
የፎቶው ባለመብት, Reuters
የምስሉ መግለጫ, የየመኑ ፕሬዝዳንት ራሻድ አል-አሊሚ እሁድ ዕለት በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ንግግር ሲያደርጉዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግሥት መሪ ሁቲዎች የያዟቸውን ግዛቶች ለማስለቀቅ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ማወጃቸውን
አስታወቁ።
የየመን መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሳዑዲ በሚመራው ጥምረት እና በሁቲዎች መካከል
የተኩስ ልውውጥ ከተደረገ በኋላ ነው።
በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በ12 ሰዓት ውስጥ ለፈጸመው 50 የአየር ድብደባዎች ምላሽ ለመስጠት
በሚል የአሀገሪቱ ብሔራዊ ነዳጅ ኩባንያ፣ አራምኮን አጥቅተዋል።
ሳዑዲ አረቢያ ስለጥቃቱ እስካሁን ድረስ ምላሽ አልሰጠችም።
ሁቲዎች ባለፈው ወር ወሳኙን የባብ አል-ማንዳብ የባህር መስመርን ጨምሮ የአገሪቱን የባህር ዳርቻዎች በቁጥጥራቸው ስር
ያደረጉበትን ጥቃት ተከትሎ፣ የየመን መንግሥት ጠንካራ መግለጫ ያወጣል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
የየመኑ ፕሬዝዳንት ራሻድ አል-አሊሚ እሁድ ዕለት በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር "ዛሬ፣ የሪፐብሊኩን ቀሪ ግዛት
መልሶ ለመቆጣጠር እንዲሁም የመንግሥትን እና የተቋማቱን ሥልጣን በመላው አገሪቱ ለማስፋት የሚያስችሉ ወታደራዊ ዘመቻዎች መጀመራቸውን
አበስራለሁ" ብለዋል።
የየመን ዋና ከተማ የሆነችው ሰነዓ በሁቲዎች ቁጥጥር ሥር ከገባች ከ10 ዓመት በላይ አልፏታል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የመንግሥት ኃይሎች የታጣቂ ቡድኑን አቅም ለማዳከም በሚል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
በሁቲዎች ላይ የሚፈጸመው ድብደባ በመላው አገሪቱ የተስፋፋ ሲሆን ይህም የቡድኑ ዋና መቀመጫ የሆነችው እና በአገሪቱ
ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኘው ሳዳን ክልልን ይጨምራል።
ነገር ግን በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በርካታ ስፍራዎችን እየተቆጣጠሩ ስለመምጣታው ምንጮች ተናግረዋል።
ሳዑዲ አረቢያ በተደጋጋሚ በሁቲ አማፂያን ጥቃትን ያስተናገደች ሲሆን ይህም የአገሪቱ የገቢ ምንጭ የሆነው የነዳጅ ሃብቷ
ላይ ያተኮረ ነው።
እሁድ ዕለት የሁቲ አማፂያን ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ ቡድኑ በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ በሚገኘው እና የአራምኮ ነዳጅ ኩባንያ ንብረት በሆነ ማጠራቀሚያ ላይ የባሌስቲክ ሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
"ሁለቱም ኦፕሬሽኖች ግባቸውን በተሳካ ሁኔታ አሳክተዋል" ያሉት ቃል አቀባዩ "ጥቃቶቹ ትክክለኛ
ዒላማቸውን የመቱ ሲሆን፣ በተመቱት ቦታዎች ላይም ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ አስከትለዋል" ሲሉ የደረሰውን ጉዳት አብራርተዋል።
ቡድኑ የሳዑዲን የነዳጅ ማዕከላት መምታቱን ሲገልጽ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ሳዑዲ አረቢያ በእሁዱ ጥቃት ላይ እስካሁን
ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠችም።
ሆኖም ከዚህ ቀደም አንዳንድ ተመሳሳይ መግለጫዎችን
"አሳሳች" በማለት ውድቅ ማድረጓ እንዲሁም ሁቲዎችን "ምናባዊ ድሎችን በማሳደድ" ላይ ናቸው በማለት
መተቸቷ ይታወሳል።
የመን በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ድሃ አገራት አንዷ ስትሆን፣ አሁንም ድረስ በከባድ ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።