ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጊኒ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ቢያንስ 30 ሰዎች ሞቱ
በጊኒ መዲና ኮናክሪይ አቅራቢያ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ ቢያንስ 30 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቷ መንግሥት አስታወቀ።
አደጋው የደረሰው በመዲናዋ ዋና የቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ላይ ያለ የቆሻሻ ክምር በአቅራቢያው ባሉ ቤቶች ላይ በመውደቁ ነው።
ትናንት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ በደረሰው አደጋ ከሞቱት በተጨማሪ 22 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከል የስድስቱ ከባድ ጉዳት መሆኑ ተገልጿል።
አደጋው የደረሰበት የዳሬሰላም ሰፈር አስተዳዳሪ ላንሲን ሲይላም ቀደም ብለው የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
"እስካሁን 18 አስክሬኖችን አውጥተን ወደ ሆስፒታል አስክሬን ክፍል ወስደናል" ብለዋል።
ሲሬ ዲያሎ የተባለች ሴት በቦታው ላሉ ጋዜጠኞች አምስት ልጆቿ መሞታቸውን ተናግራች። "ልጆቼን በሙሉ አጥቻለሁ። ማድረግ የምችለው በእግዚአብሔር ላይ መታመን ብቻ ነው" ብላለች።
በርካቶች በፍርስራሹ ሥር ተቀብረው ሊሆን ስለሚችል የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችልም ስጋት አለ።
ከፍተኛ ዝናብን ተከትሎ ከደረሰው አደጋው የተረፉ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ በአካባቢው ወሳኝ የሆኑ መሣሪያዎች እንዲሁም ወታደሮችን ጨምሮ የሰው ኃይል መሰማራቱን መንግሥት ገልጿል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሕይወት አድን ሠራተኞች ርብርብ እያደረጉ ነው። የሕይወት አድን ሠራተኞች እንደ ተራራ የተቆለለውን ቆሻሻ ለመጥረግ ስካቫተር ሲጠቀሙ ታይተዋል።
የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር - ጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ማማዶው ኦውሪ ባህ የነፍስ አድን ጥረቱን እና ሁኔታውን ለመገምገም የአደጋውን ሥፍራ ጎብኝተዋል።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በቆሻሻ መጣያ ሥፍራው አደጋ ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። እአአ በ2017 እዚያ ሥፍራ ላይ የቆሻሻ ክምር ተንሸራቶ 10 ሰዎች መመሞታቸው ይታወሳል።
ጊኒ በኅዳር ወር ግዙፍ የማዕድን ማውጫ ፕሮጀክት ያስጀመረች ሲሆን፣ በዓለም ላይ ትልቁን የባክሳይት እና የብረት ማዕድን ክምችት ያላት አገር ናት።
ነገር ግን የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ደካማ መሠረተ ልማት እና ድህነት አንቆ ይዟታል።
የዓለም ባንክ በሚያዚያ ወር ባወጣው ሪፖርት ከ15.1 ሚሊዮን ሕዝቧ ውስጥ 3.7 ሚሊዮን የሚሆኑት በቀን ከ4.20 ዶላር ባነሰ ገቢ እንደሚኖሩ ይፋ አድርጓል።
የጊኒ የአገር ግዛት አስተዳደር ሚኒስትር ጄናብ ቱሬ ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቁት መንግሥት የቆሻሻ መጣያውን ደህንነቱ የተጠበቀ ስላልሆነ እንደሚዘጋው አስታውቀው ከኮናክሪ ውጭ ሌላ ስፍራ እንደሚዘዋወር ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ እሁድ ዕለት የደረሰውን ጉዳት ለመመልከት እና እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ለመገምገም የቆሻሻ መጣያ ስፍራውን ጎብኝተዋል።
መንግሥት የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ሕዝቡ "መረጋጋት፣ አጋርነት ማሳየት እና የሕይወት አድን ሠራተኞችን እና የመንግሥትን መመሪያዎችን በጥብቅ መከተል" እንዳለበት አሳስቧል።