ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ ሺዎችን ለማዕድን ፍለጋ ያራኮተው አንድ የፍየል እረኛ ያገኘው ትንሽ ወርቅ
የምዕራብ ኬንያ ነዋሪ የሆነ አንድ የፍየል ጠባቂ ያገኘው ትንሽ ወርቅ ማኅበረሰቡ ለወርቅ ፍለጋ እንዲራኮት ማድረጉን ለቢቢሲ ተናገረ።
የ33 ዓመቱ ማናሴ ሎማቻር እንደሚለው የአካባቢው ነዋሪዎች በገጠራማዋ ትንሽ መንደር ወርቅ ለመፈለግ የተሰማሩት ከበርካታ ሳምንታት በፊት ያገኛትን ሦስት ግራም ወርቅ በ280 ዶላር መሸጡ ከተሰማ በኋላ ነው።
ከአንድ ወር በፊት በመንደሯ አቅራቢያ ጥሻ እና የግጦሽ ሥፍራ የነበረው መሬት አሁን ላይ በጉድጓድ እና በአፈር ቁልል እንዲሁም በማዕድን ማውጫ ካምፖች ተወርሷል።
በእርግጥ ይህንን የፈጠረው የሎማቻር ዕድል ይሁን ሌሎች የቅርብ ጊዜ ግኝቶች ግልፅ አይደለም።
ሆኖም የአካባቢው ባለሥልጣናት ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በአካባቢው ለወርቅ ፍለጋ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
ውድ የሆነው ማዕድን በአብዛኛው ኑሯቸው በግብርና ላይ የተሰመረተ የኡጋንዳ እና የኬንያ ሰዎችን ሕይወት ይለውጣል።
ሆኖም ሰዎች በአካባቢው ወርቅ ለመግኘት ቢቆፍሩም እስካሁን እዚህ ግባ የሚባል ነገር አላገኙም።
የፍየል እረኛው ሎማቻር እንደሚለው ወርቅ ያገኘው የጠፋችበትን ፍየል ሲፈልግ በአጋጣሚ ነው። በወንዙ አቅራቢያ ሴቶች ወርቅ ሲፈልጉ እንደተመለከተ እና እንደተቀላቀላቸው የሚናገረው ሎማቸር፣ ትንሽ ወርቅ ካገኘ በኋላ መንደርተኛው በአካባቢው ወርቅ እንዳለ መገንዘቡን ያስረዳል።
የምዕራብ ፖኮት አውራጃ ምክትል ኮሚሽነር ሳሙዔል ኬሬ እንደሚሉትም መራኮቱ የጀመረው ሁለት ጊዜ ወርቅ መገኘቱን ተከትሎ ነው።
" መጀመሪያ ላይ ወጣት ወንዶች ወርቅ አግኝተዋል፤ በሚቀጥለው ቀንም በተመሳሳይ ቦታ ሴቶች አነስተኛ መጠን ያለው ወርቅ አግኝተዋል።" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሆኖም ነሐሴ ወር ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ተገኝቷል መባሉ የበርካታ ሰዎችን ትኩረት ስቧል።
ኬሬ እንደሚሉት አሉባልታዎች መሰራጨታቸው እና የተገኘው መጠን እና ቁጥሩ መጋነኑ "ትንሽ ወይም ምንም" የማዕድን ቁፋሮ ልምድ የሌላቸው በርካታ ሰዎች ወደ ሥፍራው እንዲያመሩ አድርጓል።
ከመጀሪያው ጀምሮ ወርቅ ለማግኘት ተስፋ አድርገው የተሰማሩ አንዳንድ ሰዎች ግን ተስፋ በመቁረጣቸው ምክንያት ጥለው እየወጡ ነው። በዚህም ምክንያት በአካባቢው የተሰማሩ ሰዎች ቁጥር መጀመሪያ ላይ ከነበረው 10 ሺህ ወደ 2 ሺህ 500 ወርዷል።
በአካባቢው ወርቅ መገኘቱ ምንም የማያጠራጥር ባይሆንም በመሬት ውስጥ ያለው የክምችት መጠን እና የንግድ አቅም ላይ ጥያቄዎች አሉ።
የማዕድን ሥፍራው የምትገኝበት ምዕራብ ፖኮት አውራጃ ከኡጋንዳ ጋር የሚዋሰን ሲሆን የሁለቱም አገራት ማኅበረሰቦች ማኅበራዊ እና ቤተሰባዊ ትስስር አላቸው።
በምሥራቅ ኡጋንዳ ቡሲያ ነዋሪ ሆኑት የማዕድን አውጪ ባለሙያ ሙጊሻ ጎድፍሬይ ዜናውን ከሰሙ በኋላ ወደ ቼፖረር አቅንተዋል።
ከሥፍራው ለመድረስ 27 ዶላር ገንዘብ አውጥተዋል ። ሆኖም በመንደሩ ያለው ሁኔታ ምቹ አይደለም።
"ዛፍ ሥር ነው የምንተኛው፣ ሲነጋ ሥራችንን እንቀጥላለን፣ አንዳንዴ ቀንና ሌሊት እንሰራለን" ብለዋል። እስካሁን ምንም ያገኙት ነገር ባይኖርም ተስፋ ግን አልቆረጡም።
" የሆነ ነገር ካላገኘን አንመለስም፤ የምንፈልገውን ስናገኝ ነው ወደ ቤታችን የምንመለሰው።" ብለዋል።
በአካባቢው ምግብ፣ ውሃ እና ሌሎች ፍጆታዎችን የሚሸጡ 200 ሱቆች መከፈታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የሰዎች መበራከት ወትሮም ትንሽ መሠረተ ልማት ፣ ውሃ እና ንፅህና በሌላት መንደሯ ላይም ጫና ፈጥሯልም ብለዋል።
የኅብረተሰብ ጤና ባለሥልናትም ሁኔታውን እንዲከታተሉ እና ወረርሽኝ እንዳይከሰት ለመከላከል በአካባቢው ተሰማርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ ጥቃት ይፈፀማል የሚል ስጋት በመፈጠሩ የፀጥታ ቅኝት እንዲጨምር መደረጉን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ሕፃናት ትምህርታቸውን ትተው ወደ ማዕድን ቁፋሮ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋትም የተፈጠረ ሲሆን ታዳጊዎች በዚህ ላይ እንዳይሰማሩ የሚያደርጉ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።
ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ሰዎችም ጥልቅ ጉድጓድ መቆፈራቸውን ተያይዘውታል።
በርካታ ከባድ መኪናዎች በአቅራቢያ ወደምትገኘው ኦርተም ከተማ የተጓዙ ሲሆን ባለሥልጣናት ውጤቱን እየተጠባበቁ ነው።
እስከዚያ ድረስ መጠኑም ሆነ ለገበያ የሚውል ነው የሚለው ላይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ለሎማቻር ግን መልሱ የሚረዳው የበለጠ ቅንጅት ለመፍጠር ካልሆነ በስተቀር የማዕድን ቁፋሮውን እንደማያስቆመው ተናግሯል።
ይልቁኑ መንግሥት ለአካባቢው ማዕድን አውጪዎች ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ የሆነ መንገድ እንዲዘረጋላቸው ይፈልጋል።