"በ40 ዓመቴ የካስትሮ እውነተኛ ልጅ ሆንኩ"፡ አመጸኛዋ የፊደል ካስትሮ ልጅ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

አሊና ፈርናንዴዝ ልጅ ሳለች ፊደል ካስትሮ በተደጋጋሚ ያለችበት ድረስ እየሄዱ ይጠይቋት ነበር።

በልጅነቷ ኩባን ለ50 ዓመታት ያህል በፍጹም አምባገነንነት፣ በጠንካራ ክንዶቹ ሥር በማድረግ ያስተዳደሩት ሰው ወላጅ አባቷ እንደሆነ አታውቅም ነበር።

ካስትሮ እና ናቲ ፈርናንዴዝ ከጋብቻ ውጪ በነበራቸው ግንኙነት ነበር አሊና በአውሮፓውያኑ 1956 የተወለደችው።

እናቷ በዋና ከተማዋ ሃቫና የምትኖር ከናጠጠ ሃብታም ቤተሰብ የዘር ግንዷ የሚመዘዝ ቆንጆ ነበረች። ካስትሮ ደግሞ በወቅቱ ከሽምቅ ተዋጊዎች ንቅናቄ መሪዎች አንዱ ነበር።

በቀጣዮቹ አስርት ዓመታት ውስጥ እስከ 3 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ወደ ጎረቤት ዩናይትድ ስቴትስ ሸሽተው እንደነበር ይገመታል። ከእነዚህም መካከል የካስትሮ ልጅ ትገኝበታለች።

ከአውሮፓውኑ 1959 እስከ 2008 የመሩት እና በኅዳር 2016 በካንሰር የሞቱት ካስትሮ፣ 100ኛ ዓመታቸውን ነሐሴ 13 ቀን ያከብሩ ነበር።

ከካስትሮ ልጆች መካከል ፈርናንዴዝ ብቸኛዋ በይፋ የምትታወቀው ናት።

ፈርናንዴዝ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ታዋቂ እና አወዛጋቢ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ስለሆነበሩት እና "አባቴ" ብላ መጥራት ስለማትፈልጋቸው ካስትሮ ለቢቢሲ ተናግራለች።

የመጀመርያዎቹ ትዝታዎች እና በምሽት የሚደረጉ ጥየቃዎች

ስለካስትሮ የመጀመሪያ ትዝታዋ ቀደም ሲል የሚኪ ማውስ ካርቱን የሚያሳዩ የነበሩ የቴሌቪዥን መስኮቶችን የሞላ ጢም የወረሰው ሰው ነው።

"ሚኪ ማውስ ጠፋ" የ70 ዓመቷ አዛውንት ፈርናንዴዝ ታስታውሳለች፤ "በተሽከርካሪዎች ላይ የተሳፈሩ ጢም የወረሳቸው ሰዎች ተኩት፣ በጣም አስፈራሩኝ እና በቴሌቪዥን መስኮት ላይ ዜና ሆነው ለቀናት ቆይተዋል።"

የአገሪቱ ለውጥ የራሷን ጨምሮ ብዙ ቤተሰቦችን ከፋፈለ፤ እናቷም አብዮቱን ተቀበለች ። ነገር ግን ሌሎች ዘመዶቿ፣ አሊና በወቅቱ አባቷ እንደሆነ የምታምነው ኦርላንዶ ፈርናንዴዝን ጨምሮ፣ ሁሉንም ነገር ትተው ወደ አሜሪካ ለመሄድ መረጡ።

አሊና ይህንን ሁሉ ሙሉ በሙሉ ሳታውቅ እያደገች ሳለ፣ አዲሱ የኩባ መሪ አልፎ አልፎ ወደ ቤቷ መምጣት ጀመረ።

ካስትሮ በሳሎን ወለል ላይ ከእርሷ ጋር ሲጫወቱ፣ ስጦታዎች ያመጡላት እንደነበር ታስታውሳለች።

ከእነዚህም መካከል በጣም እንግዳ የሆነውን አንዱ የበለጠ ትዝ ይላታል። "እንደራሱ የለበሰ አሻንጉሊት ሰጠኝ፤ ትንንሽ የጢሙን ፀጉሮች እነቅል ነበር ምክንያቱም ለእኔ አሻንጉሊት ነበር" ብላለች።

እውነታው ተገለጠ

የ10 ዓመት ልጅ እያለች ስለ እውነተኛ አባቷ እውነቱን አወቀች።

"እናቴ ነገረችኝ። ትምህርት ቤቴን ልትቀይር እንደሆነ እና መንገደኛ በድንገት እንዲነግረኝ አልፈለገችም።"

ካስትሮ አልፎ አልፎ በሚያደርጓቸው ጉብኝቶች የአባትነት ሚና መጫወት ጀምረው ነበር። ነገር ግን እናቷ አባቷ እንደሆነ ስትነግራት "የመከዳት እና የመታለል ስሜት" እንደተሰማት ታስታውሳለች።

ፈርናንዴዝ የቅርብ ጓደኛዋን ጨምሮ በዙሪያዋ ያሉ ብዙ ሰዎች ስለ እውነተኛ አባቷ የሚነገሩ ኡባልታዎችን ያውቁ ነበር።

"ጉዳዩ የአደባባይ ምሥጢር ነበር፤ በዙሪያዬ የነበሩት ሁሉ ያውቁ ነበር" ትላለች።

ፈርናንዴዝ የአባቷን ስም ወደ ካስትሮ ለመቀየር ፈቃደኛ አልሆነችም፣ ምክንያቷ ደግሞ ለዓመታት እውነተኛ አባቷ በይፋ እንዲታወቅ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ነው።

"'ልጁ ነሽ ወይ?' ብለው ሲጠይቁኝ 'አይደለሁም' እል ነበር፤ አንድ ቀን የአባቴ ስም ተቀይሮ በድንገት መታየት ውርደት የሚያስከትል ሆኖ ተሰማኝ። ምንም ፋይዳው አልታየኝም።"

ፈርናንዴዝ በኩባ በነበረችበት ወቅት በአባቷ ላይ እና በአገሪቱ ላይ በተጫነው አዲስ ሥርዓት ላይ ብስጭቷ እና ቅሬታዋ እየጨመረ መጣ። የፊደል ካስትሮ ልጅ መሆኗን ሲያውቁ ብዙ ሰዎች ደብዳቤዎችን ለአገሪቱ መሪ እንድታደርስላቸው ይሰጧት ነበር።

"የቤተሰቦቻቸው አባላት የተገደሉባቸው እና ለእነሱ ሲኦል ከነበረው አገር እንዲወጡ ፈቃድ ለማግኘት የሚሞክሩ ሰዎች ነበሩ።"

በመሪው ዙሪያም እርሱን አግዝፎ የሚያሳይ የተሳለ አመለካከት ነበር።

"አንድ ሰው (ካስትሮ) ሰባት ሰዓት የፈጀ የቴሌቪዥን ንግግሮችን ሰጥቶ በቀጣዩ ቀን እኛ በክፍል ውስጥ እንድናየው የተገደድንበትን ንግግር ያደረገ ሰው…ቅዠት ነበር። አቅሉን በሳተ ቤት ውስጥ እየኖርክ እንደሆነ ይሰማሃል" ትላለች።

ፈርናንዴዝ እና እናቷ ፈረንሳይ ቆይተው ከመጡ በኋላ የካስትሮ ጉብኝት እየቀነሰ መጣ። እንደ እርሷ ገለጻ ከእናቷ ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማቀዝቀዝ በማሰብ ካስትሮ ነው ወደ ፈረንሳይ የላካቸው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኩባው መሪ አልፎ አልፎ ድንገተኛ እና የማይጨበጡ ውሳኔዎችን በማድረግ ወደ ሕይወቷ ይመጣ ነበር። ለምሳሌ የፍቅር አጋሮቿን አለመቀበል ወይም ወደ ሌላ ትምህርት ቤት እንድትዛወር ማድረግ ከውሳኔዎቹ መካከል ይገኙበታል።

"ሁልጊዜም መላ ቅጣቸው የማይታወቅ ሃሳቦች ነበሩ። በእርሱ ላይ ሳልደገፍ መኖርን ተምሬያለሁ" በማለት ታስታውሳለች።

ፊደል ካስትሮ በግል ሲታዩ ምን እንደሚመስሉ ስትጠየቅ፤ አስተዋይ፣ ትሁት፣ ጨዋ፣ ቀልጣፋ "ወሰን የሌለው የማወቅ ጉጉት" እንዳላቸው ትገልጻለች። ነገር ግን አባቷ በተደጋጋሚ እንደዋሿትም ጠቅሳለች።

"አንድ ነገር እንደነገረኝ ይረሳል፤ ከዚያም በኋላ ስለ ተመሳሳይ ጉዳይ ሌላ መረጃ ይነግረኝ ነበር።"

በአባት እና በልጅ መካከል የተደረጉ ንግግሮችም ቢሆኑ ቀላል አልነበሩም።

"እሱ ብቻውን ለረዥም ጊዜ የሚያወራ ሰው ነበር። ከእኔ ጋር ማውራት ከፈለገ የእኔ ድርሻ ማዳመጥ ብቻ ነበር።"

ከሃቫና ሽሽት

ፈርናንዴዝ ኩባን ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ለቅቃ መሄድ ትፈልግ እንደነበር ትናገራለች። አባቷ ከገነባውን ሥርዓት፣ ከአባቷ በየዕለቱ እየራቀች እንደሆነ ተሰምቷታል።

በወቅቱ የዕለት ተዕለት ሕይወቷን የወረሰው እጥረት ለዚህ ስሜቷ አንዱ ምክንያት ነበር።

ብዙ ጊዜ ወደ ውጭ አገር ለመጓዝ እንደሞከረች የምታስታውሰው ፈርናንዴዝ፤ አገዛዙ ግን ይኹንታ አልተሰጣትም።

በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሶቪየት ኅብረት መፍረስ በኩባ ውስጥ ልዩ ወቅት ተብሎ የሚጠራውን የረሃብ እና ሰፊ የመብራት መቆራረጥ እንዲከሰት አድርጓል።

ፈርናንዴዝ ቀድሞውኑ በግልጽ የምትቃወም በመሆኗ የአገሪቱ መሪ ልጅ ብትሆንም እታሰር ይሆናል በማለት ትፈራ ነበር።

"እኩለ ሌሊት ላይ የሚሰማ የመኪና በር መከፈት ወደ አንተ እየመጡ እንደሆነ እንድታስብ ያደርግሃል።"

የቅርብ ጓደኞቿ በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 19/1993 ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት ዕቅድ ከአገር እንድትወጣ አመቻቹላት።

አንዲት ስፔናዊት ፈርናንዴዝ ፓስፖርቷን እና የአውሮፕላን ትኬቷን እንድትጠቀም ፈቀደች። ሌላ ሰው ፓስፖርቱን እንድትጠቀም ፎርጅድ ሠርቶላታል።

ፈርናንዴዝ ደግሞ በዋና ከተማዋ ሃቫና ወደሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ታክሲ ይዛ ሄደች።

"ታክሲ ውስጥ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ እንደ ስፔናዊ ለማውራት መለማመድ ጀመርኩ፤ ምክንያቱም ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ስደርስ፣ መናገር ቢኖርብኝ ስፔናዊ የሚመስል ቅላጼ ሊኖረኝ ይገባል። በዚህም ሹፌሩን ሙሉ በሙሉ አታልዬዋለሁ።"

ዊግ አድርጋ፣ ሜካፕ ተቀብታ ላለመታወቅ ጥረት ካደረገች በኋላ አውሮፕላን ማረፊያ ደረሰች።

"ያለ ምንም ችግር ኢሚግሬሽኑን አለፍኩ። በረራው ዘግይቶ ስለነበር በፀጥታ መጽሐፍ እያነበብኩ ተቀምጬ 'ምንም ይሁን ምን የሚመጣውን በጸጋ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ' ስል አስብ ነበር።"

ከረዥም ጊዜ ቆይታ በኋላ የአውሮፕላን ጉዞው ያለምንም ችግር ተጀመረ። መጀመሪያ ወደ ማድሪድ ከበረረች በኋላ በቀጣይ ወደ አሜሪካ ለመግባት ፈቃድ አገኘች።

ከዚያም የ16 ዓመት ልጇን ከኩባ ለማስወጣት ፈቃድ እንዲሰጣት አቤቱታ አቀረበች። የአሜሪካ የሰብዓዊ መብቶች መሪ ቀሲስ ጄሲ ጃክሰን አደራዳሪ ሆነው እናት እና ልጅ በመጨረሻ በአውሮፓውያኑ 1994 ለመገናኘት በቁ።

ፈርናንዴዝ በቋሚነት በማያሚ መኖር ከመጀመሯ በፊት በዩናይትድ ስቴትስ እና በስፔን ቆይታለች።

'በ40 ዓመቴ የካስትሮ እውነተኛ ልጅ ሆንኩ'

ኩባን ለቅቃ ከወጣች በኋላ፣ በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ ለመተቸት ስትል ከፊደል ካስትሮ ጋር ስላላት ግንኙነት በይፋ መናገር ጀመረች።

ለረዥም ጊዜያት የእርሱ ልጅ መሆኗን ለመደበቅ ብትሞክርም፣ ለቅቃ ከወጣች በኋላ በ40 ዓመቷ ኩባን ይህንን እውነታ በመቀበል መንቀሳቀሷን ትናገራለች።

በ1997፣ በስፔን ከፍተኛ ሽያጭ ያገኘ እና በኋላም ወደ በርካታ ቋንቋዎች የተተረጎመውን "አሊና፡ የፊደል ካስትሮ አመጸኛ ልጅ ማስታወሻ" የተሰኘውን መጽሐፍ አሳትማለች።

የፊደል ካስትሮ ሞት እንዴት እንደሰማች ስትጠየቅ "ሐዘንም ደስታም አልተሰማኝም። ለእኔ አስደንጋጭ አልነበረም" ብላለች።

በአሁኑ ወቅት፣ የካስትሮ ቤተሰብ ተተኪ ተደርገው በሚታዩት ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ-ካኔል ስር፣ ኩባ እጅግ ከባድ የሆነ ቀውስ እያጋጠማት ነው። አንዳንዶች ይህ ሁኔታ በኩባ ታሪክ ውስጥ አስቸጋሪ ከነበረው "ልዩ ወቅት" የበለጠ የከፋ እንደሆነ ይናገራሉ።

አሜሪካ ለረጅም ጊዜ የቆየውን ማዕቀብ ባጠናከረችበት ወቅት፣ ኩባ ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ፣ እንዲሁም የተለያዩ አቅርቦቶች እጥረት እና ረሃብ እያጋጠማት ነው።

ፈርናንዴዝ ይህ ቀውስ በአባቷ በተመሠረተው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሥርዓት ምክንያት የተፈጠረ እንደሆነ ታምናለች።

"መንግሥት ሁሉንም ንግዶች ሲቆጣጠር ሁሉም ሰው ያለ ነጻነት እርቃኑን ይቀራል።"