ጋዜጠኛው ከመራር ክርክር በኋላ በኡጋንዳ ንጉሥ ሆነው ዘውድ ሊጭኑ ነው

የፎቶው ባለመብት, Ngabo Amon/BBC
በኡጋንዳ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ውስጥ ጋዜጠኛ እና አቅራቢ በመሆን የሚታወቁት የ56 ዓመቱ፣ ልዑል ኤድዋርድ ሩኪዲ ኪጃናንጎማ ኒያቦንጎ ሁለተኛ፣ ከአገሪቱ አራት ዋና ዋና ታሪካዊ መንግሥታት አንዱ በሆነው የቶሮ መንግሥት አዲስ ንጉሥ ሆነው ዘውድ ሊጭኑ ነው።
በሦስት ዓመታቸው ወደ ዙፋን መጥተው ለ31 ዓመታት የመሩት ንጉሥ ኦዮ ኒይምባ ካባምባ እጉሩ ሩኪዲ አራተኛ ፣ በ34 ዓመታቸው በካንሰር ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ የተካሄደው የንግሥና ውርስ ሂደት ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቷል።
በባህሉ መሠረት የሟቹ ንጉሥ የታወቀ ልጅ እሱን መተካት ያለበት ሲሆን፣ ይህ ባለመሆኑ ነው ውዝግቡ የተነሳው።
የንጉሣዊ ቤተሰቡ ቅርብ አባላት እንደሚሉት ኦዮ አንድ ትንሽ ልጅ የነበረው ሲሆን ሕጻኑ ቀጣዩ ንጉሥ እንዲሆን የሚያዝ ኑዛዜም ትቶ አልፏል።
ነገር ግን ልጁ በይፋ ለሕዝብ ታይቶ የማያውቅ ከመሆኑም በላይ፣ ንጉሡን የመረጡትና በመጨረሻም ኪጃናንጎማን የሰየሙት የ21 አባላት ያሉት የባቢቶ ጎሣ ኮሚቴ አላወቀውም።
ሟቹ ንጉሥ ኦዮ በይፋ ተሞሽረው አያውቁም፤ ስለ ባለቤታቸውም ሆነ ስለ ልጃቸው የሚታወቅ ነገር ጥቂት ነው ተብሏል።
ሆኖም እናታቸው ንግሥት ቤስት ኬሚጊሳ የሟቹ ንጉሥ ኑዛዜ መከበር ነበረበት ሲሉ ይከራከራሉ።
ንግሥት ቤስት "የመጣው ንጉሥ የንግሥና ሥርዓት የተከበረው የልጄ አስከሬን ከተቀበረበት በትንሽ ሜትሮች ርቀት ነው" ሲሉም ድርጊቱን "መራራና የሚያም" ብለውታል።
ነገር ግን ንግሥናውን የሚተካው ኮሚቴው የቶሮን ባህልና ወግ መሠረት በማድረግ መምረጡን በመግለጽ የንግሥቲቱን ፍላጎት ውድቅ አድርጎታል።
ከቤተ-መንግሥቱ ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ንጉሥ መሆን የሚቻለው ከባቢቶ ጎሣ፣ በተለይም ከንጉሥ ጆርጅ ዴቪድ ማቲው ካሙራሲ ሩኪዲ ሦስተኛ የዘር ሐረግ ብቻ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Ngabo Amon/ BBC
ኪጃናንጎማ እና ሟቹ ንጉሥ ኦዮ የአክስት እና የአጎት ልጆች ሲሆኑ ሁለቱም እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ1928 እስከ 1965 የቶሮን መንግሥት ያስተዳደሩት የ11ኛው ንጉሥ የሩኪዲ ሦስተኛ (ኦሙካማ) የልጅ ልጆች ናቸው።
ሌላው ለቦታው ታጭቶ የነበረው በእንግሊዝ አማተር ክለብ ውስጥ የሚጫወተው ልዑል ጆርጅ ዴስሞንድ ካሙራሲ ጥሪውን ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
በፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ የሚመራው የኡጋንዳ መንግሥትና የጦር ኃይሎች አዛዡ ሙሁዚ ካይነሩጋባ የኪጃናንጎማን መመረጥ ደግፈዋል።
በኪጃናንጎማ ላይ የቀረበ ሕጋዊ አቤቱታ ባለመኖሩ የዘውድ መጫኑ ሥነ ሥርዓት እንዲቀጥል ፈቃድ ተሰጥቷል።
ምንም እንኳን የኡጋንዳ ባህላዊ ነገሥታት መደበኛ የፖለቲካ ሥልጣን ባይኖራቸውም፣ ከፍተኛ ባህላዊ ተፅዕኖ አላቸው።
በ1960ዎቹ ተሽረው የነበሩት እነዚህ መንግሥታት በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ሲባል እንዲያንሰራሩ ተደርገዋል።
ከማከረሬ ዩኒቨርሲቲ በማስ ኮሙዩኒኬሽን የተመረቁት ኪጃናንጎማ፣ በ21 ዓመታት የሚዲያ የሥራ ዘመናቸው ያፈሩትን ሰፊ የሕዝብ ግንኙነት በመጠቀም፣ ትኩረታቸውን በአንድነትና በልማት ላይ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
እናታቸው አሲምዌ ዩስታ ልጃቸው በጥንታዊ የንግሥና ባህልና ተግሣፅ ያደገ በመሆኑ ለኃላፊነቱ ብቁ መሆኑን ገልጸዋል።


































