ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከሩሲያ ከባድ ጥቃት በኋላ ኔቶ የአየር መቃወሚያ ሥርዓት እንዲሰጣቸው ጫና ሊያደርጉ ነው
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከተባባሰው የሩሲያ ጥቃት አገራቸውን ለመከላከል በቱርክ በሚካሄደው የኔቶ ስብሰባ ላይ የአየር መቃወሚያ ለማግኘት የኪቭ አጋሮችን እንደሚወተውቱ ተገለፀ።
ዋና ከተማይቱ ኪቭ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የሩሲያ ሚሳኤል የዘነበባት ሲሆን፤ በጥቃቶቹ ከ50 የሚበልጡ ንፁሃን ተገድለዋል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የእርዳታ ጥሪያቸው እንዲህ አይነት ጥቃቶችን ለመቀልበስ የሚያግዝ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በአንካራ የሚካሄደው የምሥራቅ አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጉባኤ ዜሌንስኪ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ወሳኝ ንግግር ለማድረግ እድልም ያገኛሉ።
ንግግሩን የሩሲያ "የጭካኔ" ጥቃቶች የደካማነት ማሳያ እንጂ የጥንካሬ እንዳልሆነ እንዲሁም ቭላድሚር ፑቲን "የተከበረ" ሰላም ለማምጣት ንግግር እንዲያደርጉ ጫና ሊደረግባቸው ይገባል የሚል አቋማቸውን ለማስረዳት ይጠቀሙበታል።
በቅርብ ጊዜያት ዩክሬን ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ጥቃቶች ኪቭ የረዥም ርቀት የድሮን ጥቃቶችን ሩሲያ ላይ አጠናክራ መፈፀሟን ተከትሎ የመጣ ነው።
ኪቭ በድሮን ጥቃቶች የነዳጅ ማጣሪያዎችን እና ወታደራዊ ዒላማዎችን በመምታት ከፍተኛ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እና የኃይል መቆራረጥ እንዲፈጠር አድርጋለች።
የሩሲያ የማኅበራዊ የትስስር ገፆች ሰዎች ነዳጅ ለመግዛት ለሰዓታት ሲሰለፉ እና በተፈቀደላቸው አነስተኛ የነዳጅ መጠን ሲጋጩ በሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች የተሞሉ ናቸው።
በኔቶ ጉባኤ ዋዜማ ዜሌንስኪ የቱርኩ ስብሰባ "ባዶ" እንደማይሆን ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።
የኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩቴ አባል አገራት የአቅማቸውን ያህል ድርሻቸውን እንዲወጡ እና ዩክሬን "ሉዓላዊነቷን እንድትከላከል" የሚያስፈልጋትን እንድታገኝ አሳስበዋል።
ኪቭ በምሥራቅ የሩሲያን የምድር ግስጋሴ በመግታት ያደረገችውን ጥረት በመጠቆም "የጦርነት ሜዳውን ዓውድ እየቀየረች ነው" ሲሉም አስምረዋል።
በቅርቡ እየፈፀመቻቸው ያለው የድሮን ጥቃቶችም ለዩክሬን ወኔ ሰጥቷል።
በመሪዎቹ አፍ ያለው ቃል "የእድል መስኮት" ስለመከፈቱ ነው።
ይሁን እንጂ ጦርነቱ በሰማይ ተቀጣጥሎ ሲቀጥል የሩሲያ የባላስቲክ ሚሳኤሎች ለኪቭ ገሃዳዊ ችግር ፈጥረውባታል።
የዩክሬን አየር ኃይል በየቀኑ የሚደበድቡትን የሞስኮን መሣሪያዎች እየመዘገበ እና ያከሸፋቸውንም እየቆጠረ ነው።
ሰኞ ዕለት ሁሉም የድሮን ጥቃቶችን በስኬት መከላከል ቢችልም፤ ሚሳኤሎችን ለማክሸፍ ግን እንደማይችል እውን ሆኗል።
በሰዓት በርካታ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ተምዘግዝገው የሚያጠቁ መሆኑ እና ዩክሬን መጋዘን ውስጥ በቂ አሜሪካ ሰራሽ 'ፓትሪዮት' የሚሳኤል መከላከያ አለመኖር ጥቃቶችን ለመቀልበስ ፈታኝ ሆኖባታል።
ዜሌንስኪ በሰኞ መግለጫቸው ብስጭታቸውን እንዲህ ሲሉ ገልፀዋል። "በዛሬው ዓለም ሰዎችን ከባላስቲክ [ሚሳኤል] ሽብር ለመጠበቅ የሚያስፈልግ ምርት አለማደጉ የሚያስደንቅ ነው።"
ፕሬዝዳንቱ የአውሮፓ አጋሮቻቸውን ከራሳቸው ክምችት 'ፓትሪዮት' የአየር መቃወሚያ መሣሪያቸውን እንዲሰጧቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል። በዩክሬን ንፁሃን እየተገደሉ መሣሪያዎቹ መጋዘን ውስጥ መቀመጣቸው ለማንም አይጠቅምም በማለት እየሞገቱ ነው።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ኔቶን እና ፕሬዝዳንት ትራምፕን ዩክሬን የጦርነቱን ማዕበል እንደቀየረች እና ሩሲያ ረብ ላለው የሰላም ድርድር እንድትቀመጥ ጫና እንዲያደርጉ ለማሳመን ይወተውታሉ።
ትራምፕ በዚህ ሳምንት ከፑቲን ጋር ለ90 ደቂቃ ያህል በስልክ ቢነጋገሩም ዩክሬን በቅርብ ባስመዘገበችው ድል ግን የተደመሙ ይመስላሉ።
ከሁሉም በላይ ኪቭ "በጥንካሬዋ አሊያም በዲፕሎማሲ" ከባዱ የክረምት ጊዜ ከመምጣቱ በፊት ጦርነቱን በፍጥነት መቋጨት ትፈልጋለች።
ይሁን እንጂ ዩክሬን ይህን እድል ለማግኘት ዘለንስኪ ከተሞችን እና ንፁሃንን ለመጠበቅ ተጨማሪ የሚሳኤል መቃወሚያ ያስፈልገናል ብለው ይሞግታሉ።