"እዚህ መሬት ላይ መሆን መብቴ ነው"፡ በወይራ ፍሬ ለቀማ ወቅት ጥቃት የደረሰባቸው ፍልስጤማውያን

ፊቱ በደም የተሸፈነው ማጂድ ፋህድ ከመኪኖቹ በአንዱ ውስጥ ነበር
የምስሉ መግለጫ, ፊቱ በደም የተሸፈነው ማጂድ ፋህድ ከመኪኖቹ በአንዱ ውስጥ ነበር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በይዞታ ሥር ባለው ዌስት ባንክ ዓመታዊ የወይራ ፍሬ ለቀማ እየተካሄደ ሳለ ሰፋሪዎች ፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት አድርሰዋል። ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑት ሰፋሪዎች መኪኖችንም አቃጥለዋል።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች አቡ ፋላህ በተባለ መንደር በፍልስጤማውያን ማሳ ላይ የደረሰውን ውድመት ተመልክተዋል።

የአካባቢው ባለሥልጣን አራት ፍልስጤማዊ-አሜሪካውያንን ጨምሮ 12 ፍልስጤማውያን መጎዳታቸውን ተናግረዋል። ከተጎዱት መካከል ጋዜጠኞችም ይገኙበታል።

በዓመታዊው የወይራ ፍሬ ለቀማ ቀን ጠዋት ላይ በደረሰው ጥቃት የተጎዱ ፍልስጤማውያን በመኪና ሲወሰዱ የቢቢሲ ጋዜጠኞች አይተዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ላይ የወይራ ፍሬ መልቀሚያ መገልገያዎች ተጭነውም ነበር።

ፊቱ በደም የተሸፈነው ማጂድ ፋህድ ከመኪኖቹ በአንዱ ውስጥ ነበር።

"የወይራ ፍሬ እየለቀምን ሳለ 15 አይሁዳውያን ጥይት መተኮስ፣ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። ጭንቅላቴ እና አንገቴን መትተውኛል። ደሜን እዩት!" ብሏል።

በቅርብ ርቀት ባለው ቱሙስ አያ መንደር የምክር ቤት አባል የሆነው ያሲር አልካም እንደተናገረው አሜሪካዊው ማጂድ በሰፋሪዎች ጥቃት ደርሶበታል።

ሚስማር በተመታበት ዱላ ጥቃት የደረሰበት ማጂድ ሕክምና እየተደረገለት ነው። በዕድሜ የገፉ እናቱም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የተጎዱ ሰዎችን ሆስፒታል ሲወስድ የነበረ ግለሰብ እንደተናገረው ሰፋሪዎቹ በዱላ ጥቃት አድርሰዋል። ካቃጠሏቸው መኪኖች አንዱም የእሱ ነው።

አብራው የነበረች ሴት "ማሳ ውስጥ ገብተን እቃችንን እንዳስቀመጥን መጡ፤ እኛም ሮጥን" ብላለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃቱ መድረሱን እንደሚያውቅ ገልጿል።

ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑት ሰፋሪዎች ፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት አድርሰዋል
የምስሉ መግለጫ, ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑት ሰፋሪዎች ፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት አድርሰዋል

የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ "በዌስት ባንክ በማንኛውም አካል የሚፈጸም የወንጀል ድርጊት የሆነ ጥቃትን እናወግዛለን። ተጠያቂዎቹ እንዲታሰሩ፣ ምርመራ እንዲደረግ እና እንዲፈረድባቸው እናሳስባለን" ብለዋል።

የ73 ዓመቷ ኢም ካልዶን ምንም ቢፈጠር ወደ መሬታቸው ተመልሰው እንደሚሄዱ ይናገራሉ።

"መሬቱ የኔ ነው። እዚህ መሆን መብቴ ነው" ይላሉ።

አምና የወይራ ፍሬ በሚለቀምበት ወቅት ከነበረው ጥቃት አንጻር የዘንድሮው የከፋ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።

በዌስት ባንክ የወይራ ፍሬ መልቀም ፈታኝ ሆኗል። ሰፋሪዎች ከመነሳታቸው በፊት ንጋት ላይ በፍጥነት የሚለቅሙም አሉ።

ቢቢሲ በተመለከተው አንድ መንደር የወይራ ፍሬ በፍጥነት ለመልቀም የተሰባሰቡ ፍልስጤማውያንን ሰፋሪዎች በቅርብ ርቀት ሲጠብቁ ነበር።

ፍልስጤማውያን በመሰላል ዛፉ ላይ በመውጣት ፍሬውን ቶሎ ለመልቀም ይሞክራሉ። ሦስት መንደሮች አንድ ላይ በመሆን ለቀማውን አከናውነዋል።

በአንደኛው መንደር መሬት ያለው አሚን ካህሊል እንደተናገረው ሰባት ሰፋሪዎች ከብበውት ነበር።

የእስራኤላውያን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት የለውም።

አሚን እንደሚለው አካባቢው ለሰፋሪዎች ጥቃት ከተጋለጡት መካከል ነው።

"እዚህ አካባቢ ሰባት የሰፋሪ መንደሮች አሉ። ዘንድሮ ሁሉም ነዋሪዎች አንድ ላይ የወይራ ፍሬ ለመልቀም ተሰባስበዋል። ጥቂት ሰዎች ብቻ ሲለቅሙ የበለጠ ለሰፋሪዎች ጥቃት ይጋለጣሉ።"

የአካባቢው ነዋሪዎች ቢሰባሰቡም ሰፋሪዎች ጥቁር ለብሰው ከብበዋቸዋል። የወይራ ዘይት ዛፎችን ሲያቃጥሉም ነበር።

ፍልስጤማውያን አርሶ አደሮች በድንጋጤ ሲጮሁ እና ልጆቻቸው ከማሳ እንዲወጡ ሲነግሩ ይሰማል።

በዓመታዊው የወይራ ፍሬ ለቀማ ቀን ጠዋት ላይ በደረሰው ጥቃት የተጎዱ ፍልስጤማውያን በመኪና ሲወሰዱ የቢቢሲ ጋዜጠኞች አይተዋል
የምስሉ መግለጫ, በዓመታዊው የወይራ ፍሬ ለቀማ ቀን ጠዋት ላይ በደረሰው ጥቃት የተጎዱ ፍልስጤማውያን በመኪና ሲወሰዱ የቢቢሲ ጋዜጠኞች ተመልክተዋል
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሰፋሪዎች ፍልስጤማውያኑን ከብበው ድንጋይ ሲወረውሩ ነበር። ፍልስጤማውያን ወጣቶችም ድንጋይ በመወርወር ራሳቸውን ለመከላከል ሞክረዋል።

የእስራኤል ኃይሎች በሥፍራው ሲደርሱ ሰፋሪዎች ወደ አርሶ አደሮቹ እየሮጡ መሄድ ጀምረዋል።

አሜሪካዊው የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ሄይዲ ሌቪን በጥቃቱ ከተጎዱት አንዷ ናት። ዘገባ እየሠራች ሳለ ሰፋሪዎች እንደከበቧት ትናገራለች።

"መሬት ላይ ወድቄ ሲደበድቡኝ ነበር። ካሜራዬ እና ቦርሳዬን ለመያዝ ሞከርኩ። የጭንቅላት ቆብ እና ጥቃት የሚቋቋም ጃኬት ማድረጌ አትርፎኛል። ከመሬት ተነስተሽ ቁሚ ብለው በድጋሚ ይመቱኝ ጀመር። ወደ 10 ደቂቃ ያህል ነው የተመታሁት።"

የዋሽንግተን ፖስት ዋና አርታኢ ማት ሙሪ ጋዜጠኛ መሆኗ በግልጽ እየታወቀ ድብደባው መፈጸሙን ተናግሯል።

"ጋዜጠኛዋ ሥራዋን እያከናወነች ሳለ የደረሰባት ጥቃት አስቆጥቶናል" ብሏል። "ጥልቅ ምርመራ እንዲደረግ እና የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጉዳዩን እንዲከታተሉ እናሳስባለን" ሲል ጠይቋል።

ሰፋሪዎች ጥቃት ሲያደርሱ የሚያሳዩ ቪድዮዎች ቢወጡም እንኳን የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት "እውነታው እንዳልጠራ" ገልጾ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል "ኃይል የተቀላቀለበት ግጭት" መከሰቱ ከተሰማ በኋላ ወታደሮች ወደ አካባቢው መላካቸውን ገልጿል።

ሴት ጋዜጠኛ መጎዳቷን አስታውቆ "ሁሉም የክስተቱ ሁኔታዎች" እንደሚመረመሩ አስታውቋል።

ፍልስጤማውያን አርሶ አደሮች ከአካባቢው ሲሸሹም የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር። የሚተኩሱት ሰፋሪዎቹ ይሁን ወታደሮች ግልጽ አልነበረም።

ከተወሰነ ሰዓት በኋላ የእስራኤል ወታደሮች ወደ ፍልስጤማውያን ማሳ አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል።

አብዛኛውን ጊዜ ግጭት ሲነሳ የእስራኤል ወታደሮች መሰል እርምጃ ይወስዳሉ።

ዘንድሮ በመላው ዌስት ባንክ በወይራ ፍሬ ለቀማ ወቅት በደረሰ ጥቃት እስካሁን አንድ ፍልስጤማዊ ሲገደል፣ 120 ፍልስጤማውያን መጎዳታቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በፍልስጤማውያን የወይራ ዛፍ ማሳ ዙርያ ሕገ ወጥ አይሁዳውያን ይዞታቸውን እያስፋፉ ነው።