ተቋርጦ የነበረው የኮምቦልቻ በረራ ቢጀመርም በላሊበላ በረራ አለመኖሩን ነዋሪዎች ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዛሬ መስከረም 18፣ 2019 ዓ. ም. ወደ ኮምቦልቻ የሚደረግ በረራ ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም ከሰዓት 8 ሰዓት አካባቢ ዳግመኛ መጀመሩን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ።
ሆኖም ግን ከባለፈው ሳምንት አንስቶ በላሊበላ የተቋረጠው በረራ እስከ ዛሬ ድረስ አለመጀመሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ቢቢሲ ዛሬ ጠዋት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ወደ ኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያ "መግባት እንደማይቻል" ተናግረው ነበር።
ቢቢሲ ከአየር መንገዱ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ምላሽ የጠየቀ ሲሆን "በማኅበራዊ ገጻችን መረጃ እንሰጣለን" ሲሉ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
እስካሁን ድረስ ከአየር መንገዱ በኩል የተሰጠ መግለጫም የለም።
ባለፈው ሳምንት የህወሓት ታጣቂዎች በክልሉ የሚገኙ ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ በረራዎች "ላልተወሰነ ጊዜ" መቋረጣቸው ተገልጿል።
የኮምቦልቻ ነዋሪዎቹ ለበረራው መቋረጥ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በውል እንደማያውቁ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሁለት የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች እስከ ዛሬ ድረስ በረራ አለመጀመሩን ተናግረዋል።
በከተማዋ ምንም ዓይነት ግጭት አለመኖሩን የተናገሩት አንድ ነዋሪ በላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ "በርከት ያሉ የፀጥታ አባላት እንደሚገኙ" ገልጸዋል።
በረራ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በመቋረጡ ታሪካዊቷን ላሊበላ ለመጎብኘት የሄዱ "ከ50 በላይ የውጭ አገር ዜጎች" ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ መቸገራቸውን ጨምረው አስታውቀዋል።
በተለያዩ አስጎብኚዎች አማካኝነት ወደ ላሊበላ ከሄዱት የውጭ አገራት ዜጎች መካከል አብዛኞቹ አሜሪካውያን እና እስራኤላውያን መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የላሊበላ ነዋሪ ከባለፈው ሳምንት አንስቶ እስከዛሬ ድረስ የአውሮፕላን በረራ እንደተቋረጠ ገልጸዋል። የተሽከርካሪዎች ጉዞም እንደሌለ ጨምረው አብራርተዋል።
"አሁን የሚሰማ ነገር የለም። ፀጥ ያለ ነው። ከትናንት ጀምሮ ተኩስም አይሰማም። ትናንት ጠዋት ከባድ መሣሪያ ተተኩሶ ነበር። አሁን ከተማው ሰላም ነው" ብለዋል።
ምንም እንኳን አሁን ድባቡ "ፀጥ ረጭ ያለ" መሆኑን ቢገልጹም "በጦርነት በምን ደቂቃ ምን እንደሚፈጠር ስለማይታወቅ ስጋቱ አለ" ሲሉ ያሉበትን ፍርሃት ገልጸዋል።
ወደ ላሊበላ የተሽከርካሪዎች ጉዞ እንደሌለ እኚሁ ነዋሪ አክለዋል።
"በቅርቡ ከባሕር ዳር ወደዚህ የሚመጣ አስከሬን በሰው [ሸክም] ነው ወደዚህ የገባው። አስከሬኑን ከዚያ ባጃጅ ተቀብሎ ነው መምጣት የቻለው" ሲሉም በከተማይቱ ያለውን ሁኔታ ለቢቢሲ አብራርተዋል።
ከመስከረም 13፣ 2019 ዓ. ም. ጀምሮ መብራት እንደተቋረጠ እና የሸቀጥ ዋጋ እንደናረም አክለዋል።
"ዘይት 2 ሺህ ብር ነበር። አሁን 2500 ብር ገባ። ኦሞ ከ30 ብር 70 ብር ገብቷል። ሁሉም ነገር እየጨመረ ነው።"
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግመኛ መቀስቀሱን ተከትሎ ንግድ ባንክ ብዙም ሳይቆይ አገልግሎት እንዳቋረጠ እና ሌሎች ባንኮች "እስከ 5 ሺህ ብር" እየሰጡ ቆይተው አሁን ላይ ምንም ገንዘብ ማውጣት እንደማይቻል ተናግረዋል።
"አሁን ሁሉም ባንክ አቁሟል። ሰውም ሞባይል ባንኪንግ ነው የሚጠቀመው" ብለዋል።
ቢቢሲ ከአካባቢው ባለሥልጣናት እና ከባንኩ ቅርንጫፍ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የላሊበላ ነዋሪ እንደገለጹት ትናንት የመስቀል በዓል በሰላም የተከበረ ሲሆን ዛሬም እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ የተረጋጋ ድባብ ይስተዋላል።
ነገር ግን ከትናንት በፊት በነበሩት ሦስት ቀናት የነበረው ሁኔታ "በጣም አስከፊ ነበር" ሲሉ ገልጸዋል።
"ላሊበላ ውስጥ የትኛውም አካባቢ ሆነን ከፍተኛ ንዝረት ያለው አስደንጋጭ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ነበር የምንሰማው። ጦርነቱ ላሊበላ ውስጥ ሳይሆን ከከተማው ውጭ ነበር።"
ትናንት እና ዛሬ ሰላም ቢሆንም ምን ያህል ይቀጥላል የሚለውን አለማወቅ የፈጠረባቸውን ስጋት አብራርተዋል።
ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገረው የአስጎብኚዎች ማኅበር አባል እና ለአሥርታት በቱሪዝም ዘርፍ የሠራው ባለሙያ እንደሚለው፤ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በረራ አልተጀመረም።
ወደ ላሊበላ ለመጓዝ አቅደው የነበሩ ቱሪስቶች ባለፉት ቀናት የሆቴል እና የጉብኝት ዕቅዶችን "እስከ ኅዳር ድረስ" መሰረዛቸውን ተናግረዋል።
ወደ ከተማው ለጉብኝት የሄዱ "ወደ 40 የሚጠጉ" ቱሪስቶችን በመኪና ወደ ኮምቦልቻ መላካቸውን ገልጸዋል።
"የፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ፖላንድ፣ እስራኤል ዜጎች ይገኙበታል።ትናንት የተወሰኑትን፣ ዛሬ የተወሰኑት ወደ ኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያ መኪና አፈላልገን ልከናል። ከኮምቦቻ አዲስ አበባ እንዲሄዱ" ብለዋል።
ነዋሪው አክለውም "ሁሉም ባንክ ብር የለም። ከአራት ቀን ጀምሮ ብር እየሸሸ ነው ስለተባለ እና በባንክ የሚሰጠው ብር ትንሽ ስለነበር ፍርሃት ፈጥሯል" ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።
"ዋናው ጦርነት ይጎዳናል የምጣኔ ሃብት ጦርነትም ይጎዳባል። ሁሉም ሸቀጥ የለም ይባላል፤ በአንድ ጀንበር የሸቀጥ ዋጋ ይንራል" ሲሉም ተናግረዋል።
አሁን ላይ በከተማው "ኮሽታ የለም" ቢሉም በቀጣይ ግን ምን እንደሚፈጠር አለማወቃቸውን ጠቅሰዋል።
"ላለፉት 5 አመታት ከጦርነት ድባብ አልወጣንም። ያለፈውንም ጦርነት ያየሁ ሰው ነኝ። ተስፋ ሳልቆርጥ ሰላም ይሆናል የምል ሰው ብሆንም ሰላም ነው ስንለው የሚያገረሽ ሆኗል። ዝም ብለን በደመ ነፍስ እየኖርን ነው። ነገን አቅዶ መኖርም አይቻልም።"
በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን፤ በአማራ እና አፋር ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆኑም ተዘግቧል።
በትግራይ የኢትዮ ቴሌኮም የስልክ እና የኢንተርኔት መስመር የተቋረጠ ሲሆን ይህም በሸቀጦች ግብይት እና በገንዘብ ዝውውር ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።


































