ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዓለም አቀፍ ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ላይ በተወሰደ እርምጃ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
59 አገራትን በተሻገረ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መረቦች ላይ በተወሰደ እርምጃ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
በዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል አስተባባሪነት የተካሄደው ተልዕኮው ለወሲባዊ ብዝበዛ፣ ለግዳጅ ሥራ እና ወንጀል እንዲሁም ለግዳጅ ልመና ሰዎችን ማዘዋወር ላይ ያተኮረ ነው።
በካምቦዲያ በበይነ መረብ ለማጭበርበር ሰዎችን የሚያዘዋውር መረብ እና በማኅበራዊ ገፆች እድሜያቸው ያልደረሱ ሴቶች በአውሮፓ ሴተኛ አዳሪ እንዲሆኑ የሚመለምሉ ቡድኖች በተልዕኮው መበተናቸውን የኢንተርፖል ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ 2,070 ተጎጂዎች እና ተጎጂ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች የተለዩ ሲሆን፤ አብዛኞቹም ሴቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች ውስጥ 334ቱ ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ሲሆኑ 690ዎቹ ደግሞ በተያያዘ ወንጀል በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተገልጿል።
ከአውሮፓ የሕግ አስከባሪዎች ኤጄንሲ ኢሮፖል እና የአውሮፓ የድንበር ቁጥጥር ፍሮንቴክስ ጋር ተልዕኮውን ያስተባበረው ኢንተርፖል ተልዕኮው ያደጉ እና የተለወጡ ሕገ ወጥ የሰው ዝውውር መንገዶች እና ዘዴዎችን ያጋለጠ ነው ብሏል።
የላቲን አሜሪካ ተጎጂዎች ለግዳጅ ሥራ ወደ አውሮፓ የመዘዋወር አዲስ አዝማሚያ ያገኘው ኢንተርፖል፤ ከላቲን አሜሪካ ለወሲባዊ ብዝበዛ ከተዘዋወሩ ተጎጂዎች ውስጥ 10 በመቶዎቹ በእድሜ ያልደረሱ ናቸውም ብሏል።
በተልዕኮው አካል ኮሎምቢያ ሰዎች በተጭበረበሩ ሥራዎች ተታለው ወደ ውጭ አገር እንዳይጓዙ ግንዛቤ ለመፍጠር በአየር ማረፊያዎች የመከላከል ዘመቻ ጀምራለች።
የብራዚል ፌደራል ፖሊስ 83 ብራዚላዊያን እና 323 የውጭ አገር ዜጎች በአጠቃላይ 406 ተጎጂዎች በካምቦዲያ በበይነ መረብ እንዲያጭበረብሩ በግዳጅ ተዘዋውረው ማግኘቱን ኢንተርፖል ገልጿል።
ተጠርጣሪዎች እና ተፈላጊ ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ የኢንተርፖል የይፈለጋሉ ማስታወቂያዎች ወጥተዋል።
መደብር ውስጥ እንዲሰሩ የተገደዱ ሁለት የቦሊቪያ ሕፃናትን የአርጀንቲና ፖሊስ ታድጎ፤ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተገልጿል።
ተልዕኮው እ.አ.አ ከሰኔ 8 እስከ 12 ድረስ የተካሄደ እና በአፍሪካ፣ አሜሪካ [አኅጉር]፣ እስያ እና አውሮፓ አገራት ከ40 ሺ በላይ ሕግ አስከባሪ መኮንኖችን ያሳተፈ ነው።
ዘመቻው አብዛኞቹ ተጎጂዎች ለወሲባዊ ብዝበዛ የተዘዋወሩ እንደሆኑ እና 20 በመቶዎቹ በግዳጅ ወንጀል ውስጥ እንዲሰማሩ፣ 11 በመቶዎቹ የግዳጅ ሥራ እንዲሁም ሁለት በመቶቹ ወደ የግዳጅ ልመና እንዲገቡ መደረጉን አግኝቷል።
ኢንተርፖል በዘመቻው የለያቸው ተጎጂዎች ጥበቃ እና እርዳታ እንዲያገኙ መደረጉን እንዲሁም በዘመቻው ውጤት 465 ምርመራዎች መከፈታቸውን ገልጿል።
ተጨማሪ 201 ተጠርጣሪዎች በተልዕኮው መለየታቸውም ተነግሯል። ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ስፔን፣ ናይጄሪያ፣ ታይላንድ እና ቬትናምን ጨምሮ በርካታ አገራት በዘመቻው ተሳትፈዋል።
የኢንርፖል ፀሐፊ ቭላድሲ ኡርኪዛ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከተደራጁ ወንጀሎች ውስጥ በየዓመቱ ቢሊዮን ዶላሮችን በማመንጨት "በጣም ትርፋማ እና ሰፊ" መሆኑ ቀጥሏል ብለዋል።
ወንጀሎቹ "ለተጎጂዎች ከባድ እና ዘላቂ ጉዳት" ማድረሳቸውን ያከሉት ፀሐፊው፤ ተልዕኮው አገራት የወንጀል መረቦችን ለመበጣጠስ እና ትብብራቸውን ሲያጠናክሩ ምን ሊያሳኩ እንደሚችሉ ማሳያ እንደሆነ ገልፀዋል።