በደቡብ አፍሪካ ሕገ ወጥ የማገገሚያ ማዕከል ውስጥ በሰንሰለት የታሰሩ ሕሙማን ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Department of social development
በደቡብ አፍሪካ ሕገ ወጥ የማገገሚያ ማዕከል ውስጥ 200 ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ አንድ ፓስተር እና ባለቤታቸው በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
በሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል በሚገኘው ማዕከል ውስጥ ከነበሩ ሰዎች መካከል በሰንሰለት እግራቸውን የታሰሩ ይገኙበታል።
ምፑማላንጋ ግዛት በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚተዳደረው ማዕከል የተደረሰበት የአካባቢው ባለሥልጣናት ባካሄዱት ኦፕሬሽን ነው።
"አሰቃቂ ኢ-ሰብአዊ ሁኔታ" መመልከታቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
አንዳንዶቹ ሕሙማን "መላው ሰውነታቸው አንዳበጠ" እና ሌሎች ሕሙማን ደግሞ "አንዳቸው ከሌላቸው ጋር በሰንሰለት ታስረው እንደነበር" ተገልጿል።
ማገገሚያ ማዕከሉን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ፓስተር እና ባለቤታቸው፤ ሰዎችን በማገት ተከስሰዋል። ተጨማሪ ክሶችም ሊቀርቡባቸው እንደሚችሉ ተገልጿል።
ጥንዶቹ እስካሁን ድረስ አስተያየት አልሰጡም።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በደቡብ አፍሪካ ሕገ ወጥ ማገገሚያ ማዕከላት እየተበራከቱ መጥተዋል። ለዚህም ምክንያቱ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመር ነው ተብሏል።
አምና የአገሪቱ ማኅበራዊ አገልግሎት መሥሪያ ቤት 100 ሕገ ወጥ ማገገሚያዎችን ማግኘቱን አስታውቋል።
አብዛኞቹ ማዕከላት በጋውቴንግ ግዛት የሚገኙ ናቸው። በዚህ ግዛት ውስጥ የደቡብ አፍሪካዋ ትልቅ ከተማ ጆሃንስበርግ ትገኛለች።
በምፑማላንጋ ግዛት በነበረው ማዕከል የ16 ዓመት ሴት እና የ11 ዓመት ወንድ በዕድሜ ከሚበልጧቸው አዋቂዎች ጋር አንድ ክፍል ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጓል።
ማዕከሉን የሚያስተዳድሩት ጥንዶች 60 ሰዎች እንደሚኖሩ ቢናገሩም ፍተሻ ሲደረግ ወደ 200 ሰዎች ተገኝተዋል። ከእነዚህ መካከል ከ30 በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
አብዛኞቹ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ እንደሆኑ ይታመናል። በማዕከሉ በአግባቡ አገልግሎት የሚሰጥ መጸዳጃ ቤት እና ውሃም የለም።

የፎቶው ባለመብት, South Africa Police Service
የደቡብ አፍሪካ ማኅበራዊ አገልግሎት መሥሪያ ቤት "አንዳንዶቹ በዚህ ሕገ ወጥ ማቆያ ለተወሰነ ጊዜ ቆይተዋል" ብሏል።
በማዕከሉ ተይዘው ከነበሩ አንዱ የሆነው ጊፍት ስኮሳና 'ኒውዝሩም አፍሪካ' ለተባለው የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገረው ሕሙማንን በሰንሰለት ማሰር "የተለመደ አሠራር" ነው።
"ወደ ማዕከሉ ስንገባ እንዲሁም ሊቀጡን ሲፈልጉ በሰንሰለት ያስሩናል" ብሏል።
ሆኖም ግን ማዕከሉ ውስጥ በመቆየቱ ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስ መላቀቁን ተናግሯል።
ሌላ በማገገሚያው የነበረ ግለሰብ በበኩሉ ቆይታው ለአእምሮ ሕመም እንደዳረገው ገልጿል።
ጥንዶቹ በወር 3,000 ራንድ (182 ዶላር) ያስከፍሉ ነበር። ግማሹ ገንዘብም ለቤተ ክርስቲያን ገቢ ይደረጋል።
በማገገሚያው ከተገኙ ሰዎች 14 ያህሉ ለሕክምና ሆስፒታል መወሰዳቸውን ፖሊስ አስታውቋል። 132 ሰዎች ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል።
ጥንዶቹ በቀጣይ ሳምንት ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።



































