ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሆርሙዝ ወሽመጥ በመስተጓጎሉ የኃያላን የፍጥጫ ማዕከል የሆነው ፓናማ ካናል
የኢራን ጦርነት ከዓለም ወሳኝ የባሕር መስመሮች አንዱ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ መተላለፊያነት ባስተጓጎለበት በዚህ ወቅት፣ በሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኝ ሌላ የባሕር መስመር ውጥረት ምንጭ ሆኖ ብቅ ብሏል። ይህ የባሕር መስመር አትላንቲክ እና ፓሲፊክ ውቅያኖሶችን የሚያገናኘው የፓናማ ካናል ነው።
አሜሪካ በካናሉ ላይ እየጨመረ የመጣው የቻይና ተፅዕኖ፣ ዓለም አቀፍ ንግድ እና ደኅንነትን አደጋ ላይ ይጥላል በሚል አስጠንቅቃለች።
ክሱን ውድቅ የምታደርገው ቻይና በበኩሏ፣ አሜሪካ ይህንን ጉዳይ በውሃ መስመሩ ላይ ያላትን ቁጥጥር ለማስፋፋት እንደ ምክንያት እየተጠቀመች ነው የሚል ወቀሳ አቅርባለች።
በሁለቱ ኃያላን መሃል የገባችው ፓናማ ደግሞ በካናሉ ላይ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ መሆኑ እንዲሁም በውዝግቡ ላይ ገለልተኛ ሆና እንደምትቀጥል ገልጻለች።
ፓናማ ካናል ምንድነው? እንዴትስ ይሠራል?
ፓናማ ካናል በፓናማ ልሳነ ምድር የተዘረጋ እንዲሁም አትላንቲክ እና ፓሲፊክ ውቅያኖሶችን የሚያገናኝ የ80 ኪሎ ሜትር ሰው ሠራሽ የባሕር መተላለፊያ ነው።
ካናሉ፤ መርከቦች በደቡብ አሜሪካ ደቡባዊ ጫፍ የሚገኘውን ኬፕ ሆርን በመዞር የሚያደርጉት ረጅም ጉዞ እንዲቀንስ ያደርጋል። የባሕር መተላለፊያው መኖር፣ ጉዞው የሚወስደውን ጊዜ እና የትራንስፖርት ወጪን በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል።
በካናሉ የሚያልፉ መርከቦች የትራንዚት ክፍያ ይከፍላሉ። ክፍያው የሚወሰነው እንደ የመርከቡ መጠን እና ዓይነት እንዲሁም ጭነት ያሉ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ገብተው ነው።
ካናሉ መርከቦችን ከባሕር ወለል በላይ ወደ ጋቱን ሐይቅ ለማንሳት እና ተቃራኒው አቅጣጫ ወደሚገኘው የባሕር ዳርቻ ለማሳረፍ የሚያስችል ውሃን ከፍ እና ዝቅ የሚያደርግ (ሎክስ) ሥርዓት ይጠቀማል።
መርከቦች በሚያልፉበት በእያንዳንዱ ጊዜ፣ በሚሊዮን ጋሎን የሚቆጠር ንጹህ ውሃ ከጋቱን ሐይቅ እና ከአቅራቢያው ካሉ የውሃ ማጠራቀሚያዎች እንዲወጣ ይደረጋሉ።
ካናሉ መርከቦችን ለማሳለፍ ንጹህ ውሃን የሚጠቀም መሆኑ፣ ለድርቅ ተጋላጭ ያደርገዋል። የአገሪቱ ባለሥልጣናት የውሃ መጠን በሚቀንስበት ወቅት መርከቡ የሚያርፍበት ውሃ ጥልቀት ላይ ገደብ ይጥላሉ። ይህም መርከቦች የሚይዙት የጭነት መጠን እና የካናሉ የማስተናገድ አቅም እንዲቀንስ ያስገድዳል።
በካናሉ በኩል የሚደረግ የመርከብ ጉዞ ለምን ጨመረ?
ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር፣ በካናሉ የሚያልፉ መርከቦች ብዛት በስምንት በመቶ ጨምሯል። ግንቦት ላይ በየቀኑ የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር በአማካይ 38 ደርሷል።
ይህ ቁጥር የውሃ መስመሩ ሊያስተናግድ ለሚችለው የመጨረሻ አቅም የተጠጋ መሆኑን የዓለም ትልቁ ዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞ ማኅበር 'ቢምኮ' ገልጿል።
የቢምኮ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የኢራን ጦርነት ከተነሳ በኋላ በነበሩት አምስት ሳምንታት ውስጥ የነበረው የመርከቦች ጉዞ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በ16 በመቶ ጨምሯል።
ግጭቱ፣ ከዓለም የነዳጅ ምርት አንድ አምስተኛው በሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ጉዞን አስቸጋሪ ማድረጉን ተከትሎ፣ የእስያ ገዢዎች ከአሜሪካ ገልፍ ኮስት አቅራቢዎች የሚገዙትን ድፍድፍ እና የተጣራ ነዳጅ ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል።
ከእነዚህ ጭነቶች ውስጥ አብዛኞቹ የሚጓዙት በአትላንቲክ እና በፓሲፊክ መካከል በሚገኘው ፓናማ ካናል በኩል በመሆኑ፣ የትራንዚት ፍላጎቱ አድጓል።
ይህ የመርከቦች ጉዞ መጨመር ደግሞ ለማለፍ የሚጠበቀው ጊዜ እንዲጨምር፣ ለምዝገባ ከፍተኛ ፉክክር እንዲኖር እና ቅድሚያ ለማግኘት ተጨማሪ ክፍያ እንዲጠየቅ ምክንያት ሆኗል። አንዳንድ የመርከብ ኦፕሬተሮች ፈጣን ትራንዚት ለማግኘት የሚደረግ ጨረታ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደከፈሉ ተሰምቷል።
"ፓናማ ልክ እንደ ሆርሙዝ [በመርከቦች] ብዛት የሚለካ መተላለፊያ አይደለም፤ የሥራው ዓይነት የተለየ ነው። ከዓለም የባሕር ንግድ የሚያስተላልፈው 5 በመቶ ገደማ ነው፤ ከአሜሪካ ጭነት ውስጥ ግን 40 መቶ ገደማው ይጓጓዝበታል" ይላሉ ዳላስ በሚገኘው 'ኖርዝ ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ' የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ኦርላንዶ ጄ. ፔሬዝ።
"ሆርዘዝ የኤነርጂ መተላለፊያ መስመር ነው። ፓናማ ደግሞ አንድ የኃያል ኢኮኖሚ የአቅርቦት ሰንሰለት መተለላፊያ መስመር ነው። ሁለቱም ወሳኝ ናቸው" በማለት ያብራራሉ።
በተጨማሪም የፓና ማካናል የሚያጋጥሙት አካባቢያዊ ተግዳሮቶች እየጨመሩ ነው።
የጋቱን ሐይቅ ውሃ ለረጅም ጊዜያት ከነበረው አማካይ መጠን አንደቀነሰ ቀጥሏል። ይህም የፓናማ ካናል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት መርከቦች የሚያርፉበት የውሃ ጥልቀትን እንዲገድብ አድርጓል።
ከመጪው መስከረም ወር አንስቶም በየቀኑ የሚያልፉት የመርከቦች ብዛት ከ36 ወደ 32 እንዲቀንስ ተወስኗል።
ባለሥልጣናት እንደሚናገሩት ይህ ሁኔታ የተከሰተው፣ እንደ ኤል ኒኖ ባሉ የአየር ንብረት ለውጦች ምክንያት በመጣው የዝናብ እረጥት የተነሳ ነው።
ሰሞነኛው ሁኔታ ከሦስት ዓመት በፊት በ2023 የከፋ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር በመገደቡ የተፈጠረውን ረጅም ወረፋ እና የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል ያስታወሰ ሆኗል።
ካናሉ እንዴት ተሠራ?
ፓናማ ካናል 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የተገነባው በአሜሪካ ነው። እስከ አውሮፓውያኑ 1977 ድረስም ካናሉን እና በዙሪያው ያለውን የካናል ዞን ስትቆጣጠር ቆይታለች።
ኋላም በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር ዘመነ መንግሥት በተደረገ ድርድር በተፈረመው 'የቶሪሆስ-ካርተር ስምምነት' አማካኝነት ዋሽንግተን የካናሉን አስተዳደር ለካናዳ አሳልፋ የምትሰጥበት የጊዜ ሰሌዳ ወጥቷል።
የአስተዳደር ርክክቡ በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 1999 ተጠናቅቋል።
በአሁኑ ሰዓት በስምምነቱ መሠረት የውሃ መስመሩን በገለልተኝነት እና ዓለም አቀፍ የመርከብ ትራንስፖርት እንዲተላለፍበት በሚያደርግ መልኩ ካናሉን የሚያስተዳድረው የፓናማ ካናል ባለሥልጣን ነው።
አሜሪካ ቻይና ላይ የምታነሳቸው ስጋቶች ምንድን ናቸው?
ውዝግቡ ባለቤትነት ላይ ከሚነሳው ጥያቄ ይልቅ ወደ ተጽዕኖ የበላይነት ያመዝናል።
መቀመጫውን በሆንግ ኮንግ ያደረገው 'ሲኬ ሀትቺሰን' በስሩ በሚገኘው የፓናማ ፖርትስ ካምፓኒ በኩል ላለፉት አስርት ዓመታት፣ በካናሉ የፓሲፊክ እና የአትላንቲክ መግቢያዎች የሚገኙ ሁለት ወደቦችን ሲያስተዳድር ቆይቷል።
ኩባንያው ባልቦአ እና ክሪስቶባል ወደቦችን የሚያስተዳድረው ከፓናማ ጋር በፈጸመው ስምምነት መሠረት ነው።
ምንም እንኳ ኩባንያውም ሆነ ቻይና በካናሉ ምንም ዓይነት ሚና ባይኖራቸውም፣ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከቤይጂንግ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት በአካባቢው መኖራቸውን በስጋትነት ያነሳሉ። በተለይም ውሃ መተላለፊያው ዙሪያ በሚገኙ ወደቦች፣ ሎጂስቲክስ እና ትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ጉዳይ ያሳስባቸዋል።
በ2026 መጀመሪያ የፓናማ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሲኬ ሀትቺሰን ጋር ስምምነት የተፈጸመበት የሕግ ማዕቀፍ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም የሚል ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ ውጥረቱ ተባብሷል።
ፕሮፌሰር ፔሬዝ፣ "ዋሽንግተን ከቻይና ጋር ግንኙነት ያላቸውን የወደብ አስተዳዳሪዎች የምትመለከታቸው፣ ከዚህ በፊት ትቆጣጠር በነበረው ሀብት ዙሪያ እንደሚገኙ ስትራቴጂካዊ መሣሪያዎች ነው። ቤይጂንግ ደግሞ ፓናማን ሕጋዊ ኮንትራትን እንድትቀለብስ ጫና የሚደረግባት ትንሽ አገር አድርጋ ትመለከታታለች" ይላሉ።
ይሁ ሁኔታ የካናሉ ገለልተኝነት ፈተና ውስጥ እንደከተተውም አክለዋል።
በቺሊ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ጥናቶች ኢንስቲትዩት የክብር ፕሮፌሰር የሆኑት ኾርሄ ሃይነ፣ ንትርኩን "ሙሉ በሙሉ መሠረት የለሽ" በማለት ይገልጹታል።
እንደ ሃይነ ገለጻ፣ 'ሲኬ ሀትቺሰን' በካናሉ አስተዳደር መሳተፍ የጀመረው ሆንግ ኮንግ ወደ ቻይና ሉዓላዊነት ከመመለሷ ከወራት በፊት በአውሮፓውያኑ 1997 መሆኑን ይጠቅሳሉ።
"ሥራቸው ኮንቴይነሮች እና ተያያዥ የወደብ ሥራዎችን ማስተዳደር ብቻ ነው። ራሱ ካናሉን አያስተዳድሩም" ይላሉ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ቻይና በፓናማ ውስጥ ከመጠን በላይ ተጽእኖ አላት በማለት ይከስሳሉ። አሜሪካ ካናሉን መልሳ ልትቆጣጠር እንደምትችልም ይናገራሉ። ፓናማ ይህንን ሃሳብ በጽኑ ተቃውማዋለች።
በተጨማሪም የትራምፕ አስተዳር ወደ ቻይና ወደቦች የሚጓዙ የፓናማ ሰንደቅ ዓላማን የሚያውለበልቡ መርከቦች ላይ የምታደርገው ቁጥጥር በመጨመር አጸፋ እርምጃ እየወሰደች ነው የሚል ክስ አቅርቧል።
የቻይና ምላሽ ምንድነው?
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊን ጂያን ሚያዝያ ላይ ውንጀላዎቹን "ሙሉ በሙሉ መሠረት የለሽ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል፤ አሜሪካ ለፖለቲካዊ ዓላማ ጉዳዩ አጣማዋለች በማለትም ከስሰዋል።
"ለረጅም ጊዜ ፓናማ ካናልን ይዞ የቆየው ማነው? ፓናማን በወታደሩ የወረረው፣ ሉዓላዊነቷን እና ክብርዋን በዘፈቀደ የደፈጠጠውስ ማነው?" ሲሉ ጠይቀዋል።
"ፓናማ ካናልን የሚመኘው፣ በዘላቂነት ገለልተኛ ሆኖ መቀጠል ያለበትን ይህንን ዓለም አቀፍ የውሃ መስመር የራሱ ግዛት ለማድረግ የሚሻውስ ማነው? መልሱ ግልጽ ነው" በማለት አክለዋል።
ቤይጂንግ የፓናማን የፓናማን ሉዓላዊነት እና የካናሉን ገለልተኛነት እንደምታከብር ትናገራለች።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በተደረገ ክርክር ላይ የቻይናው አምባሳደር ፉ ኮንግ "የአሜሪካ የውሸት ፈጠራ እና በቻይና ላይ የምትሰነዝረው መሠረት የለሽ ጥቃት ካናሉን ለመቆጣጠር ሰበብ መፈለግ እንጂ ሌላ አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።
በመሃል አጣብቂኝ ውስጥ የገባችውን ፓናማ የሚመሩት ፕሬዝዳንት ሆሴ ራኡል ሙሊኖ በበኩላቸው፣ አገሪቱ በካናሉ ላይ ሉዓላዊነት እንዳላት ደጋግመው አንስተዋል። ገለልተኛ አቋም መያዝ፣ ለተለየም ይሁን ዓለም አቀፍ ስጋት የሚሆን "አንዱ እና ምርጡ መከላከያ" እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህ ውዝግብ ለምን ተጠናከረ?
አሜሪካ እና ቻይና በፓናማ ካናል ጉዳይ የገቡበት አለመግባባት የካቲት ላይ ከፈነዳው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ የቀደመ ነው።
ቻይና በፓናማ ብቻ ሳይሆን በመላው ላቲን አሜሪካ ላይ የምታነሳቸው ከኢንቨስትመንት፣ ከስትራቴጂካዊ መሠረተ ልማት እና ከቀጠናዊ ተፅዕኖ ጋር የተያያዙ ስጋቶች ለዓመታት ሲብላሉ ቆይተዋል።
ተንታኞች የአሁኑን ውዝግብ የሚመለከቱት በጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ ምክንያት እንደመጣ መዘዝ ነው፤ አንድ ቀጠና ውስጥ የነበረ ግጭት በሌላ ቦታ ፉክክር ሲፈጥር የሚኖረው ዓይነት።
ፕሮፌሰር ኾርሄ ሃይነ፣ "በመካከለኛው ምሥራቅ በሚካሄደው ጦርነት እና በሆርሙዝ ውሽመጥ ላይ በተፈጠረው መስተጓጎል ምክንያት፣ ፓናማ ላይ የሚደርሰው ጫና አድጓል። በዚህ ምክንያት በቻይና እና በአሜሪካ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ጨምሯል" ይላሉ።
ፕሮፌሰር ፔሬዝም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ። "በሆርሙዝም ሆነ በቀይ ባሕር የምንመለከተው ተመሳሳይነት ያለው ሁኔታ ነው። በስትራቴጂካዊ የባሕር መስመሮች ላይ የሚነሱ ውዝግቦ የትልቅ ጂኦፖለቲካዊ ተቀናቃኝነቶች መድረክ እየሆኑ ነው" ብለዋል።
እንደ ፓናማ፣ የመን እና የባሕረ ሰላጤው አገራት ያሉ እነዚህን የባሕር መተላለፊያዎች የሚያስተዳድሩ ትንንሽ እና መካከለኛ አገራት "የመውጣት አቅማቸው እጅግ በተገደበበት የኃያላን ውዝግብ ምክንያት የሚጨምሩ ወጪዎችን" ለመሸከም እንደተገደዱም ገልጸዋል።