"ሁለት እህቶቼን አጥቻለሁ"፡ 139 ሰዎች ከሞቱበት የጂቡቲው የጀልባ አደጋ የተረፉ ኢትዮጵያውያን ምስክርነት

የፎቶው ባለመብት, IOM
ከጂቡቲ ወደ የመን እየተጓዘ የነበረ ጀልባ ተገልብጦ 80 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከአደጋው መትረፋቸውን ዓለም አቀፉ የስደኞች ተቋም (አይኦኤም) ገልጿል።
ለመስከረም 29 አጥቢያ ማለትም መስከረም 28/2019 ዓ. ም. ምሽት ላይ ከጂቡቲ የወደብ ከተማ ኦባክ በስተሰሜን በምትገኘው ጉህሬ አቅራቢያ ጀልባው ተገልብጦ 139 ሰዎች ሞተዋል።
ጀልባው በአጠቃላይ 305 ሰዎችን ጭኖ የነበረ ሲሆን፣ ከስደተኞቹ መካከል በርካቶች የት እንደደረሱ አልታወቀም።
ከሞቱት መካከል 15 ሕጻናት ይገኙበታል።
ከአደጋው በሕይወት ከተረፉት አንዱ አብደላ ነው። ከሐረርጌ ተነስቶ በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመድረስ ነበር ጂቡቲ የገባው።
ከዚህ በፊት በ2014 ዓ.ም. ወደ ሳዑዲ ተጉዞ ነበር። 2018 ረመዳን ወር ላይ ግን ተይዞ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ተደርጓል።
አብደላ ወደ ሳዑዲ እየተጓዘ የነበው ለሁለተኛ ጊዜ ነበር። በዚህኛው ጉዞው እህቱም አብራው ነበረች።
ጀልባው ሲገለበጥ ከሞቱት መካከል እህቱ አንዷ ናት።
"ከዚህ በኋላ ወደ ሳዑዲ አልመለስም" የሚለው ስደተኛው በአደጋው ጓደኞቹም መሞታቸውን ይናገራል።
የ13 ዓመት ልጅን ጨምሮ ከአደጋው የተረፉ ሕጻናት "ያለ ቤተሰብ መቅረታቸውን" ይገልጻል።
አብደላ እና ሌሎችም ከአደጋው የተረፉ ኢትዮጵያውያን በአይኦኤም ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ።
የአይኦኤም የጂቡቲ የተልዕኮ ኃላፊ አሌክሳንድሬ ኮይሳክ "የተሻለ ሕይወት ፍለጋ በዚህ የስደት መስመር የሚጓዙ ፍልሰተኞች የሚገጥማቸው አስቸጋሪ ሁኔታ የሚያስታውስ አሳዛኝ ክስተት ነው" ብለዋል።
የጂቡቲ ባለሥልጣናት የጠፉትን ስደተኞች እየፈለጉ እንደሆነ ዓለም አቀፉ የስደኞች ተቋም አስታውቋል።
ከአደጋው ከተረፉት መካከል ከራያ ቆቦ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እየሄደ የነበረው ደርቤ ይገኝበታል።
ከአምስት ቀናት በፊት ነበር ወደ ጂቡቲ የገባው።
"ደላላ እያደዋዋለ አመጣን። ሁለት ሴት የአጎቴ ልጆችን ይዤ ነበር" ይላል።
ጂቡቲ ከደረሱ በኋላ ወደ የመን ከሚወስዷቸው የየመን ዜጎች ጋር ተገናኙ።
"ጂቡቲ ከደረስን በኋላ የመኖች በጀልባ ጫኑን። 20 ግፋ ቢል 30 ደቂቃ እንደተጓዝን እዚያው አሰመጠን" ሲል ቅጽበቱን ያስታውሳል።
ጀልባው ባሕር ውስጥ ከገባ በኋላ ሰጥሞ መገልበጡን ደርቤ ይናገራል።
"305 ሰው ነበር። ጀልባው ወደ ውስጥ ዘቀጠ። [ምክንያቱ] የሕዝብ ብዛት ነው" ሲል ይገልጻል።
አብረውት እየተጓዙ የነበሩ የአጎቱ ልጆችን አጥቷል።
"ሁለት እህቶቼን አጥቻለሁ። በብዛት የሞቱት ሴቶች ናቸው። ጨለማም ስለሆነ መተጋገዝ የለም።"
ጀልባው እየተጓዘ የነበረው ማታ ከሦስት ሰዓት በኋላ ነበር።

ጀልባው ሲገለበጥ እና ስደተኞቹ ወደ ባሕር ውስጥ ሲገቡ ተረባርቦ በገመድ ለማውጣት ሙከራ ቢደረግም ሕይወት ማትረፍ ቀላል አልሆነም።
"በገመድ እናወጣቸዋለን፣ ተመልሰው ያመልጡናል። እህቴም በትግል ነው ያመለጠችን።"
ጀልባው ከተገለበጠ በኋላ አናቱ ላይ ሆነው መትረፍ እንደቻሉ ይናገራል።
"እኛ የተረፍነው ጀልባው ላይ በመሆናችን ነው። ገመድ ስለምናገኝ ገመድ እያገኘን ወጣን።"
ስደተኞቹ የተገኙት አደጋው ከደረሰ በኋላ በነጋታው ጠዋት ላይ ነው።
ሌሊት ላይ የባሕር ውሃ ሲመታቸው እንዳደረ ያስታውሳል። ከጀልባው የሚወድቁ ሰዎችን ለማንሳትም ሲሞክሩ ነበር።
"በተገለበጠው ጀልባው ላይ ውሃው እየመታን አደርን። የሚወድቁ እያነሳን። ሳይገለብጠን በፊት 150 ሰው አካባቢ መትረፍ ይቻል ነበር።ሲገለብጠን ግን ብዙ ሰው አለቀ" ይላል።
ደርቤ በአደጋው ጉዳት ደርሶበት በቀይ መስቀል ሕክምና እንደተሰጠው ይናገራል።
የባሕር ውሃ ወደ ሰውነታቸው የገባባቸው ሰዎች እንዳሉ ይገልጻል።
"በሰዓቱ ተዳክሜ ነበር። ፈጣሪ ይመስገን ተረፍኩ" ይላል።
የአይኦኤም የጂቡቲ የተልዕኮ ኃላፊ አሌክሳንድሬ ኮይሳክ "ከአገሪቱ [ጂቡቲ] ባለሥልጣናት ጋር በመሆን የድንገተኛ ጊዜ ድጋፍ ለመስጠት የቡድናችን አባላት በቦታው ተገኝተዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
ከጀልባ መገልበጥ አደጋው ለተረፉ ሰዎች የሥነ ልቦና ድጋፍ፣ ጊዜያዊ መጠለያ፣ ምግብ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን እንዲያገኙ እርዳታ እየተሰጣቸው እንደሆነ ተገልጿል።
አሌክሳንድሬ "የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ እጅግ አሳዛኝ ነው። ከአደጋው ለተረፉ እና የሚወዷቸውን ሰዎች በአደጋው ላጡ ሰዎች መጽናናትን እንመኛለን" ብለዋል።
የጂቡቲ ባለሥልጣናት የጠፉትን ሰዎች ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የደኅንነታቸው ጉዳይ አስፈሪ መሆኑን አይኦኤም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ደርቤ እንደሚለው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ቢነገራቸውም በቀጣይ ምን እንደሚፈጠር እርግጠኛ አይደለም።
"ትመለሳላችሁ ይሉናል እንዴት እንደሆነ እኔ እንጃ" ይላል።
ጀልባው ላይ የጫኗቸው የመኖች "ሲደበድቡን ነበር" የሚለው ስደተኛው "ጭነቱስ ለምን ይሄን ያህል [ሰው] ስንል ነበር። ምንም እንደማይሆን ነግረው ጫኑን። ገመድ ሲሰበሰብ ሊገለበጥ እንደሆነ ገባኝ። ሊገለበጥ ነው ብዬ ፈርቼ ነበር። ስንገለበጥ የመኖቹ ሁሉ ጠፉ" ሲልም ክስተቱን ይገልጻል።
ባለፉት ጥቂት ወራት በየመን በተባባሰው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመናውያን ጦርነቱን በመሸሽ ወደ ጂቡቲ እየተሻገሩ ሲሆን፣ አደጋ የገጠማቸውን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት ወደ የመን እየተጓዙ ነው።
ኢትዮጵያውያኑ በባሕር እና በበረሃ ላይ በሚያደርጓቸው አሰቃቂ ጉዞዎች ለአደጋ ከመጋለጣቸው በተጨማሪ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ እንግልት እና ሰቆቃ እንደሚፈጸምባቸው የመብት ድርጅቶች ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

የፎቶው ባለመብት, IOM
በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ለመግባት በጂቡቲ አድርገው ባብ ኤል-መንደብን ተሻግረው ወደ የመን ይጓዛሉ።
ስደተኞቹ በመንገዳቸው ላይ ከሚገጥማቸው ፈተና ባሻገር በየመንም ለጥቃት፣ ለዘፈቀደ እስራት፣ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ብዝበዛ ይጋለጣሉ።
በአውሮፓውያኑ 2025፤ ከ900 በላይ ስደተኞች በዚህ መስመር ለማለፍ ሲሞክሩ መሞታቸውን አልያም መጥፋታቸውን የአይኦኤም መረጃ ያሳያል።
የካቲት 2026 ላይ በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ 45 ሰዎች ጠፍተዋል።
ይሄንን አደገኛ መስመር የሚጠቀሙ ስደተኞች ቁጥርም በ18 በመቶ መጨመሩን ተቋሙ ገልጿል።
አደጋው የደረሰው በሳዑዲ አረቢያ በሚደገፈው የየመን መንግሥት እና በሁቲ አማጺያን መካከል ውጊያ ተባብሶ በቀጠለበት ነው።
አይኦኤም ውጊያውን "አሳሳቢ" ብሎ የገለጸው ሲሆን፤ ከመስከረም አጋማሽ አንስቶ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ76,000 ወደ 200,000 ከፍ ማለቱን አስታውቋል።
ባለፉት ሳምንታት በየመን በሚካሄደው ውጊያ ምክንያት ስደተኞች ወደ ጂቡቲ መግባታቸው ይታወሳል።
በሰሜን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ጦርነትም ወደ ቀጣናው ሊሻገር ይችላል የሚል ስጋት እየተስተጋባ ነው።
አይኦኤም ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ የገቡ ሰዎች ከ20,000 በላይ መሆናቸውን ገልጿል።




































