ጸረ-ሴማዊነት በአስደንጋጭ ሁኔታ ማንሰራራቱን አንድ ጥናት አመለከተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም ዙሪያ ጸረ-ሴማዊነት በከፍተኛ ሁኔታ እያንሰራራ መሆኑን በቴል አቪቭ ዩኒቨርስቲ የተደረገ ጥናት አመለከተ።
የጸረ-ሴማዊነት መገለጫ የሆኑ ክስተቶችም ባለፈው ዓመት በአስደንጋጭ ሁኔታ መጨመራቸውን ይሄው ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን እና አውስትራሊያ በከፍተኛ ሁኔታ ጸረ ሴማዊነት እያንሰራራባቸው ካሉ ሃገራት መካከል መሆናቸውን አትቷል።
ይህንንም ጸረ-ሴማዊነት ያቀጣጠለው የግራ እና የቀኝ ክንፍ አክራሪዎች ከሚያደርጓቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚደረጉ ቅስቀሳዎች ጋር በተያያዘ መሆኑንም ተመልክቷል።
ሪፖርቱ ይፋ የሆነው ረቡዕ ምሽት መታሰብ ከሚጀምረው የእስራኤላውያን ጭፍጨፋ እለት ነው።
በእስራኤል ዮም ሃሾህ በመባል የሚታወቀው ይህ ዕለት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በመላው አውሮፓ በናዚ ጀርመን የተገደሉ ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች መታሰቢያ ነው።
የ2021 ጸረ ሴማዊነት ዓለም አቀፍ ሪፖርት፣ በቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ የሂማኒቲ ዲፓርትመንት የዘመናዊ አውሮፓውያን አይሁዶች ጥናት ማዕከል ነው የተሰራው።
በዓለም ዙሪያ በደርዘን የሚቆጠሩ ጥናቶችን እንዲሁም ከህግ አስከባሪ አካላት፣ ከአይሁድ ድርጅቶችና ከሚዲያዎች የተገኙ መረጃዎችን በሰፊው አካትቷል።
በባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ከፍተኛ የአይሁዳውያን የህዝብ ቁጥር ባለባቸው በርካታ አገራት ውስጥ ጸረ-ሴማዊነት በከፍተኛ ሁኔታ ማንሰራራቱ የተፈጠሩ ክስስተቶች አመላካች ናቸው።
ከነዚህም ውስጥ፦
- ከእስራኤል ውጭ ከፍተኛ የአይሁዳውያን ቁጥር ባለባት አሜሪካ፣ በኒውዮርክ እና በሎስ አንጀለስ የተመዘገቡ ጸረ-ሴማዊ የጥላቻ ወንጀሎች ካለፈው ዓመት በእጥፍ አድገዋል።
- በፈረንሳይ ያለውን አኃዝ ስንመለከትበት ደግሞ ጸረ-ሴማዊነት ከ2020 ጋር ሲነፃፀር የባለፈው ዓመት 75 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱን ነው።
- በካናዳ አንድ የአይሁድ ቡድን በነሐሴ ወር ውስጥ ጸረ-ሴማዊ አካላዊ ጥቃት በ40 አመታት ታይቶ የማይታወቅ ነው ብሏል።
- በዩኬ በአይሁዶች ላይ ላይ የተመዘገቡ አካላዊ ጥቃቶች ከ2020 ጋር ሲነጻጸር 78 በመቶ ጨምሯል።
- በጀርመን በፖሊስ የተመዘገቡ ፀረ-ሴማነት ክስተቶች ከ2020 ጋር ሲነፃፀር 29 በመቶ፣ ከ2019 ጋር ሲነጻጸር 49 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱ ተመዝግቧል።
- በአውስትራሊያ እንዲሁ ጸረ-ሴማዊነት አንሰራርቷል የተባለ ሲሆን በግንቦች ወር ብቻ ከፍተኛ የተባለው 88 በመቶ አሻቅቧል።
የሪፖርቱ አዘጋጆች በቅርብ ጊዜ በእስራኤል መንግሥት እና በፍልስጤም ታጣቂዎች መካከል በጋዛ ሰርጥ የተደረገው ጦርነት ለጸረ-ሴማዊነት ማንሰራራት በከፊል ተጠያቂ አድርገዋል።
የእስራኤል መንግሥት እና ታጣቂዎች ለ11 ቀናት በተፋለሙበት ግጭት በጋዛ 261 ሰዎች ሲገደሉ በእስራኤል 14 ሰዎች መሞታቸውን የተባበበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ሪፖርቱ በተጨማሪም ሃሰተኛ መረጃዎች፣ ሴራዎች እና መጠነ ሰፊ ቅስቀሳዎች በማህበራዊ ትስስር ገፆች መሰራጨታቸው ለጸረ-ሴማዊነቱ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላል።












