ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ለማስቀረት ያደረጉትን ሙከራ ውድቅ አደረገ
ሰነድ አልባ ስደተኞች በአሜሪካ የሚወልዷቸው ልጆች የአሜሪካ ዜግነት እንዳያገኙ ለማገድ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያደረጉትን ጥረት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ባሳለፈው ውሳኔ የአሜሪካ ዜግነት ከሌላቸው ስነድ አልባ ስደተኞች በአሜሪካ የሚወለዱ ልጆች የአገሪቱን ዜግነት የማግኘት መብታቸውን ለመቀልበስ የተደረገው ጥረት አግዷል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የሕግ ቡድናቸው ሲያራምድ የቆየውን አቋም ሕግ አውጪዎች ብዙም ሲደግፉት አልታየም።
በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔም እንደ ትልቅ ድል ቆጥረውታል።
ከዘጠኙ የጠቅላይ ፍርድ ቤት የዕድሜ ዘመን ዳኞች አብላጫውን ቁጥር የያዙት 150 ዓመት ያስቆጠረውን በመወለድ የሚገኝ የዜግነት መብት እንዲቀልበስ አልፈቀዱም።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ትራምፕን እንደሚያስቆጣ ይጠበቃል። ሰነድ አልባ ስደተኞች ወደ አሜሪካ የሚገቡበትን መንገድ ለመገደብ ሌሎች አማራጮች መፈለጋቸው አይቀርም።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የትራምፕን ሐሳብ የቀለበሰው 6 ለ 3 በሆነ ድምጽ ነው።
የአሜሪካ ዜጋ ካልሆኑ እና ሕጋዊ ሰነድ ከሌላቸው ስደተኞች የሚወለዱ ልጆች፣ አሜሪካ ውስጥ በመወለድ ዜግነት እንዳያገኙ ለማድረግ ትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝን ለመጠቀም ሞክረዋል።
ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የሥር ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞችን ለማገድ የሚያስችላቸው ሥልጣን ውስን እንዲሆን ሲበይን፤ትራምፕ "ትልቅ ድል" ብለውት እንደነበር ይታወሳል።
ትራምፕ ስለ ዛሬው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ገና አስተያየታቸውን ባይሰጡም ከዚህ ቀደም በመወለድ የሚገኝ ዜግነት "የሕገ ወጥ ስደት ትልቁ ማግኔት" ማለታቸው አይዘነጋም።
ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ የስደተኞች ፖሊሲያቸው አካል በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ማስቀረት ሆኖ ቀጥሏል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በመወለድ በሚገኝ ዜግነት "ሰንሰለት ታስረን መኖር አንችልም" ብለው ጽፈዋል።
"በምጣኔ ሃብት አያዋጣም። የትኛውም አገር አያደርገውም" ሲሉም ዜግነት የማግኘት መብቱን አጥብቀው ተችተዋል።
የአሜሪካ ሕገ መንግሥት አራተኛ አንቀጽን በመጥቀስ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የትራምፕን ሐሳብ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል።
ከዳኞቹ አንዱ የሆኑት ጆን ሮበርትስ "በአሜሪካ የተወለዱ ወይም ዜግነት ያገኙ በሕግ ከለላ ስለሚያገኙ የአሜሪካ ዜጋ ናቸው" ብለዋል።
የትራምፕ የሕግ ቡድን ሰነድ አልባ ስደተኞች ላይ የአሜሪካ ሕግ "ተግባራዊ አይሆንም" ሲል ተከራክሯል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የትራምፕን ሐሳብ ውድቅ ያደረገው በአብላጫ ድምጽ ስለሆነ ፕሬዝዳንቱ ውሳኔውን ለመቀልበስ ይቸገራሉ።