'ዩክሬን አዲስ ፕሬዝዳንት የሚያስፈልጋት ጊዜ ላይ ደርሳለች' ሲሉ ትራምፕ ተናገሩ

ቮሎዲሚር ዘለንስኪ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ዩክሬን አዲስ ፕሬዝዳንት የሚያስፈልጋት ጊዜ ላይ ደርሳለች" ብለው እንደሚያስቡ ገለፁ።

ትራምፕ ይህን ያሉት፣ የዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር በደረሰችው የናፍጣ ስምምነት ላይ ላቀረቡት ትችት በሰጡት መልስ ነው።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት፣ በሚሊዮኖች ቶን የሚቆጠር የናፍጣ ነዳጅ ከሩሲያ ወደ አሜሪካ እንዲላክ የተደረሰው አዲስ ስምምነት፣ ሞስኮ በአገራቸው ላይ ጦርነቱን እንድትቀጥል የሚረዳትን ገንዘብ እንደሚያስገኝላት አስጠንቅቀዋል። ይህንንም ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን "የተሰጠ ስጦታ" ሲሉ ገልፀውታል።

ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ከዋይት ሀውስ ውጭ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ ዜሌንስኪ በሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያ ተቋማት ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን በመቀጠል "በዓለም ላይ ችግር መፍጠር ይፈልጋሉ" ብለዋል።

ትራምፕ፣ የዩክሬን አቻቸው ይህን "ማቆም አለባቸው" ካሉ በኋላ ዩክሬን "ስምምነት ላይ መድረስ የሚችል አዲስ መሪ ማግኘት አለባት" ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ሩሲያ እአአ በ2022 ወረራ ከፈፀመችባት ወዲህ፣ ዩክሬን ወታደራዊ ሕግ ተግባራዊ በማድረጓ ምርጫዎች ታግደዋል።

አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ በጀመሩት ጦርነት ሳቢያ ከዓለም የነዳጅ ምርቶች አንድ አምስተኛው የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ ናፍጣን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦቶች ላይ ከፍተኛ ውስንነቶች ገጥመዋል።

ከፍተኛ የነዳጅ አምራች የሆነችው ሩሲያ እና ዩክሬን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳቸው የሌላኛቸው የኃይል መሠረተ ልማቶችና የትራንስፖርት ተቋማት ላይ የሚፈፅሟቸውን ጥቃቶች አጠናክረው ቀጥለዋል። ይህም ቀድሞውኑም ፈተና የተጋረጠበትን የነዳጅ ኃይል አቅርቦት ገበያ የበለጠ ጫና ውስጥ ከቶታል።

"ሩሲያ ላይ የፈለጋችሁትን ማድረግ ትችላላችሁ፣ ነገር ግን የነዳጅ ማጣሪያ ተቋማቱን አትምቱ፤ ምክንያቱም ይህ በዓለም ላይ ችግር ይፈጥራል ብለን ነበር" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።

"በርካታ ስምምነቶችን ማድረግ ይችል ነበር፤ ሆኖም በሆነ ምክንያት አያደርግም" ሲሉም ዜሌንስኪን ከሰዋል።

ትራምፕ ከዋይት ሀውስ ውጭ መግለጫ ሲሰጡ
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፑቲን ልዩ መልዕክተኛ ኪሪል ድሚትሬቭ፣ የትራምፕን ጣልቃ ገብነት "ታሪካዊና ልዩ እርምጃ" ሲሉ ገልፀው፣ ዩክሬን "በትክክል ለሰላም ትኩረት የሚሰጥ አመራር ያስፈልጋታል" ብለዋል።

ሩሲያ ናፍጣ ወደ ውጭ እንዳትልክ የተጣሉ ማዕቀቦች እስከ አውሮፓውኣኑ ሚያዝያ 7 ድረስ እንዲታገዱ ከሞስኮ ጋር ስምምነት መደረሱን የአሜሪካው ፕሬዚዝንት አርብ ዕለት አረጋግጠዋል።

ዜሌንስኪ በሰጡት ምላሽ፣ ስምምነቱ ሞስኮ አዳዲስ ወታደራዊ መሣሪያዎችን ለመግዛት እና ጦርነቱን ለመቀጠል ተጨማሪ ገንዘብ እንድታገኝ ያስችላታል ብለዋል።

በተጨማሪም፣ ሞስኮ ስምምነቱን "ጦርነቱን እና በከተሞች ላይ ቦምብ መጣሏን እንድትቀጥል" የተሰጣት ፈቃድ አድርጋ ወስዳዋለች ሲሉ በዛፖሪዢያ የተፈፀመውን ቢያንስ 20 ሰዎች የተገደሉበት አዲስ ጥቃት ተከትሎ ከሰዋል።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በቅርብ ጊዜ እድገቶች ዙሪያ ቅዳሜ ዕለት ከበርካታ አጋሮቻቸው ጋር ባደረጉት ንግግር "በዩክሬን የሰዎችን ሕይወት ለመጠበቅ እና የአውሮፓን ደኅንነት ለማስጠበቅ እውነተኛ ውሳኔዎች" እንዲወሰኑ ጠይቀዋል።

የዳውኒንግ ስትሪት ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም ከዜሌንስኪ ጋር በስልክ ባደረጉት ንግግር ሙሉ ድጋፋቸውን ገልጸፀዋል።

የአሜሪካና ሩሲያ የናፍጣ ስምምነት ዜና ከአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ካያ ካላስም ትችት ገጥሞታል።

ካላስ፣ ማዕቀቦቹን ማንሳት "ሞስኮ ጦርነቱን እንድትቀጥል ተጨማሪ ገቢ ያስገኝላታል" ሲሉ የዜሌንስኪን ሐሳብ አጠናክረዋል። አክለውም፣ "በሩሲያ ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ አሁን ጊዜው አይደለም፤ አውሮፓ ይህን አታደርግም" ሲሉ ተናግረዋል።

የኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ኃላፊዋ ካላስ እንደገለፁት፣ የአውሮፓ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሩሲያ ጦርነቱን ከጀመረች ወዲህ ከተወሰዱት ሁሉ የላቀ አዲስ ማዕቀብ ሰኞ ዕለት ለማጽደቅ አቅደዋል።

አሜሪካ ከሩሲያ ጋር የደረሰችው ስምምነት፣ ትራምፕ በአገራቸው የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ ከሚያደርጓቸው ጥረቶች አንዱ መሆኑ ተገልጿል።