ሳምሰንግ ትርፉ በ1,800% ማደጉን ገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የደቡብ ኮርያው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሳምሰንግ ትርፉ 1,800 በመቶ መጨመሩን አስታወቀ።

በመላው ዓለም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቺፖች (AI memory chips) ተፈላጊነት እየጨመረ በመምጣቱ ትርፋማነቱ ማደጉን ገልጿል።

ለያዝነው ዓመት ባስቀመጠው ትንበያ መሠረት ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባሉት ወራት 58.4 ቢሊዮን ዶላር እንዳገኘ እና በዚህም በተከታታይ ከፍተኛ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታውቋል።

እንደ ሳምሰንግ ያሉ ግዙፍ የደቡብ ኮርያ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ይፋዊ የትርፍ ሪፖርት ከማውጣታቸው በፊት ለባለ ሃብቶች የትርፍ ትንበያ ያቀርባሉ።

ሳምሰንግ ሐምሌ ላይ ይፋ ከሚያደርገው ይፋዊ የትርፍ መጠን አስቀድሞ ባወጣው ሪፖርት እንደተመለከተው፤ የሰሚኮንዳክተሮች (semiconductors) ተፈላጊነት መጨመር የዋጋ ንረት አስከትሏል።

በዘንድሮው ሩብ ዓመት ያስቀመጠው የትርፍ መጠን አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጨምሯል። "ከፍተኛው የሩብ ዓመት ውጤታማነት" ሲልም ገልጾታል።

በካውንተርፖይንት ሪሰርች የጥናት ተቋም ውስጥ የሚሠሩት የቴክኖሎጂ ዘርፍ ተንታኝ ማርክ አይንስታይን እንዳሉት አምና በተመሳሳይ ወቅት ንቪዲያ ኩባንያ ተቀራራቢ ገቢ አግኝቷል።

"የኤአይ ሜሞሪ ቺፕ የሚያመርቱ ኩባንያዎች ያለውን ውስን የምርት አቅርቦት እና ከፍተኛ የፍላጎት መጠን እየተጠቀሙበት ነው" ብለዋል።

ሳምሰንግ ያለውን ክፍተት ተጠቅሞ የሜሞሪ ቺፖችን ዋጋ ጨምሯል።

አይዲሲ የተባለው የጥናት ተቋም እንዳለው፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሠረተ ልማት ለመዘርጋት እና ለዳታ ማዕከሎችም ሰሚኮንዳክተሮች ከፍተኛ ተፈላጊነት አላቸው።

ከዚህ ቀደም በኢንዱስትሪው ከነበረው "የተለየ" እንደሆነ እና በኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ የቺፖች ተፈላጊነት ላይ ለውጡ ጎልቶ እንደታየ አስታውቋል።

በተቋሙ የቴክኖሎጂ ተመራማሪ ብራየን ማ "በቀጣይ ዓመት አቅርቦቱ ውስን ይሆናል ብለን አናስብም። ምክንያቱም የዳታ ማዕከሎች ፍላጎት ጨምሯል" ሲሉ አብራርተዋል።

ሳምሰንግ ከግዙፎቹ ሰሚኮንዳክተር አምራች ኩባንያዎች አንዱ ነው። እንደ ንቪዲያ እና ጉግል ላሉ ተቋማት ቺፖችን ያመርታል።

ቺፖች ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የድርሻ ሽያጭ ጨምሯል።

ዛሬ ማክሰኞ በሱዑል የሳምሰንግ የድርሻ ሽያጭ ቢቀንስም በዘንድሮው የድርሻ ገበያ ያለው ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።

የደቡብ ኮርያው የሳምሰንግ ተፎካካሪ ኩባንያ ኤስኬ ሃይንክስ የድርሻ ገበያ ከ200% በላይ ሆኗል።

የሁለቱ ተቋማት ውጤታማነት የደቡብ ኮርያን አጠቃላይ የድርሻ ገበያ በያዝነው ዓመት 80% ከፍ እንዲል አስችሏል።