ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር እውቋን ተዋናይት በተመለከተ ለሰጡት "ያልተገባ" ፆተኛ አስተያየት ይቅርታ ጠየቁ
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ እውቋን ድምጻዊ እና ተዋናይት ኬይሊ ሚኖግን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ይቅርታ ጠየቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየቱን የሰጡት በአንድ ፖድካስት ላይ ባደረጉበት ቃለ ምልልስ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኮሜዲያን ኒክ ኦስቦርን ጋር በ'ቡሽ ዲፕ' ፖድካስት ባደረጉት ቆይታ ከተዋናይት ኬይሊ ሚኖግን፣ ኖኮል ኪድማን ወይም ከዝነኛዋ ሆንዳ ቡርችሞር ጋር "ወሲባዊ ግንኙነት ይፈፅሙ ፣ ያገቡ ወይም ለፍቅር ቀጠሮ ያገኟቸው" እንደሆነ ተጠይቀው ነበር።
የ20 ደቂቃ ርዝማኔ ባለው በዚህ ቃለ ምልልሳቸው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጀመሪያ ላይ ጥያቄውን ላለመመለስ ሞክረው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ " ኦ! ኬይሌ፣ በሚገባ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አልባኒዝ በዚህ ንግግራቸው የውግዘት ውርጅብኝ ያስተናገዱት ወዲያውኑ ነበር።
አንድ የሕዝብ ተወካይ የጠቅላይ ሚስትሩን አስተያየት " ሙሉ በሙሉ ያልተገባ" ያሉት ሲሆን ሌላ ተወካይም " የሴቶች ክብር የነካ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የማይጠበቅ" ሲሉ ተችተውታል።
የኮሜዲ ይዘቶችን በማጋራት የምትታወቀው ኦስቦርን፣ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ነበር ተከታታይ የፖድካስት ፕሮግራሟን የጀመረችው።
የፖድካስት ገጿ " ማንም የማይደፍራቸውን ጥያቄዎች የምትጠይቅ"፤ " ትክክለኛ ያልሆነች ጋዜጠኛ" ሲል ይገልጻታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ ዕለት በኦንላይን በሰጡት መግለጫ " ግልጽ ለሆነው አስተያየቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውግዘት ያስከተለባቸውን አስተያየት የሰጡበት ቃለ ምልልስ የተደረገው በካናቤራ በሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያ ሲሆን የተለቀቀው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነው።
ኦስቦርን መጀመሪያ ላይ ጥያቄውን ገታ አድርጋው የነበረ ሲሆን ባለፈው ሕዳር የሥራ አጋሯን ጆዲ ሃይደንን ያገቡት አልባኒስ መጀመሪያ ላይ " አግብቻለሁ፣ ትዳር ውስጥ ከገባሁ ገና ስድስት ወሬ ነው" ብለው ነበር።
በኋላ ላይ ግን በኦስቦርን በተደረገባቸው ግፊት "ኦ! ኬይሊ፣ በሚገባ" ብለዋል።
" ኬይሊን ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ሊፈፅሙ፣ ለፍቅር ቀጠሮ ሊያገኟት ይችላሉ? " ስትል ኦስቦርን ጠይቃቸዋለች።
" የጠቀሻቸውን ሁሉ፣ በጣም ጥሩ ናት" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሏ ዛሊ ስቴጋል " አስተያየቱ ሙሉ በሙሉ ያልተገባ፣ ሊታረም የሚገባ ፆተኛ አስተያየት" ብለውታል።
የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ተወካይዋ ሳራህ ሄንደርሰንም በኤክስ ገፃቸው ላይ " አስተያየቱ የሴቶችን ክብር የነካ፣ አውስትራሊያንን ያስቆጣ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮ ያዋረደ" ሲሉ ቁጣቸውን ገልጸዋል።
አልባኒዝ ለጉብኝት ወደ ፓስፊክ ባቀኑበት ወቅት የሚወክሏቸው ሪቻርድ ማርል በበኩላቸው መንግሥት " በማኅበረሰብ ውስጥ ሴቶች ያላቸውን ቦታ ከፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው" ሲሉ ለኤቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።
" ልክ አሁን እንደተደረገው በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ቃለ ምልልሶችን አድርገናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግሥት በካቢኔያቸው ውስጥ የሴቶች እና የወንዶች ቁጥርን እኩል ያደረጉ በታሪክ የመጀመሪያው መሪ ናቸው" ሲሉም ተከላክለውላቸዋል።
አልባኒዝ በቃለ ምልልሳቸው በውጭ አገር ጉብኝታቸው ወቅት የተቀበሉት የተለየ ስጦታ እንዳለም ተጠይቀው " እንግዳ የሆነ፣ ሆኖም በጣም ጥሩ" ያሉትን የሁለት ሃብሃብ ስጦታ ከጃፓኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳኔ ታኬች እንደተቀበሉ ገልጸዋል።