ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ቴስላ መኪናዎች በደኅንነት ስጋት ምክንያት እንዲሰበሰቡ ተደረገ

የቴስላ መኪና የበር እጀታ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከዕይታ የተሰወሩ የበር እጀታዎች የኤሌክትሪክ መኪኖች የተለመደ ዲዛይን ሆኗል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አወዛጋቢ የሆኑት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የበር እጀታ ዲዛይን በቻይና ከአራት ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎችን በድጋሜ ለመሰብሰብ ምክንያት ሆነ።

2.98 ሚሊዮን ቻይና ሠራሽ ቴስላ መኪናዎችን ያካተቱት እነዚህ ተሽከርካሪዎች ድጋሜ እንዲሰበሰቡ የተደረገው በደኅንነት ስጋት ምክንያት ነው። ቅንጡዎቹ ተሽከርካሪዎች የተገጠመላቸው ድብቅ የበር እጀታዎች በአደጋ ጊዜ በቀላሉ ለመዝጋት እና ለመክፈት አስቸጋሪ ናቸው።

በዚህም ምክንያት ዢፔንግ፣ ዢኦሚ እና ጊሊይን ጨምሮ ሌሎች የቻይና መኪና አምራቾችም የእርምጃው አካል ሆነዋል።

የቢሊየነሩ ኤሎን መስክ ቴስላ መኪኖች የበር እጀታዎች ድብቅ እና የማይታዩ ሲሆኑ በሩ የሚከፈተው ባለቤቱ ወደ መኪናው ሲጠጋ ነው። በዲዛይኑ ላይ ስጋት የተፈጠረውም በቻይና ዢያኦሚ ቴስላ መኪና ያጋጠመው የኃይል መቋረጥ በሩ እንዳይከፈት ካደረገው በኋላ እንደሆነ ተነግሯል።

እርምጃውን ተከትሎ የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ "የተወሰኑ 3፣ ዋይ፣ ኤስ እና ኤክስ ሞደል መኪኖቹን የሰበሰበው የበር እጀታቸው ከመኪናው ቀለም ጋር ተመሳሳይ በመሆናቸው ለመለየት እና ለመጠቀም አስቸጋሪ በመሆናቸው" እንደሆነ ገልጿል።

" ይህም ተሳፋሪዎችን ወይም የሕይወት አድን ሠራተኞች በአደጋ ጊዜ በሮቹን በፍጥነት ለመክፈት ሊያስቸግራቸው እንደሚችል" ገልጿል።

ቴስላ ጨምሮም የሚሰበሰቡት ተሽከርካሪዎች ላይ ማስጠንቀቂያ እንደሚጽፍ እና በግጭት ወቅት መስኮታቸው በራሱ እንዲከፈት ሶፍትዌራቸውን [መተግበሪያቸውን] አሻሽላለሁ።" ብሏል።

ሆኖም መኪና አምራቹ ኩባንያ በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ተመሳሳይ እርምጃ ይወስድ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ቢቢሲ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ቴስላን፣ ዢፔንግ ፣ ዢኦሚ እና ግሪሊይን ጠይቋል።

የቻይና ብራንዶች ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ የቴስላ ሞዴል የሆነው ኤስ ሴዳንን "የሚያምር" ዲዛይን በፍጥነት ለመኮረጅ ከሞከሩ በኋላ የተደበቀው እጀታ ዲዛይን ጥቅም "ተጋኗል" ሲሉ የሲኖ አውቶ ኢንሳይትስ መሥራች ቱ ሌ ተናግረዋል።

የማስጠንቀቂያ መለያዎችን እና የሶፍትዌር [ መተግበሪያዎችን] ማሻሻልም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ አይደለም ብለዋል።

የካቲት ወር ላይ የቻይና ባለሥልጣናት የተደበቁ የበር እጀታዎችን መከልከላቸውን አስታውቀዋል።

ከመጪው ጥር ጨምሮ ተግባራዊ የሚሆኑት አዳዲስ ሕጎች እንደሚያሳዩት፣ በቻይና መኪኖች በሮቻቸው ከውስጥም ሆነ ከውጭ በእጅ መከፈት ሲችሉ ብቻ እንዲሸጡ ይፈቀዳል።

የአሜሪካ የደኅንነት ተቆጣጣሪዎችም የቴስላ የበር እጀታዎች በድንገት መሥራታቸውን አቁመው ሕፃናት ከመኪኖቹ ውስጥ መውጣት ሳይችሉ ከቀሩ በኋላ በምርቱ ላይ ያለውን ስጋት ገልጾ ነበር።

ሐምሌ ላይም የአሜሪካ ብሔራዊ የፈጣን መንገድ ትራፊክ ደኅንነት አስተዳደር ለሁሉም የመኪና አምራቾች አዲስ መደበኛ የደኅንነት መስፈርት እንዲቀመጥ ሃሳብ አቅርቧል።