ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ የምትቀላቀለው የብሪክስ 'ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ' ምንድን ነው?
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ የብሪክስን 'ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ' ለመቀላቀል የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁን ሰኔ 19/2018 ዓ.ም. አፅድቋል።
ምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት ባደረገው ለአገራዊ የልማት ፋይናንስ፣ ለመሠረተ ልማት ድጋፍ እና አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን ለማግኘት' አስፈላጊ መሆኑ ስላመነበት አባልነቱን ማፅደቁን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የባንኩን ምሥረታ ስምምነት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያፀድቀው ተላልፏል።
ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው ኢትዮጵያ አባል ለመሆን 2,945 የአክሲዮን ድርሻዎችን ትገዛለች። በአጠቃላይ አገሪቱ 294.5 ሚሊዮን ዶላር ድርሻ እንደምትገዛ ጋዜጣው አዋጁን እና ሌሎች ሰነዶችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ቢቢሲ በተመለከተው የባንኩ የአክሲዮን ድርሻ እና ካፒታል መሠረት ኢትዮጵያ ከአንድ በመቶ በታች የባንኩ ድርሻ ይኖራታል።
በ2007 ዓ.ም. በብሪክስ አባል አገራት የተመሠረተው 'ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ' ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች እና ለዘላቂ ዕድገት ሀብት ማሰባሰብ ዓላማው እንደሆነ ድረ ገፁ ያትታል።
የብሪክስ አባል አገራት በሆኑት በብራዚል፣ በሩሲያ፣ በሕንድ፣ በቻይና እና በደቡብ አፍሪካ የተመሠረተው ባንኩ፤ በገንዘብ አቅርቦት እና ገበያቸው እየተስፋፋ እና እያደጉ ባሉ አገራት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ራሱን እንደ "ማነቃቂያ" አድርጎ ይመለከታል።
አንድ ሚሊዮን ድርሻዎች ያሉት ባንኩ እያንዳንዱን ድርሻዎች በ100 ሺ ዶላር ይሸጣል።
ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ እያንዳንዳቸው 18.72 በመቶ ድርሻ አላቸው።
በቅርቡ ባንኩን የተቀላቀሉት አምስት አገራት የስድስት በመቶ ድርሻ ብቻ አላቸው።
ከአባል አገራት እና ባለድርሻዎች ጋር በቅርበት እንደሚሠራ የሚገልፀው ባንኩ፤ የምጣኔ ሀብት ልማትን ለማፋጠን እንዲሁም የአባል አገራትን ሕዝቦች አካባቢያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት ለማሻሻል ለልማት የሚውሉ ካፒታሎችን እንደሚያቀርብ ይገልፃል።
በቀድሞ ስሙ 'ብሪክስ ዴቬሎፕመንት ባንክ' በመባል የሚጠራው ባንኩ መቀመጫው በቻይና ሪፐብሊክ ሻንጋይ ነው።
ባንኩ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ በሆኑት የቀድሞ የብራዚል ፕሬዝዳንት ዲለማ ሩሴፍ የሚመራ ነው።
የባንኩ ከፍተኛው ውሳኔ ሰጪ የገዢዎች ቦርድ ነው። የባንኩ ሁሉም ሥልጣን ያለው ይህ ቦርድ ሲሆን፣ እያንዳንዱ አባል አገር ገዢ አባል እና ተለዋጭ አባል ይሾማሉ።
የባንኩ ድረ ገፅ እነዚህ የቦርድ አባላት በአብዛኛው የአገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች እና ተያያዥ ኃላፊነት ያላቸው እንደሆኑ ያመለክታል።
በገዢዎች ቦርድ የሚሰጠውን ኃላፊነት የሚወጣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ያለውም ሲሆን፤ አጠቃላይ የባንኩን እንቅስቃሴ የሚመራ ነው።
አባል አገራት ለዳይሬክተሮች ቦርድም ዳይሬክተር እና ተለዋጭ ዳይሬክተር ይመድባሉ።
የባንኩ ፕሬዝዳንት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሲሆኑ፤ የውሳኔ ክፍፍል በሚፈጠርበት ወቅት ወሳኙን ድምፅ ከመስጠት ውጭ ድምፅ የላቸውም።
ብሪክስ በ2024 ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራትን በአባልነት በመቀበል የአባሎቹን ቁጥር ከአምስት ወደ 11 አድርሷል።
ከ2023 ወዲህ የቡድኑን ባንክ አዲስ አባል ሆነው የተቀላቀሉት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ አልጄሪያ፣ ባንግላዲሽ እና ኡዝበኪስታን ናቸው።
በ'ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ' የገዢዎች ቦርድ ባንኩን እንዲቀላቀሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት አገራት ተፈቅዶላቸዋል። አገራቱ አባል ለመሆን ማስገባት የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ ካስገቡ በኋላ በይፋ አባላት ይሆናሉ።
ሪፖርተን ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ ኢትዮጵያ ለመግዛት ካሰበችው የአክሲዮን ድርሻ 20 በመቶውን (58.9 ሚሊዮን ዶላር) በቅድሚያ የምትከፍል ሲሆን፤ ቀሪውን በ13 ዓመት ገደማ ትከፍላለች።
ባንኩ እንደ ትራንስፖርት፣ በካይ ያልሆነ ኃይል ልማት፣ ውሃ እና እንደ ቤቶች ያሉ የማኅበራዊ ልማቶች ግንባታ ገንዘብ እንዳቀረበ በድረ ገፁ ዘርዝሯል።
በቅርቡ ለደቡብ አፍሪካ የመንገደኞች ባቡር ፕሮጄክት 1 ቢሊዮን ዶላር ለማቅረብ ፕሮጄክቱን ያፀደቀ ሲሆን፤ ከወራት በፊት ደግሞ ለሕንድ የቤቶች ግንባት 75 ሚሊዮን ዶላር ብድር አፅድቋል።
ኢትዮጵያ በባንኩ የብድር ሥርዓት ግብርና፣ ኃይል እና የኢንዱስትሪ ዘርፉ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው እንዲሁም ከአየር ንብረት እና የታዳሽ ኃይል ፕሮጄክቶችም ልዩ ትኩረት እንደሚያገኙ ዘግቧል።
'ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ' አባልነትን እንዲያፀድቅ የተላከለት ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣን ዘመኑን ጨርሶ ሰኔ 30/2018 ዓ.ም. በይፋ ይበተናል።
ማክሰኞ ሰኔ 29/2018 ዓ.ም. መደበኛ እና የመጨረሻ ስብሰባውን የሚያደርገው ምክር ቤት የባንኩን አባልነት የውሳኔ ሃሳብ ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል።