አሜሪካ እና ሊባኖስ በወንጀል ለሚፈለጉት የሶሪያ ጄነራል ከለላ መስጠታቸውን ቢቢሲ አጋለጠ

ጀነራል ባሳም አል-ሀሰን የጉዞ ሰነድ
የምስሉ መግለጫ, ባሳም አል-ሀሰን በበሻር አል-አሳድ አገዛዝ ወቅት በነበራቸው ሚና በሰብአዊነት ላይ በተቃጣ ወንጀል የሚፈለጉ ናቸው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሰብአዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ለሚፈለጉት የቀድሞ የሶሪያ ጄነራል የአሜሪካ እና የሊባኖስ ባለሥልጣናት ገንዘብ እንደመደቡ እና ከለላ እንደሰጡ የቢቢሲ ምርመራ አረጋገጠ።

የሶሪያ የኬሚካል ጦር መርሃ ግብር መሪ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባሽር አል-አሳድ ከፍተኛ አማካሪ የነበሩት ባሳም አል-ሐሰን የአሳድ አገዛዝ መውደቁን ተከትሎ በሊባኖስ ከለላ ተሰጥቷቸዋል።

በቢቢሲ እና በአሜሪካው ኤንፒአር ቅንጅት የተደረገ ምርመራ፤ የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ እና ሌሎች የአሜሪካ እና የሊባኖስ ተቋማትን ባሳተፈ ስምምነት ጄነራሉ በሊባኖስ እንዲቆዩ እንደተፈቀደላቸው አረጋግጧል።

የስምምነቱ ምክንያት አል-ሐሰን በአውሮፓውያኑ 2012 በሶሪያ ስለተጠለፈው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ኦስቲን ቲስ ተጨማሪ የደኅንነት መረጃዎችን ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆናቸው እንደሆነ ተነግሯል።

ባለፈው ወር ቢቢሲ የጋዜጠኛው ጠለፋ በአል-ሐሰን ትዕዛዝ የተፈፀመ ተልዕኮ መሆኑን ዘግቧል።

የአዲሱ የሶሪያ መንግሥት ሁለት የተለያዩ ቅርንጫፍ ተቋም ባለሥልጣናት የቀድሞው ጄነራል ወደ ደማስቆ መልሰው ለፍርድ ማቅረብ እንደሚፈልጉ ለቢቢሲ ተናረግረው፤ ነገር ግን የአሜሪካ ባለሥልጣናት አል-ሐሰን በቤይሩት እንዲቆዩ እንደሚፈልጉ እና ደማስቆ እጇ እንደታሰረ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ኤፍቢአይ፣ የአሜሪካ የስለላ ተቋም ሲአይኤ እና የሊባኖስ ጠቅላይ ደኅንነት ቢሮ ስለ ግንኙቱ አስተያየት እንዲሰጡት ጠይቆ ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

ስለ ስምምነቱ እውቅና ያላቸው ምንጮች መረጃ ለማግኘት ለጄነራሉ "መኖሪያ፣ ጥበቃ" እና ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንዲቀርቡላቸው መስማማታቸውን አረጋግጠዋል።

ምንጮች የአሜሪካ መንግሥት በሦስተኛ ወገን በኩል ለአል-ሐሰን ገንዘብ መላኩንም ተናግረዋል። የቀድሞው ጄነራል በአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ የተጣለባቸው ናቸው።

ይህ ስምምነት በ2025 እንደተደረሰ ይታመናል።

አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ኦስቲን ታይስ
የምስሉ መግለጫ, አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ኦስቲን ታይስ በአውሮፓውያኑ 2012 ደብዛው የጠፋ ሲሆን፣ ባሳም አል-ሐሳን በጋዜጠኛው መጥፋት ውስጥ እጃቸው እንዳለ ይታመናል

ሆኖም ከጋዜጠኛው የጠለፋ ምርመራ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በስምምነቱ መሠረት አል-ሐሰን መረጃ መስጠት ከጀመሩ ወዲህ እዚህ ግባ የሚባል ማስረጃ አለመገኘቱን ጠቁመዋል።

አል-ሐሰን ከጋዜጠኛው ምርመራ ጋር በተያያዘ የገንዘብ ድጋፍ አሊያም ውጭ አገር ለመኖር ድጋፍ የተሰጣቸው ብቸኛ የቀድሞ የሶሪያ አገዛዝ ባለሥልጣን አይደሉም።

በታኅሣሥ 2024 የአሳድ መንግሥት መውደቁን ተከትሎ አል-ሐሰን ወደ ኢራን ማምለጣቸው ይታመን ነበር።

ከቀድሞው የሶሪያ መንግሥት እና ከሊባኖስ ባለሥልጣናት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው የሶሪያ ባለሀብት አል-ሐሰንን ወደ ሊባኖስ ለማምጣት በአሜሪካ፣ በሊባኖስ እና በኢራን መካከል ድርድር መካሄዱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ባለሀብቱ አል-ሐሰን ስለጋዜጠኛው ጠለፋ ብቻ ሳይሆን ስለ ሶሪያ የኬሚካል መሣሪያ ባላቸው እውቀት እንዲሁም ከኢራን ጋር ባለቸው ወታደራዊ ግንኙነት ምክንያት አሜሪካ ፍላጎት እንዳሳደረችባቸው ገልፀዋል።

አል-ሐሰን ባለፈው ዓመት ጋዜጠኛው በቀድሞው ፕሬዝዳንት አሳድ ትዕዛዝ መገደሉን ለአሜሪካ መርማሪዎች ቢናገሩም፤ ለምርመራው ቀረብ ያሉ ሰዎች ስለምስክርነቱ ጥርጣሬ እንዳደረባቸው ተናግረዋል።

የጋዜጠኛው አስከሬን የተቀበረበትን ሥፍራ ቢጠቁሙም አካባቢው ሲፈተሽ ምንም አለመገኘቱን በርካታ ምንጮች ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ለቃለ መጠይቅ ቢቢሲ ጥያቄ ያቀረበላቸው አል-ሐሰን በቤይሩት ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ኤፍቢአይ እና ሲአይኤ ፈቃድ እንዲጠይቅ መርተዋል።