ግብፅ "በኃይል የባሕር በር ለማግኘት ከሚደረግ ሙከራ መቆጠብ" እንደሚገባ ገለጸች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ፣ "ከዓለም አቀፍ ሕግ ውጭ በኃይል የባሕር በር ለማግኘት" የሚደረጉ ጥረቶች መቆም እንዳለባቸው ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአረብ እና የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ተናገሩ።

የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአፍሪካ ቀንድ "የሚገኙ አገራት "አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት" መጠበቅ እንዳለበት ገልጸዋል።

ባድር አብደላቲ ትናንት እሁድ ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም. ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአረብ እና የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከአሜሪካው አፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ጋር በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የተደረገው ንግግር በተለይም በሱዳን፣ አፍሪካ ቀንድ እና ሊቢያ ያሉ ጉዳዮች የተነሱበት እንደሆነ ተገልጿል።

ግብፅ፣ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ላላችው ሱዳን "አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት" ያላት ድጋፍ "የማይናወጥ" እንደሆነ መግለጿን የጉዳይ ሚኒስቴሯ መግለጫ ያመለክታል።

ሱዳን ውስጥ "ትይዩ ተቋማትን ለመፍጠር የሚደረግ ማንኛውንም ሙከራ" አገራቸው እንደምትቃወም የገለጹት አብደላቲ፣ ሦስት ዓመት ያለፈውን ጦርነት ለመቋጨት "በሱዳናውያን ባለቤትነት እና መሪነት የሚካሄድ አጠቃላይ የፖለቲካ ሂደት" እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአሜሪካው አፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ንግግር ላይ በአፍሪካ ቀንድ የሚታዩ ጉዳዮችን ተነስተዋል። የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "በቀጣናው የሚገኙ አገራት "አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት" መጠበቅ እንዳለበት ተናግረዋል።

አብደላቲ አያይዘውም "በኃይል የባሕር በር ለማግኘት" ይደረጋል ያሉትን ሙከራ ተቃውመዋል። "የቀጣናውን ሰላም እና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የአንድ ወገን እርምጃዎች" መወሰድ እንደሌለባቸው አንስተዋል።

አክለውም "ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ በኃይል የባሕር በር የማግኘት [እንቅስቃሴን] ለመጫን ከሚደረግ ማንኛውም ሙከራ መቆጠብ እንደሚገባ በአጽንኦት አንስተዋል" ሲል የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አስፍረዋል።

የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ይደረጋል ያለው ሙከራ በየትኛው አገር እንደሚካሄድ አልጠቀሰም። ይሁን እንጂ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብደላቲ ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ባሕር በር ለማግኘት ያለውን ፍላጎት እየገለጸ ባለበት ወቅት ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ባሕር በር ማግኘት "ለኢትዮጵያ የኅልውና ጉዳይ" መሆኑን ላለፈው ሦስት ዓመት ገደማ ሲገልጽ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥታቸው ይህንን ፍላጎት ማሳካት የሚሻው "በሰላማዊ መንገድ" እና "በንግድ ልውውጥ" እንደሆነ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘቷ ጉዳይ ላይ "ተፈጽሟል" የሚሉት ስህተት እንዲሁም "ነገ ይታረማል" የሚለው ገለጻቸው፤ በኤርትራ በኩል በበጎ አልታየም።

የኤርትራ መንግሥት ይህ የኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ እንቅስቃሴ "በአገሪቱ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ላይ የተቃጣ ትንኮሳ" እንደሆነ በመግለፅ ተቃውማለች።

የቀይ ባሕር ደኅንነት የሚመለከተው የውሃ አካሉን የሚጎራበቱ አገራትን ብቻ እንደሆነ የምትገልጸው ኤርትራ፣ ይህንን አቋሟን በግብፅ ጋር በመሆንም አንጸባርቃዋለች።

ከአንድ ወር በፊት የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ በተገናኙበት ወቅት የቀይ ባሕር "ደኅንነት እና አስተዳደር የሚመለከተው የጠረፉን አገራት ብቻ" መሆኑን ገልጸዋል።

የጠረፉ አካል ያልሆኑ አገራት ቀይ ባሕርን "በሕገ ወጥ መንገድ ለመቆጣጠር የሚደረጉት ሙከራ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው" ሲሉም ሁለቱ አገራት አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።

ይህ የግብፅ አቋም በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አላገኘም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ግንቦት ላይ በሰጡት መግለጫ ትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን ካነሳች በኋላ ከግብፅ በኩል "ውጥረት፣ ትንኮሳ የሚመስሉ ነገሮች እየታዩ" መሆናቸውን በመጥቀስ ከስሰዋል።

ይህ ጥያቄ ከተነሳ በኋላ "ኢትዮጵያን ለማነቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የመጨመር እና የመጠናከር አካሄድ እናያለን" ያሉት ቃል አቀባዩ፣ አዲስ አበባ "የባሕር በር ፍላጎት አጀንዳዋን" አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ለዓመታት በዘለቀ ውዝግብ ውስጥ የምትገኘው ግብፅ፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ስጋት ከፈጠረባት ኤርትራ ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ከኢትዮጵያ ተቃራኒ የሆነ አቋም እያራመዱ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ሁለቱ አገራት በአገሪቱው ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን በመርዳታ በተደጋጋሚ ሲከስሱ ይሰማል።