በበርሊን ማራቶን ጉዳት ስላጋጠማት አትሌት ትዕግሥት አሰፋ አሰልጣኟ ምን አሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እሁድ ዕለት በጀርመን በርሊን በተካሄደው የማራቶን ውድድር ላይ ስትሳተፍ ከባድ ጉዳት ያጋጠማት አትሌት ትዕግስት አሰፋ የቀዶ ሕክምና ተደርጎላታል።
ቢቢሲ ያነጋራቸው አሰልጣኟ ገመዶ ደደፎ በውድድሩ የዓለም ክብረ ወሰንን ለማሻሻል በማለም እየሮጠች በነበረበት ወቅት በቀኝ እግሯ ጅማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳጋጠማት ተናግረዋል።
አትሌት ትዕግሥት የበርሊን ማራቶንን ለሦስተኛ ጊዜ 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ04 ሰከንድ በመግባት አጠናቅቃለች።
በውድድሩ አትሌት ትዕግስት በሩት ቼፕንጌቲች የተያዘውን የዓለም ክብረ ወሰን ለማስመለስ አቅዳ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ኪሎ ሜትሮች ባጋጠማት የጅማት መጎዳት ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።
ከውድድሩ በኋላም በጀርመን የቀዶ ሕክምና ተደርጎላታል።
ቢቢሲ አማርኛ ለአሰልጣኟ ገመዶ ደደፎ ትዕግሥት ስላለችበት ሁኔታ ጥያቄ አቅርቦ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ "ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ" እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ቢቢሲ አማርኛ ፡ ጉዳቱ ለረዥም ጊዜ ከውድድር ያርቃታል?
አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ፡ አሁን የምንወስንበት ሰዓት ላይ አይደለንም። መጀመርያ እርሷ የምትወስዳቸው በርካታ 'ፕሮሲጀሮች' አሉ። እርሷ የምትከተላቸው እንቅስቃሴዎች አሉ፤ አሁን ዶክተሮች ከቀዶ ሕክምናው በኋላ የሚሰጧት። አሁን እነርሱን 'ፕሮሲጀሮች' ከተከተለች በኋላ ጥሩ ሁኔታ ላይ የሚመጣ ከሆነ ቀጣይ ወደ ሥራሽ ግቢ ይሏታል። እነርሱ እስከ ሦስት ወር ድረስ ጥሩ ለመንቀሳቀስ፣ ወደ በፊቱ የልምምድ ፕሮግራም፣ ወደ ሩጫው ለመግባት እና ጥሩ ለመንቀሳቀስ እስከ ሦስት ወር ሊፈጅ ይችላል ነው የሚሉት። ነገር ግን የሚወሰነው በዚህ ስድስት ሳምንታት ውስጥ በምታሳየው ለውጥ ይሆናል።
ቢቢሲ አማርኛ ፡ ወደ ውድድር ከመግባቷ በፊት ጉዳት ነበራት? ወይስ በውድድር ውስጥ ሳለች ነው ጉዳቱ ያጋጠማት?
አሰልጣኝ ገመዶ ፡ የጉዳት ስሜት አልነበራትም፤ ግን ከዚህ በፊት እንዲሁ አኪሌሷን [የእግሯን ጅማት] ያማት ነበር። የሚያማት አኪሌስ ግን እንዲህ እዚህ ደረጃ ይደርሳል ተብሎ አልተጠበቀም። ይህ የተከሰተው ውድድሩ ላይ ነው።
ቢቢሲ አማርኛ ፡ ጉዳት እያለባትም ግን በጣም ጥሩ ውጤት ነው ያስመዘገበችው። የዓለም ክብረ ወሰንን ባለመስበሯ ስሜቷ ምን ነበር?
አሰልጣኝ ገመዶ ፡ ይህንን የዓለም ክብረወሰን በእጇ ለማስገባት ብዙ ልምምድ አድርጋለች። ጥሩ ዝግጅትም አድርጋለች። እና ለሁለት ዓመት ያህል የተዘጋጀችበት ውድድር ስለሆነ፣ ሌሎቹን ውድድሮችም ስታደርግ የነበረው ይህንን ለማሳካት ነበር። ረዥም ጊዜ ከተዘጋጀህ በኋላ [እንዲህ ዓይነት ነገር ሲፈጠር] ይከፋሃል።
ቢቢሲ አማርኛ ፡ ውድ ሆስፒታል እየታከመች ነው። ከአንድም ሁለት ሆስፒታል እየተመላለሰች እየታከመች መሆኑን ሰምተናል። የሕክምና ወጪዋን ማን ነው የሚሸፍነው?
አሰልጣኝ ገመዶ ፡ እስካሁን ኢንሹራንስ አላገኘንም። ሕክምናዋን የምትከታተለውም በግሏ አይደለም። እንደ አጋጣሚ ሆኖ አዲዳስ ልክ ጉዳት ባጋጠማት ቅጽበት እንዳይጠናባት በሚል በሂሊኮፕተር ነበር መጥቶ ሆስፒታል ያደረሳት። አሁንም ድረስ ሁሉንም የሕክምና ወጪ ኩባንያው እየሸፈነ ይገኛል። እንደውም የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ በየጊዜው እየደወለ የጤንነት ሁኔታዋን እየጠየቀ ነበር።
ቢቢሲ አማርኛ ፡ ይህ ስምምነታችሁ ላይ ነበር?
አሰልጣኝ ገመዶ ፡ የለም። በራሳቸው ተነሳሽነት ነው ይህንን የሚያደርጉት።

የፎቶው ባለመብት, Gemedu Dedefo
ቢቢሲ አማርኛ ፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አትሌት ትዕግሥት አሰፋ በተለያዩ ውድድሮች ውጤታማ ስትሆን አይተናል። ይህንን ስኬቷን ያመጣው ምንድን ነው ይላሉ?
አሰልጣኝ ገመዶ ፡ ትዕግሥት በጣም ታታሪ አትሌት ናት። ራሷ ትምህርት ቤት ማለት ናት። ስለራሷ ጥንቅቅ አድርጋ ስለምታውቅ፣ ስለ ሥራዋ በሚገባ ስለምታውቅ፣ እያንዳንዱን ነገር በጥንቃቄ ነው የምትጓዘው። የተባለችውን ደግሞ ታደርጋለች። ይህ ነው ለዚህ ሊያበቃት የቻለው።
ቢቢሲ አማርኛ፡ በቅርብ ጊዜ በተከታታይ ወድድሮች ላይ ስትሳተፍ ነበር። ለጉዳቱ መንስዔ የሆነው የውድድር መደራረብ ይሆን?
አሰልጣኝ ገመዶ ፡ የውድድር መደራረብ ነው ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ከሦስት እና አራት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ያስሮጥናት ማራቶን ውድድር የለም። ሳይንሱ የሚለውን ነገር በተቻለ መጠን ጠብቀን ነው በውድድር ላይ የምናሳትፋት።
ቢቢሲ አማርኛ ፡ ከፍተኛ ስም ያላቸው ውድድሮች ላይ ትሳተፋለች። በእርስዎ በኩል ደግሞ የስልጠና ፍላጎቶች ይኖራሉ። የረጅም ጊዜ የስፖርት ሕይወቷን የመጠበቅ ጉዳዮችን ሚዛን እንዴት እየጠበቃችሁ ነው?
አሰልጣኝ ገመዶ ፡ ትዕግሥት ጠንካራ ወድድሮችን ስትሳተፍ ተፎካካሪዎቿም እንዲሁ ጠንካራ ናቸው። የምትወዳደርባቸው ውድድሮችም እንዲሁ ወሳኝ ናቸው። ለዚህኛው ውድድር ስናደርግ የነበረው ከሰውነቷ ጋር የሚደረግ ውድድር ነው ማለት ይቻላል። ለምን ሌሎች ተፎካካሪዎች ያሸንፉኛል ሳይሆን ምን ያህል መሮጥ እችላለሁ? ምን ያህል ውጤታማ ነኝ ለዚህ? ምን ያህል የዓለም ክብረ ወሰንን ማሻሻል እችላለሁ? የሚለውን ለማሳየት እና ከዚህ በፊት ሴት ልጅ ከዘጠኝ፣ ከስምንት በታች [በ2 ሰዓት 08 ደቂቃ] መሮጥ ትችላለች ብለን ግምት ሰጥተን ነበር እና ያንን ለማሳካት ትልቅ ጉጉት ነበራት። ግን በደረሰባት ጉዳት ያንን ሳታሳካ ቀርታለች። እንግዲህ ያንን ወደፊት ጤንነቷ ከለተመለሰ መሞከሯ የማይቀር ነው።
ቢቢሲ አማርኛ ፡ ትግስት ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስባለች። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ጫና፣ የሚዲያ ፍላጎት እና የሚጠበቁ ነገሮችን እንዴት እያስተናገዱ ነው?
አሰልጣኝ ገመዶ ፡ የመጀመርያው የእኛ ትኩረት ሥራችን ነው። እኛ ለሚዲያ ጆሮ ሰጥተን፣ ለሚዲያ ትኩረት ሰጥተን ራሳችንን ለማስተዋወቅ ያደረግንበት ቀን የለም። ትዕግሥትም ያንን አታደርግም። የሥልጠና ጊዜ ልምምድ ነው። ትኩረቷን ማጣት አትፈልግም። በዚህ ረገድ የሚያስጨንቀን ነገር አለ ብዬ መናገር አልችልም።
ቢቢሲ አማርኛ ፡ የትግስት ቀጣይ የ12 ወራት ዋና ዋና ግቦች ምንድን ናቸው? እንዲሁም የትኞቹ ውድድሮች ለእሷ በጣም አስፈላጊ ናቸው?
አሰልጣኝ ገመዶ ፡ ለእርሷ በጣም አስፈላጊ ነው ብለን የምንጠብቀው ሚያዚያ ላይ የሚደረገው የለንደን ማራቶን ነበር። እርሱን እሮጣለሁ ብላ አቅዳ ነበር። ፕሮግራሟም እርሱ ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ የዓለም ዋንጫ ነበር። ግን ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ዛሬ ላይ ቆሜ መናገር አልችልም። የትናንቱን ዕቅዳችንን ነው እንጂ አሁን ከጉዳቱ በኋላ ያለውን መገመት አልችልም።
ቢቢሲ አማርኛ ፡ ትዕግሥትን በአጭር ቃል ቢገልጿት ምን ይላሉ?
አሰልጣኝ ገመዶ ፡ በጣም ጠንካራ አትሌት እና እልኸኛ ቆራጥ ሠራተኛ ናት።



































