"ቤት የለኝም፤ ፍራሽ የለኝም፤ ቤተሰብ የለኝም"- ተባብሶ የቀጠለው የየመን ውጊያ

የፎቶው ባለመብት, Liam Weir/BBC News
በደቡብ ምዕራብ የመን አብሮን የነበረው ወታደር "ይሄ የመጀመሪያው ድሮን ነው፤ ብዙውን ጊዜ ተከትሎ የሚመጣው ሌላ ጥቃት ነው" ሲል ሁኔታውን ይገልጻል።
ከላይ የሚሰማው ድምጽ እየጨመረ ሲመጣ ጫካ ውስጥ ተደበቅን። ከዚያም መኪና ውስጥ ገብተን ከአካባቢው ወጣን።
ከ10 ደቂቃ በኋላ ጥቃቶች ይፈጸሙ ጀመር። ከፍተኛ ድምጽ ያስተጋባል። ድሮኑ የትኛው ቦታ እንደወደቀ ግልጽ አልነበረም።
በደቡብ ምዕራብ በምትገኘው ታይዝ ከተማ የውጊያ አውድማውን መጀመሪያ እና ማቆሚያ ለመለየት ያስቸግራል።
በሳዑዲ አረቢያ የሚደገፉት የመንግሥት ኃይሎች የሁቲ አማጺያንን ገፍተው ለማስወጣት እየታገሉ ነው።
የሁቲ አማጺያን በያዝነው ወር መባቻ በቀይ ባሕር በኩል አድርገው ቁልፍ መተላለፊያ መስመሮች እየያዙ ነው። በዚህም ምክንያት የእርስ በርስ ጦርነቱ ተባብሷል።
ከመንግሥት ኃይሎች ጋር በመሆን ከታይዝ አንስተን የተለያዩ የፍተሻ ጣቢያዎችን እያለፍን ተጉዘናል። ጉዞው የመንግሥት ኃይሎች በሚቆጣጠሩት አካባቢ ውስጥ ሲሆን ከዚያ ውጭ ባለው ሥፍራ ውጊያዎች ይካሄዳሉ።
ቤቶች በየቦታው ተበታትነው ይታያሉ። በርካቶች ውጊያውን በመሸሽ መኖሪያቸውን ጥለው ስለወጡ ቤቶቹ ኦና ሆነዋል።

የፎቶው ባለመብት, Liam Weir/BBC
በከተማው የሚንቀሳቀሱ መኪኖች እና ሞተር ሳይክሎችም ስለሌሉ ፀጥታ ነግሷል።
ብቸኛው የሚሰማው ድምጽ የቀንድ ከብቶች እና የፍንዳታ ነው።
አሊ ቤቱ በር ላይ ተምጦ ፍየሎች ይጠብቃል። "ትናንት ሁለት ሞርታር በአቅራቢያዬ ወድቋል" ይላል።
ልጆቹ የሚሰማውን የተኩስ ድምጽ መቋቋም ስላቃታቸው ወደ ተፈናቃዮች መጠለያ ልኳቸዋል።
ከብቶችን ለመጠበቅ ሲሉ ከባለቤቱ እና እህቶቹ ጋር ሆነው ቤታቸው ቀርተዋል።
"ደክሞኛል፤ ግን ምርጫ የለኝም። እንሰሳቱ ከሌሉ ሁላችንም በረሃብ እንሞታለን" ይላል።
አሊ ሁቲዎች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ አደጋ እንደሚያደርሱበት በመስጋት የአባቱን ስም አልተናገረም።
የሁቲ አማጺያን እንደተናገሩት ሠራዊታቸውን አሰባስበው ከፍተኛ ጥቃት ለመሰንዘር ተዘጋጅተዋል።
የመንግሥት ኃይሎችም መረጃው እንዳላቸው እና እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ወደ ውጊያ አውድማው በቀረቡ የፍተሻ ጣቢያዎች ያገኘናቸው ተዋጊዎች በቅርቡ ከተራራማ ሥፍራዎች የተመለሱ ናቸው።
በ100 ሜትሮች ርቀት ውስጥ ሁቲዎች እየቀረቡ መጥተዋል። ከተዋጊዎቹ አንዱ እንደሚናገረው 18 የመንግሥት ኃይል አባል የሆኑ ሰዎች አስከሬናቸው ወድቋል። በተኩስ ልውውጡ መካከል የሰዎቹን አስከሬን ማንሳትም አልቻሉም።
ሁቲዎች ቁልፍ የሆነውን የቀይ ባሕር ዳርቻ ሞክሀ ከተማ መያዛቸውን ተከትሎ በታይዝ ከተማ የሚደረገው ውጊያ ተባብሷል።
ሞክሀ ከከተማው በስተምዕራብ 85 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
ላለፉት አራት ዓመታት የነበረው የተኩስ አቁም ተጥሷል።

የፎቶው ባለመብት, Liam Weir/BBC News
ቡድኑ ስትራቴጂያዊ የሆነውን ባል ኤል-መንደብ ወሽመጥ ለማየት የሚያስችለውን ሥፍራ ተቆጣጥሯል። ይህ ቁልፍ የሆነው ወሽመጥ አውሮፓ እና እስያን የሚያገናኝ የመርከቦች መተላለፊያ መስመር ነው።
በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ቀጣናው የበለጠ ቀውስ ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚል ስጋትም ተፈጥሯል።
ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች ያሏት ታይዝ የየመን ሦስተኛ ትልቅ ከተማ እና የባህል መዲና ናት።
በስተሰሜን በሁቲዎች ቁጥጥር ሥር በሚገኙ አካባቢዎች እና በስተደቡብ በመንግሥት ኃይል ሥር በሚገኙ ሥፍራዎች መካከል ናት።
የመንግሥት ኃይሎች ማዕከላዊ ታይዝን ሲይዙ ሁቲዎች በሰሜን እና ምሥራቅ አቅጣጫ ኃይላቸውን አሰማርተዋል።
ከፍተኛ ውጊያ የተካሄደው በምዕራብ አቅጣጫ ነው። ሁለቱም ቡድኖች በከተማዋ ደቡባዊ መውጫ ያለውን ተራራማ ሥፍራ ለመያዝ ይዋጋሉ።
የመንግሥት ኃይሎች ሞክሀ ከተማን መልሰው መቆጣጠር አልቻሉም።
ከተማዋን ከከበበው ተራራ በተደጋጋሚ የተኩስ ድምጽ ይሰማል።
ታይዝ በአውዳሚው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የውጊያ ማዕከል ሆናለች።
በአውሮፓውያኑ 2015 የሰንዓውን መንግሥት ያስወገዱት ሁቲዎች፤ ታይዝን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሞክረዋል።
ሆኖም ግን በታጣቂዎች አማካኝነት ሁቲዎች ከአብዛኛው የከተማዋ ክፍል ለቅቀው ወጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Liam Weir/BBC
ወደ ታይዝ የተጓዝነው ከደቡባዊቷ ኤደን ነው። በዚህም ዓለም አቀፍ ዕውቅና የተሰጠው የየመን ፕሬዝዳንታዊ አመራር ምክር ቤት እና መንግሥት ይገኛል።
በመንገዱ ላይ የሚገኙት ወደ 30 የሚደርሱ የፍተሻ ጣቢያዎች በተለያዩ ኮማንደሮች ቁጥጥር ሥር ናቸው።
ይህም በመንግሥት በኩል የሚዋጉ ኃይሎች መካከል ያለውን ክፍፍል ያሳያል።
ወደ ከተማዋ ስንቃረብ አምቡላንሶች ማለፍ ጀመሩ። በግማሽ ሰዓት ውስጥ ወደ ታይዝ ዋነኛ ሆስፒታል የሚጓዙ ቢያንስ አምስት አምቡላንሶች አልፈዋል።
በከተማዋ ማዕከል ውጊያው ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል።
የደረስነው ከመሸ በኋላ ቢሆንም የመደብሮች መብራት አልጠፋም። ሬስቶራንቶች በሰዎች ተሞልተው፣ መንገድ ላይ ልጆች ይጫወታሉ።
አሁን በተቀሰቀሰው ግጭት ሁቲዎች ከሌሎች የጦር መሣሪያዎች በተጨማሪ በስፋት ድሮን እየተጠቀሙ ነው።
ሳዑዲ፣ ምዕራባውያን አገራት እና የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች እንደሚሉት ዋነኛ የጦር መሣሪያ፣ የገንዝብ ድጋፍ እና ወታደራዊ ምክር አቅራቢ ኢራን ናት።
ኢራን ግን ሁቲዎችን በጦር መሣሪያ እንደማትደግፍ አስታውቃለች። ለአማጺያኑ ፖለቲካዊ ድጋፍ እንዳላት ግን አልካደችም።
ሁቲዎች ሕጻናት ወታደሮችን እየመለመሉ ነው የሚለው ክስ ለዓመታት ሲቀርብ ቆይቷል። አንድ የመንግሥት ወታደር በጦር ግንባር እንዳያቸውም ተናግሯል።
"የመናዊ ልጅን አይቶ እሱ ላይ መተኮስ ከባድ ነው። ግን እነሱም ጥይት አቀባብለዋል። ራሳችንን መከላከል አለብን" ሲል ገልጿል።
በ2022 ሁቲዎች ከተመድ ጋር በተፈራረሙት ስምምነት ልጆችን በውትድርና ማሰለፍን ለማቆም ቃል ገብተዋል።
ቢቢሲ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የተሰለፉ ታዳጊዎችንም አነጋግሯል።
ሳዑዲ የምትመራው እና የየመን መንግሥትን የሚደግፈው ጥምረት መሣሪያም ጭምር ያቀርባል።

የፎቶው ባለመብት, Liam Weir/BBC
የሳዑዲ ጦር በቀይ ባሕር ዳርቻ በሁቲ ይዞታዎች ላይ በማነጣጠር በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቃቶችን አድርሷል።
ሁቲዎች በደቡብ ምዕራብ ሳዑዲ በከተሞች እና መሠረተ ልማቶች ላይ የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃቶች ፈጽመዋል።
ታይዝ ወደሚገኘው አል-ታህውራ ሆስፒታል በውጊያ የተጎዱ ሰዎች ይጎርፋሉ። የጽኑ ሕሙማን ማቆያው ውስጥ ያሉ አልጋዎች ባጠቃላይ በታካሚዎች ተሞልተዋል።
አንዳንዶቹ ታካሚዎች ተዋጊዎች ሲሆኑ ንጹኃን ዜጎችም ይገኙበታል።
የ12 ዓመቷ ጋሀና ናባል ፍየል እየጠበቀች ሳለ ነበር በመሣሪያ ስብርባሪ ጭንቅላቷ ላይ የተመታችው። በአቅራቢያዋ የሁቲ ሞርታር መውደቁን ቤተሰቦቿ ይናገራሉ።
ጋሀና ራሷን ስታለች። ጭንቅላቷ በቁስል መጠቅለያ ታሽጓል፤ ፊቷም አብጧል።
የምትነቃ ከሆነ ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚጠብቃት በመጨነቅ ቤተሰቧ ይመለከቷታል።
ጭንቅላቷ ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት "ከዚህ ቀደም የነበረችውን ዓይነት ሰው ተመልሳ እንደማትሆን" ሐኪሟ ይናገራል።
ከታይዝ በ20 ኪሎሜትር ርቀት ላይ አል-ሞኒግ የተፈናቃዮች መጠለያ ይገኛል። በመቶዎች በሚቆጠሩ ድንኳኖች ከሞክሀ እና ከሌሎች መንደሮች የተፈናቀሉ ሰዎች ይኖራሉ።
ባለፉት 10 ቀናት ብቻ 200 ቤተሰቦች ወደ መጠለያው ገብተዋል።
ማርያም ሳሌህ (ስሟ ተለውጧል) ከአንድ ሳምንት በፊት ከሞክሀ ተሰድዳ ወደ መጠለያው ገብታለች። ባለቤቷ እና አምስት ልጆቿ አብረዋት ናቸው። ትንሹ ልጇ ሰባት ዓመቱ ነው።
ልጆቿን ለመመገብ ስትል ኮፍያ እየሰፋች መንገድ ላይ ትሸጣለች።
"ባዶ እግራችንን ነው የተጓዝነው። ከልጆቻችን ውጭ ምንም ነገር አልያዝም" ትላለች።
የአጎቷ ልጅ ከውጊያ እየሸሸ ሳለ በመሣሪያ ስብርባሪ ተገድሏል። ከኋላዋ እየተጓዘ ሳለ ነበር ሕይወቱ ያለፈው።
ቤተሰቡ ሲሸሽ ከፊትም ከኋላም ውጊያ ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር።
"ያለቀልን መስሎን ነበር። ልጆቹ ማልቀስ እና መጮህ ቀጠሉ። ግን ጉዞዋችንን ቀጠልን።"
ፋጢማ መሐመድ ሳሌህ በሌላ ቤተሰብ ድንኳን በር ላይ ተቀምጣለች። መራመድ የማትችለው ፋጢማ መተኛ ቦታ እንደሌላት ትናገራለች።
"ምንም የለኝም። ቤት የለኝም። ፍራሽ የለኝም። ቤተሰብ የለኝም። ምንም።"
ውጊያው መንደሯ ሲደርስ ከሁለት ወንድ ልጆቿ እና የልጅ ልጆቿ ጋር ነበረች። መራመድ ስለማትችል ጉዞውን ላለማሰናከል ብላ ልጆቿ ሮጠው እንዲያመልጡ ነገረቻቸው።
ለሁለት ቀናት ያህል በእንብርክክ እየተጓዘች ነበር።
"በእንብርክኬ ስሄድ ጥይት ከየአቅጣጫው ይዘንብ ነበር። እንደ መብረቅ ከላዬ ይሰማኝ ነበር። እኔም ለፈጣሪዬ መጸለይ ቀጠልኩ።"
በሞተር ሳይክል እየተጓዘ የነበረ ሰው አግኝቷት ወደ መጠለያው ወሰዳት። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ቤተሰቧን አላገኘችም።
በአውሮፓውያኑ መስከረም 22 የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም ባወጣው አሐዝ እስካሁን ድረስ በየመን ከ130,000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
በእርስ በርስ ጦርነቱ የተፈናቀሉ ሰዎች 5.2 ሚሊዮን ናቸው።
በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ ተጨማሪ 100,000 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንደሚፈናቀሉ ተመድ ገልጿል።



































