ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለ ፓስፖርት አይጦች እና ስለ ቲቢ የሚመራመሩት ኢትዮጵያዊ
አይጦቹ፤ የሳምባ በሽታ (ቲቢ) ያለባቸውን ሰዎች ለመለየት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ናሙናዎች አነፍንፈው በጠረን ለይተዋል። ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው እንዳይያዙ ታድገዋል።
አይጦቹ፤ የጦርነት አውድማዎችን አነፍንፈው በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር መሬትን ከተቀበሩ ፈንጂዎች ነጻ አውጥተዋል።
ሂሮራትስ (HeroRATs) ተብለው ነው የሚጠሩት። በሳይንሳዊ ስማቸው Cricetomys Snsorgei ልንላቸው እንችላለን።
አፍሪካን ጃይን ትፖችድ ራትስ (African Giant Pouched Rats) በሚለው መጠሪያቸውም ይታወቃሉ። ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በብዛት ይኖራሉ። በኢትዮጵያ እና ታንዛንያ ተራራማ አካባቢዎች እንዲሁም በማዕከላዊ አፍሪካ በቀላሉ ይገኛሉ።
እንደ ሌሎቹ የአይጥ ዝርያዎች አይደሉም። ሳምባ በሽታ (ቲቢ) እና ፈንጂን አነፍንፎ ከመለየት ባሻገር እንደ ርዕደ መሬት ያሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሲከሰቱ በፍርስራሽ ስር ተቀብረው በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ያፈላልጋሉ።
ዶ/ር ተፈራ በላቸው ስለእነዚህ አይጦች አውርተው አይጠግቡም። በአይጦቹ ታግዞ ምርምር የሚያደርገው የቤልጂየም ተቋም የሆነው አፖፖ የተባለው ተቋም ቀጣናዊ ኃላፊ ናቸው።
አፖፖ በኢትዮጵያ፣ በታንዛንያ እና በሌሎችም አገራት ቅርንጫፎች አሉት። በተለይም በሳምባ በሽታ ላይ ምርምር ውጤታማ ሆነዋል።
የሳምባ በሽታ ከሚፈታተናቸው 30 የዓለም አገራት አብዛኞቹ የሚገኙት በአፍሪካ ነው። ስለዚህም፤ አፖፖ በናይጄሪያ፣ በሴራሊዮን፣ በአንጎላ እና በሌሎችም የአፍሪካ አገራት ሙከራዎች ያካሂዳል።
ዶ/ር ተፈራ የሕክምና ዶክተር ናቸው። ቦትስዋና እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እንዲሁም ለ15 ዓመታት ገደማ በአሜሪካ የበሽታ መካላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ሠርተዋል።
አሁን ቢሯቸው በታንዛንያ፣ ሞሮጎሮ ነው። እናም ስለ አይጦቹ ለሰዓታት ማውራት ይችላሉ።
እሳቸውን ጨምሮ አብረዋቸው የሚሠሩ ተመራማሪዎች የማኅበራዊ ሚዲያ መለያ ምሥላቸው (ፕሮፋይል ፒክቸር) አይጥ ትከሻቸው ላይ አድርገው የተነሱት ፎቶ ነው።
አይጦቹ የምርምር ቡድኑ አባላት ናቸው። ስም አላቸው፣ ፓስፖርት አላቸው፣ የጡረታ ማዕከልም አላቸው።
አይጦቹ አንዳንዴ መሥራት 'ይደብራቸዋል'፤ እናም ብዙ ኃላፊነት የተሸከሙት እነዚህ አይጦች መዝናኛ ሰዓት ይመደብላቸዋል።
ቲቢን ጨምሮ በሌሎችም ሕመሞች ላይ ጥናት የሠሩት ዶ/ር ተፈራ አይጦቹን "ላቭሊ [ተወዳጅ] እንሰሳት ናቸው" ብለው ነው የሚገልጿቸው።
አይጦቹ የሚራቡት ታንዛንያ ባለው የአፖፖ ማዕከል ውስጥ ነው።
አይጦች እና ሳይንስ
እንሰሳትን ለተለያዩ የሳይንስ ምርምሮች ወይም ሙከራዎች መጠቀም የተለመደ ነው። ለምሳሌ ውሾች የተቀበረ ፈንጂ አነፍንፈው እንዲለዩ ይሠለጥናሉ።
የአይጦች የማሽተት አቅም ግን ወደር የለሽ ነው።
የሰው ልጆች አፍንጫቸው ላይ 400 የነርቭ ጫፍ አላቸው። የውሾች ደግሞ ከ800 አስከ 900 ይደርሳል። የአይጦች የነርቭ ጫፎች 1200 ይጠጋሉ። ለዚህም ነው ከፍተኛ የማሽተት አቅም ያላቸው።
ዶ/ር ተፈራ እንደሚሉት፣ አፖፖ በዋናነት የተመሠረተው አይጦች ፈንጂ አነፍንፈው እንዲለዩ ነው። ውሾችም ፈንጂ ቢያነፈንፉም አይጦች በመጠናቸው አነስተኛ መሆናቸው ተመራጭ ያደርጋቸዋል።
አፍሪካን ጃያንት ፖችድ ራትስ ክብደታቸው ከ1.5 ኪሎግራም አይዘልም። ጭራቸውን ጨምሮ 90 ሴንቲ ሜትር ይረዝማሉ። አይጦቹ ምግብ ከተሰጣቸው ሌላ ተጨማሪ የሚጠይቁት ነገር የለም።
እነዚህ ፈንጂ በማነፍነፍ እና ሳምባ ነቀርሳን በመለየት ረገድ ተመራጭ የሚባሉት የአይጥ ዝርያዎች ቤት ውስጥ ከሚገጥሙን አይጦች ይለያሉ።
ሳይንስ የሚመርጣቸው አይጦች በቀላሉ ይላመዳሉ። እስከ 11 ዓመት ይኖራሉ። የቤቶቹ አይጦች ከሁለት ዓመት በላይ አይኖሩም።
ታታሪዎቹ የአፖፖ አይጦች ተግተው ስምንት ዓመት ይሠሩና ጡረታ ይወጣሉ።
የአይጦች ጡረታ
ታንዛንያ ያለው የጡረታ ማዕከል የተዘጋጀው የአይጦችን ተፈጥሯዊ መኖሪያ በማስመሰል ነው። ቤቱ በሸክላ እና በሳር የተሠራ ነው።
ጡረተኞቹ አይጦች ፀሐይ ይሞቃሉ። ይዝናናሉ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። በጣሪያ ላይ ይሽከረከራሉ። የሚወዱት ምግብ ይሰጣቸዋል።
አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ሀባብ እና የለውዝ ቂቤ አብዝተው ይወዳሉ።
"ሠርተው ጨርሰው ጡረታ ከወጡ በኋላ ደስተኛ ሆነው እንዲያሳልፉ እናደርጋቸዋለን" ይላሉ ዶ/ር ተፈራ።
አይጦች እንዴት ይሠለጥናሉ?
አይጦች ተወልደው እስከ አራት ሳምንት ዓይናቸው አያይም። መጀመሪያ ዓይናቸውን ሲገልጡ የሚመለከቱት አሠልጣኞቻቸውን ነው።
ተወልደው ከአንድ እስከ ሁለት ወር ድረስ ፀሐይ እንዲሞቁ በማስወጣት እና በማስገባት ሰዎች እንዲላመዱ ይደረጋሉ።
ከሦስት ወራት በኋላ 'ክሊከር ትሬኒንግ' የተባለ ሥልጠና ይወስዳሉ። ስለ ድምጽ እና ምግብ ትስስር የሚማሩበት ነው።
መጀመሪያ ድምጽ እንዲሰሙ ተደርጎ ከዚያ ምግብ ይሰጣቸዋል።
"የሳምባ ነቀርሳ ታማሚ ናሙና ወይም የፈንጂ ናሙና ወስደን ነው የምናሠለጥናቸው። ናሙናዎቹን እያሸተቱ ድምጽ እንዲሰሙ ይደረጋል። ከዚያም ድምጽ እና በሽታን እንዲሁም ድምጽ እና ፈንጂን ማስተሳሰር ይማራሉ ማለት ነው። በሽታውን ወይም ፈንጂ አሽትተው ሲያገኙ ምግብ እንደሚሰጣቸው ይማራሉ" ሲሉ ባለሙያው ሒደቱን ያብራራሉ።
የዚህ ሥልጠና መነሻ የፓቭሎቭ ጽንሰ ሐሳብ ነው።
ጽንሰ ሐሳቡ የሩሲያዊው የሥነ ልቦና ባለሙያ ኢቫን ፓቭሎቭ ምርምር ውጤት ነው።
በአውሮፓውያኑ በ1890ዎቹ የተሠራው ምርምር፤ ደውል አጩሆ ለውሻ ምግብ በመስጠት ውሻው የደውል ድምጽን ከመመገብ ጋር እንዲያስተሳስር ያደረገ ነበር።
የአፖፖ አይጦች ከዘጠኝ ወራት ሥልጠና በኋላ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የሙያ ብቃት ምዘና ይደረግላቸዋል።
በእርግጥ አይጦች በደንብ ሥልጠና ከተሰጣቸው የተማሩትን ነገር ለመከወን የተመቻቸ ተፈጥሮ አላቸው።
ሆኖም አንዳንዶቹ አይጦች በሽታ በማነፍነፍ እምብዛም ውጤታማ ካልሆኑ ወደ ፈንጂ ማነፍነፍ ወይም ወደሌላ ክፍል ይዛወራሉ።
አይጦቹ፤ የዝሆን ቀንድና ጥርስን ጨምሮ የእንሰሳት አካላት ሕገ ወጥ ዝውውርን ለመግታት የአገራት ድንበር ላይ ፍተሻ ያደርጋሉ። በአውሮፕላን ማረፊያ አነፍናፊ አይጦችን ማሰማራት ተለምዷል።
የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን እንዲያገኙም ይሠለጥናሉ። ለምሳሌ ርዕደ መሬት ሲገጥም፣ አይጦች መጠናቸው ትንሽ ስለሆነ በየቦታው እየተሽሎኮሎኩ በሕይወት ያሉ ሰዎች ያስሳሉ።
ጀርባቸው ላይ ካሜራ አድርገው በመዘዋወር ሰው ሲያገኙ ምልክት ይሰጣሉ።
የዚህ ሁሉ መነሻ እአአ በ1997 አካባቢ አንድ ቤልጂየማዊ አይጦች ፈንጂ እንዲያነፈንፉ ማስተማሩ ነው። ወደ 2007 አካባቢ ሳምባ ነቀርሳ ላይ ምርምር ተጀመረ።
የአይጦቹ ረዥም ዕድሜ፣ ከሰው ጋር በቀላሉ መላመዳቸው፣ ትልቅ ስለሆኑ ጠንካራ የማሽተት አቅም ያላቸው መሆኑ ተመራጭ አድርጓቸዋል።
"የእኛ አይጦች ቢለቀቁ የትም አይሄዱም። ወጥተው ተዝናንተው ይመለሳሉ። ለማዳነታቸው ልዩ ያደርጋቸዋል" ብለው ነው ዶ/ር ተፈራ የሚገልጿቸው።
አይጦቹ ሰው ከሰው ይለያሉ። አሠልጣኞቻቸውን ያውቃሉ። አሠልጣኞቹም የአይጦቹን ባህሪ ያውቃሉ።
ዋነኛ ትኩረታቸው ሥራቸውና ምግባቸው ላይ ነው። ሲራቡ፣ ሲጨነቁ፣ ሲታመሙ አልያም መሥራት ሳይፈልጉ ሲቀሩ ምን ዓይነት ምልክት እንደሚያሳዩ ይታወቃል።
አይጦችና ስሜቶቻቸው
ዶ/ር ተፈራ እንደሚሉት፣ አይጦች የስሜት ወዋዠቅ ሊገጥማቸው ይችላል። ሲታመሙ አልያም ሲርባቸው በተለያየ መንገድ ይጠቁማሉ።
መሥራት የማይፈልጉበት ቀን ሲኖር ከመተው ውጭ ምንም ማድረግ አይቻልም። አንዳንዴ ደግሞ ከተለመደው በላይ ቀልጣፋ ይሆናሉ።
"እንደ መደነስ የሚቃጣቸውም አይጦች አሉ። የሠለጠኑበትን ነገር በትክክል ሲያገኙ እንደ ዳንስ ይቃጣቸዋል" ይላሉ ባለሙያው።
ማታ በርዷቸው ሲያድር፣ ምግብ ሲቀየር ካልተስማማቸው ወይም ከታመሙ የጭንቀት መጠናቸው ከፍ ይላል።
አይጦች ፊታቸውን በጣም ደጋግመው ይጠርጋሉ። በሥራ መሀል ፊታቸው ላይ ያለውን ጭራ ይጠርጋሉ። ይሄ አንድ ጭንቀታቸውን የሚያስወግዱበት መንገድ ነው።
ባለ ፓስፖርቶቹ አይጦች
አይጦቹ ለቪዛ ባያመለክቱም ፓስፖርት አላቸው። ከአገር አገር ይዘዋወሩበታል።
"ቆንጆ ቆንጆ ስምም አላቸው። በስማቸው እየተጠሩ ነው ሥራ የሚሠሩት" ይላሉ ዶ/ር ተፈራ።
ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ኦባማ፣ ሴሪና እና ማጋፉሊ የሚባሉት ይጠቀሳሉ። ማጋፉሊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
አይጦቹ የራሳቸው ሐኪም አላቸው። ክትባትና ቫይታሚንም ይሰጣቸዋል።
በዓለም የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ማጋው የተባለው አይጥ በተለየ ሁኔታ በመሥራት ዓለም አቀፍ ዝናን ተቀዳጅቷል። ከአራት ዓመት በፊት ሲሞትም ዜና ነበር።
200 ሺህ ናሙና አነፍንፋ ከ3ሺህ በላይ የሳምባ ነቀርሳ ያገኘችው ካሮሊና ጡረታ ስትወጣም ትልቅ ዜና ነበር።
አይጦች ሲሞቱ. . .
እንኳንስ ከእንሰሳ ጋር ከቁስም ጋር ትስስር መፍጠር አይቀርምና፣ ጡረታ የሚወጡት ባለፓስፖርት አይጦች ሲሞቱ በአፖፖ ሐዘን ያንዣብባል። በአግባቡ ሽኝት ይደረግላቸዋል።
ዶ/ር ተፈራ "እኛጋ አይጦቹ ሲሞቱ ዜና ነው። ቲማችን [የቡድናችን አካል] ናቸው፤ ቫልዩአችን [መገለጫችን] ናቸው" በማለት ስሜቱን ይገልጻሉ።
አንዳንድ አይጦች በኢትዮጵያ ወይም በታንዛንያ እየሠሩ ከሁሉም ተመራማሪዎች ጋር ባይተዋወቁም ሲሞቱ ባለሙያዎቹ ሐዘኑን ይጋራሉ።
ከሕልፈታቸው በኋላ በቀዶ ሕክምና የሞቱበት ምክንያት ተጣርቶ ይመዘገባል። ዕድሜያቸው ደርሶ ከሚሞቱት አይጦች ባሻገር ካንሰር፣ ስኳር ወይም ኢንፌክሽን የሚገድላቸውም አሉ።
አይጦች ይሳሳታሉ?
አይጦቹ የብቃት ምዘና ሲደረግላቸው የሚለካው የስህተት መጠናቸው ነው።
እንኳንስ አይጦች ዘመነኛ ማሽንም በስህተት 'ፎልስ ኔጌቲቭ' ወይም 'ፎልስ ፖዘቲቭ' ይሰጣል።
አይጦች ከተወሰነ ደረጃ በላይ እንዳይሳሳቱ ወይም ከተቀመጠው ደረጃ በታች እንዳይሠሩ መለኪያ ተቀምጦላቸዋል።
"የዓለም ጤና ድርጅትም መቶ በመቶ በሽታው ይገኛል ብሎ አይጠበቅም። 98% ትክክል ቢሆን ብሎ ነው የሚያስቀምጠው" ይላሉ ተመራማሪው።
ሳምባ ነቀርሳ የሌለበት ሰው አለበት ብሎ የተሳሳተ ውጤት ማሳየት (ፎልስ ፖዘቲቭ) ጤናማ ሰዎች ጎጂ መድኃኒት እንዲወስዱ ያደርጋል። ሕመሙ ያለበት ሰው የለበትም (ፎልስ ኔጌቲቭ) ቢባል ግን ሌሎች ምልክቶች ታይተው ናሙናው በድጋሚ ስለሚመረመር በሽታው በሰውነቱ መኖሩ ሊደረስበት ይችላል።
በስህተት ሕመሙ አለ ወይም የለም ብሎ መበየን (Sensitivity and specificity) እንዲመጣጠኑ እንደሚደረጉ ዶ/ር ተፈራ ያስረዳሉ።
አይጦች ያዳኗቸው ሰዎች
Training rats to save lives (አይጦችን በማሠልጠን ሕይወት ማዳን) የአፖፖ መሪ ቃል ነው።
አይጦቹ፤ እአአ ከ2007- 2024 ከአንድ ሚሊዮን በላይ ናሙና ከኢትዮጵያ፣ ታንዛንያና ሞዛምቢክ አነፍንፈዋል።
ከእነዚህ መካከል ከ620 ሺህ በላይ ናሙናዎች ተመርምረው ከ32 ሺህ በላይ በሆኑት ናሙናዎች ውስጥ ሳምባ ነቀርሳ እንዳለ በቤተ ሙከራ ተረጋግጧል።
አይጦቹ ናሙናዎቹን ከማነፍነፋቸው ቀድሞ በቤተ ሙከራ ምርመራ ሲደረግ ሕመሙ እንዳለ አልታወቀም ነበር። የአይጦቹን ጥቆማ ተከትሎ ግን በበሽታው የተያዙ ሰዎችን መለየት ተችሏል።
አንድ ሰው ቲቢ ካለበት ከ10 እስከ 15 ሰዎች ሊያስይዝ ይችላል። አይጦቹ 32ሺህ ናሙናዎች ላይ በሽታው መኖሩን ባያውቁ ኖሮ ሕሙማኑ በሽታውን ሊያስተላልፉ የሚችሉበትን መጠን በማስላት፤ ወደ 400 ሺህ ሰዎችን ከሳምባ ነቀርሳ መታደግ እንደተቻለ ዶ/ር ተፈራ ይናገራሉ።
አንድ አይጥ አንድ ናሙና እንዲያነፈንፍ የሚወጣው አንድ ዶላር ቢሆን ነው። በማይክሮስኮፕ ቢመረመር እስከ ሦስት ዶላር ይከፈላል።
ዘረ መል የሚመረመርበት ሞለኪውላር ቴስት ከ10 እስከ 18 ዶላር ይፈጃል። ማሽኑ ብቻውን እስከ 18 ሺህ ዶላር ነው የሚያወጣው።
በአዲስ አበባ ወደ 60 ከሚጠጉ ሆስፒታሎች ጋር አብረው ይሠራሉ።
ሳምባ ነቀርሳ በከፍተኛ መጠን በተስፋፋባቸው እንደ ሕንድ፣ ሜክሲኮና ናይጄሪያ ባሉ አገራት ሥራቸውን ማስፋፋትም ይፈልጋሉ። አገራት በራቸውን ክፍት እንዲያደርጉም አዘውትረው ይጠይቃሉ።
ከ60 በላይ በሚሆኑ አገራት በጦርነት ወቅት ፈንጂዎች ተቀብረዋል። የአፖፖ አይጦች በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር መሬት ከፈንጅ ነጻ አድርገዋል።
አይጦቹ፤ በ11 አገራት ውስጥ ፈንጂ ያነፈንፋሉ።
ሞዛምቢክን እንደ ምሳሌ ብንወስድ በእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት የተቀበሩ ፈንጂዎች በአይጦቹ አማካይነት ተለቅመው መሬቱ ለአርሶ አደሮች ተሰጥቷል።
ዘመነኛ የቲቢ መሣሪያና አይጦች
አፖፖ በሳምባ ነቀርሳ ላይ ባደረጋቸው ምርምሮች ከተገኙ ውጤቶች መካከል መድኃኒት የሚቋቋም ሳምባ ነቀርሳ ላይ የተሠራውን ዶ/ር ተፈራ ይጠቅሳሉ።
መድኃኒት የለመደ ቲቢን ፈልጎ ማግኘት ቀላል አይደለም። አይጦች ናሙናውን አሽተተው በሽታውን እንዲያገኙ በማድረግ አፖፖ ያገኘውን ውጤት እአአ በ2023 ይፋ አድርጓል።
"አይጦቹ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቤተሰቦችን ሄደው ቢያሸቱ መድኃኒት የለመደ ቲቢን ለመለየት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ይሄ ትልቅ ከሚባሉት ግኝቶች አንዱ ነው" ይላሉ ባለሙያው።
እስከ ቅርብ ጊዜ አይጦች ከሕጻናትና አዋቂዎች የሚወሰዱ ናሙናዎችን ሲያነፈንፉ ያለው ልዩነት በግልጽ አይታወቅም ነበር።
እአአ በ2024 በታተመ ጥናት እንደተመለከተው፤ አይጦች ከአዋቂዎች በበለጠ ሕጻናት ላይ በሽታውን የማግኘት ዕድላቸው ሁለት እጥፍ ከፍ ያለ ነው።
ሌላው የአፖፖ ጥናት፤ በናሙና ውስጥ የቲቢ ባክቴሪያ መጠን ውስን ሆኖ በማይክሮስኮፕ ሊታይ ካልቻለ አይጦች በማነፍነፍ የሚያገኙትን ውጤት ይመለከታል።
"አይጦች ከሌሎች ማሽኖች በተሻለ ለውጥ እንዳመጡ የዓለም ጤና ድርጅትም ዕውቅና ሰጥቶታል" ይላሉ ተመራማሪው።
ናሙና በማይክሮስኮፕ ከታየ በኋላ አይጦች እንዲያነፈንፉት ይደረግ ነበር። እአአ በ2010 ከማይክሮስኮፕ የላቀ ውጤት ያለው መሣሪያ ተሠርቷል።
በኢትዮጵያም በታንዛንያም ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑ ሆስፒታሎች የሚጠቀሙት ይህንን መሣሪያ ነው።
"ከዚህ ዘመነኛ ቴክኖሎጂ ጋር አይጦች አብረው ይሄዳሉ የሚለውን ያወቅነው በ2025 ነው። ዓለም ላይ አለ የሚባለው የቅርብ ጊዜ ቴክኖሎጂ ከሚሰጠው ውጤት እኩል እንደሚሰጡ ታውቋል" ሲሉ ዶ/ር ተፈራ ይገልጻሉ።
የቲቢ ባክቴርያ በናሙና ውስጥ እያለ የለም የሚል ውጤት ማግኘት ላይ በተደረገው ምርምር፣ የአይጦቹ በሽታውን የመለየት ችሎታ ከ90 በመቶ በላይ መሆኑን ማወቅ ተችሏል።
ስለዚህ የቲቢ መመርመሪያ መሣሪያ ባይኖርም እንኳን አይጦችን እንደ አማራጭ መጠቀም ይቻላል። የአይጦቹ ውጤታማነት የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን ደረጃ እንደሚመጥን ባለሙያው ይናገራሉ።
"በዓለም እስካሁን ባልታየ ሁኔታ በየትኛውም ክሊኒክ በአይጦች ቲቢን ማወቅ የሚቻልበት ነው። በሳምባ ነቀርሳ ምርምር ጌም ቼንጀር [ታሪክ ለዋጭ] ሊሆኑ ይችላሉ። አገራት ምርምሩን እንድናደርግ ፈቅደው በራቸውን ክፍት እንዲያደርጉልንም እንፈልጋለን" ሲሉም ያክላሉ።
'ትክክለኞቹ አይጦች'
እንደ ሳይንቲስት ከአይጦቹ ባህሪ በአጠቃላይ ዶ/ር ተፈራ የሚገረሙት በትክክለኛነታቸው ነው። አንድ ናሙናን ለሦስት ሰከንድ ያሸታሉ።
በናሙናው ቲቢ ከሌለ ሦስት ሰከንድ ሳይሞላ ጥለውት ያልፋሉ።
አንድ አይጥ በ20 ደቂቃ ውስጥ ወደ 100 ናሙና ያነፈንፋል። አንድ የቤተ ሙከራ ባለሙያ በማይክሮስኮፕ 100 ናሙና ለመመልከት እስከ ሦስት ቀናት ይወስድበታል።
"ፍጥነታቸውና ትክክለኛነታቸው ሁሌም ያስደንቀኛል፤ ያስደስተኛል። ጥልቅ የማሽተት ችሎታቸውን መንከባከብ አስፈላጊ ነው" ይላሉ ባለሙያው።
አይጦችን የሚገልጹት "ላቭሊ [ተወዳጅ] እንሰሳት" ብለው ነው።
ከአይጦች ጋር ሲሠሩ ከሚያስገርማቸው ባህሪያቸው መካከል ፊታቸውን ደጋግመው የሚያጸዱበት መንገድ ነው።
ከሥራ ፋታ ወስዶ እንደ አዲስ ለመጀመር (ሪፍሬሽ) ለማድረግ ፊታቸውን ያጸዳሉ። አይጦች ንጹህ እንሰሳት ናቸው የሚባሉትም በዚህ ምክንያት ነው።
"ፍቅራቸውን ለመግለጽ ሲሞክሩም ፊታቸውን ያጸዳሉ። ሲጨነቁ እረፍት ለማድረግም ይጠቀሙበታል። በተደጋጋሚ ፊታቸውን በማጽዳት ራሳቸውን 'ሪፍረሽ' ሲያደርጉ በጣም ነው ደስ የሚለኝ። ቶሎ ስለሚላመዱ ትከሻችን ላይ ይሯሯጣሉ። እጃችን ላይ ይሯሯጣሉ። ምቾት ተሰምቷቸው ሲታዩ ደስ ይላሉ።"
አይጦቹ ወደ ሥራ ከመሰማራቸው በፊት ቲቢ የሌለበት ሰው ናሙና ብቻውን ማሽተት ይለምዳሉ። ሲያነፈንፉ ድምጽ እንዲሰሙ ይደረጋል።
'ቃ' የሚል ድምጽ ሲሰሙ ምግብ ይሰጣቸዋል። ማሽተት- ቃ የሚል ድምጽ መስማት- ምግብ ማግኘት የሚለውን ቅደም ተከተል አወቁ ማለት ነው።
ከዚያም ባክቴሪያው ያለበትና የሌበትን ናሙና ጎን ለጎን እንዲያሸቱ ይደረጋል። በሽታ ያለበትን ሲያነፈንፉ 'ቃ' ይልና ምግብ ይሰጣቸዋል። የሌለበት ሲያነፈንፉ ምንም አይሰጣቸውም።
የሚያነፈንፏቸው ናሙናዎች ቲቢ አለበቸው ተብለው የተጠረጠሩ ናቸው። ሳይንቲስቶቹም አይጦቹም በሽታው መኖሩን አያውቁም።
የአይጦቹን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ከናሙናዎቹ መካከል ቲቢ እንዳለባቸው የተረጋገጡ ናሙናዎች እንዲካተቱ ይደረጋል።
ባክቴሪያው እንዳለባቸው አይጦች ጥቆማ ያደረጉባቸው ናሙናዎች በማይክሮስኮፕ ወይም በሞለኪውራል ቴስት ይረጋገጣሉ።
"ከበሽታው የሚመነጭ ወደ ስድስት ዓይነት ኬሚካል አለ። ያንን አደባልቀው የማሽተት አቅማቸው ከፍተኛ ነው" ይላሉ ዶ/ር ተፈራ።
ለምንድን ነው አይጥ የምንፈራው?
ፍርሃት ሁሌም ምክንያታዊም መነሻ ባይኖረውም በርካቶች አይጦችን ይፈራሉ፣ ይጠሏቸዋልም።
ይሄ የአይጦች ፍርሃት ጉዳይ ከአፖፖ ምርምሮች ጋር ባይገናኝም፣ እንደ ባለሙያ ምክንያቱን እንዲያስረዱን ዶ/ር ተፈራን ጠይቀናል።
እሳቸውም መላ ምቶችን ያስቀምጣሉ።
አይጦች ምግብ ፍለጋ የማይገቡበት የለም። በዚህ ወቅት መርዝ ነክተው ወይም በልተው ሊሆን ስለሚችል 'ይመርዙናል' ብለው ሰዎች ይፈሯቸዋል።
አይጦች በበኩላቸው ትንሽ ስለሆኑ በሰዎች ሊጠቁ እንደሚችሉ በማሰብ ይሸሻሉ። ራሳቸውን የሚከላከሉት በማሽተት ነው። አሽትተው ይሸሻሉ። መሸሽ ካልቻሉ ራሳቸውን የሚከላከሉት በመንከስ ነው። ንክሻቸው ደግሞ በጣም ስለሚያም ሰዎች ይፈሯቸዋል።
ዶ/ር ተፈራ ሰዎች አይጦችን ባይፈሩ ነው የሚመርጡት።
"ኢኖሰንት [ምስኪን] ናቸው። ሊፈሩ አይገባም። አይጦች ጠላቶች ሳይሆኑ አጋሮች ናቸው። ሥራቸውን ይሠራሉ እንጂ ተንኮል የላቸውም። እናም እንውደዳቸው" ይላሉ።
ብዙዎች አይጦች ጠቃሚ ናቸው ብለው ለማመን ቢቸገሩም፤ ሥራቸውን ሲያዩ አለመደነቅ አይቻልም።
የሰዎችን ጤና በመጠበቅና ሕይወትን በማዳን ረገድ "እንዲያውም ከአንዳንድ ሰዎች ይልቃሉ" ብለው ነው ባለሙያው የሚገልጿቸው።