ሰዎች ታሰሩ

በፓሪስ አመጽ የተቀላቀለበትን የተቃውሞ ሠልፍ ለመቆጣጠር አድማ በታኝ ፖሊስ ተሰማርቷል
የምስሉ መግለጫ, በፓሪስ አመጽ የተቀላቀለበትን የተቃውሞ ሠልፍ ለመቆጣጠር አድማ በታኝ ፖሊስ ተሰማርቷል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ቅዳሜ ዕለት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለውን ችግር እና የኑሮ ውድነትን በመቃወም በመላው ፈረንሳይ በተካሄደ የተቃውሞ ሠልፍ ወቅት አመጽ ተቀሰቀሰ።

የፈረንሳይ መንግሥት "አመጽ ጨምሮ ታይቶበታል" ሲል በገለጸው ተቃውሞ 550,000 ያህል ሰዎች አደባባይ መውጣታቸው የተገመተ ሲሆን ቢያንስ 1,200 ሰዎች ታስረዋል።

በፓሪስ እስከ ምሽት ድረስ በጸጥታ አካላት እና በሠልፈኞቹ መካከል ከፍተኛ ግጭት የቀጠለ ሲሆን ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ በመተኮስ እና ውሃ በመርጨት ለመቆጣጠር ሞክሯል።

በዋና ከተማው እና በሌሎች አካባቢዎች ሕንፃዎች በእሳት የተያያዙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በሊሞጅስ በከተማው አስተዳደር አዳራሽ የተነሳው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ጣሪያው በከፊል እንዲፈርስ አድርጎታል።

በበርካታ ከተሞች ዘረፋ መከሰቱን ተከትሎ በከተማ አስተዳደር አዳራሾችና በንግድ ድርጅቶች ላይ ያነጣጠረ ሰፊ ውድመት መከሰቱን ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስቲን ሌኮርኑ በተከሰተው ግርግር 150 የፖሊስ አባላት ቆስለዋል ብለዋል።

በፓሪስ የተካሄደው ዋናው ሰልፍ ከሰዓት በኋላ በአብዛኛው ሰላማዊ ሆኖ ታይቷል። አንድ የወጣቶች ቡድን ለቢቢሲ "ነገሮች እንዲለወጡ የሚሞክር"፤ "ሰላማዊ ሠልፈኞች" ነን፤ ነገር ግን "ምንም ነገር እየተለወጠ አይደለም" በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ፣ ቀኑ እየገፋ ሲሄድ አንዳንድ ቡድኖች በጎዳናዎች ላይ እንደ ዴ ላ ሪፐብሊክ ባሉ ታዋቂ የከተማ ቦታዎች ላይ ጨምሮ እሳት በመለኮስ ተሽከርካሪዎችን አቃጥለዋል።

ሱቆች ተዘርፈው ቢያንስ አንድ ምግብ ቤት ሙሉ በሙሉ በእሳት ወድሟል። ቢቢሲ በአንዳንድ ቡድኖች መካከል ግጭት ሲፈጠር ተመልክቷል።

የተቃውሞ ሠልፈኞችን ለመበተን የተሰማሩ ፖሊሶች በማዕከላዊ ፓሪስ ሠልፈኞችን በዱላ ሲመቱ ታይተዋል።

በእሳት የተያያዘውን ምግብ ቤት በስልኩ የሚቀርፍ ተቃዋሚ ሠልፈኛ
የምስሉ መግለጫ, በፓሪስ የሚገኘው ምግብ ቤት ሲቃጠል

የሊዮን ከተማ ከንቲባ ግሬጎሪ ዱሴት የከተማዋን የቱሪስት ቢሮ መቃጠሉን ለቢኤፍኤምቲቪ ተናግረው ክስተቱን "አሳዛኝ" ሲሉ ጠርተውታል።

አክለውም "በጣም ታዋቂ እና ታሪካዊ ሕንፃ ስለሆነ ልባችን ተሰብሯል" ብለዋል።

የአካባቢው ፖሊስ "አመጸኛ የሆኑ ግለሰቦች" የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱን እንዳያጠፉ ከልክለዋል ብሏል።

የእሳት አደጋ ሠራተኞች በሊሞጅስ የከተማ አስተዳደሩ አዳራሽ ላይ የተከሰተውን እሳት መቆጣጠር ችለዋል። የአካባቢው አስተዳደር እንደገለጸው የሕንፃው የተወሰነ ክፍል በአደጋው ምክንያት ፈርሷል።

በደቡብ ምሥራቅ የምትገኘው ሴንት ኤቲን ከንቲባ የሆኑት ሬጊስ ጁዋኒኮ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አንድ ወጣት "እጁን በቦምብ ተመትቶ ተጎድቷል" ሲሉ ጽፈው "እንዲህ አይነት አሳዛኝ ነገር በፍፁም ሊከሰት አይገባም ነበር" ብለዋል።

የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ተቃዋሚ ሠልፈኞቹ በዋና ከተማዋ፣ በማርሴይ፣ ሬኔስ፣ ቱሉዝ እና አንገርስ ውስጥ ባሉ ቦታዎች "ፊታቸውን የሸፈኑ ግለሰቦች " ዒላማ ያደረጓቸው ላይ የአመጽ ድርጊት ፈጽመዋል" ብሏል።

በግሬኖብል፣ አቪኞን፣ ፓው፣ ሞንትፔሊየር እና ቫሌንሲን ጨምሮ በመላው ፈረንሳይ በሕንፃዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተዘግቧል።

በፓሪስ የልብስና የምግብ ሱቆች ተዘርፈዋል፤ በሊል የሚገኝ የአፕል ሱቅ ደግሞ በዘረፋው ባዶውን መቅረቱ ተሰምቷል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ የተመለከተው እና ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው ተንቀሳቃሽ ምስል በግሬኖብል የሚገኝ የቱሪስት ባቡር በከተማው መሃል በሚገኝ ጠባብ ጎዳና ላይ ጭምብል በለበሱ ሰዎች ሲነዳ እና ወደ ሦስት አድማ በታኝ ፖሊሶች ሲሄድ ያሳያል።

በተቀዋሚ ሠልፈኞች በእሳት የተያያዘ መኪና
የምስሉ መግለጫ, ዴ ላ ሪፐብሊክ በተሰኘው አደባባይ የተቃዋሚ ሠልፈኞቹ መኪና በእሳት አቀጣጥለዋል

ባለፉት ሳምንታት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ እና ከ15 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ተማሪዎች በሚማሩባቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለውን የሠራተኞች እጥረት እና የመገልገያዎች እጥረት በተመለከተ ተቃውሞ አሰምተዋል።

ቅዳሜ ዕለት የሠራተኛ ማኅበራት አባላት እና ሌሎች የተቃውሞ ቡድኖች ተቀላቅለዋቸው ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

ፈረንሳይ ለተቃውሞና ለረብሻ እንግዳ ባትሆንም አሁን ግን አገሪቱ ወደ ጥልቅ የፖለቲካ አለመረጋጋት በገባችበት ወቅት የተከሰተ ነው።

በሚቀጥለው ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው የሚያበቃው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የመንግሥት ሕንጻዎችን እና የንግድ ተቋማትን ያወደሙ፣ የዘረፉ አና የከተማ መስተዳድር አዳራሾችን በእሳት የለኮሱ "ክስ ይመሰረትባቸዋል እንዲሁም ይቀጣሉ" ብለዋል።

መንግሥት የተቃውሞ ሠልፈኞች ላነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከረ ሲሆን የትምህርት ሚኒስትሩ ኤዱዋርድ ጄፍሪ ተጨማሪ 3000 መምህራንን ለመቅጠር ቃል ገብተዋል።

ነገር ግን ተቃውሞ ሠልፈኞቹ አደባባይ መውጣታቸውን እና ተቃውሟቸውን ማሰማት አላቆሙም።

ሱቆች ሲዘረፉ
የምስሉ መግለጫ, ቅዳሜ ዕለት በነበረው የተቃውሞ ሠልፍ በፓሪስ እና በሌሎች ከተሞች ሱቆች ተዘርፈዋል