ኤርትራ ለተመድ በላከችው ደብዳቤ "ኢትዮጵያ ራስን በመከላከል ስም ጦርነትን ምክንያታዊ ልታደርግ ነው" ስትል ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Yemane G. Meskel/X
ኤርትራ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያ "ራስን በመከላከል ስም" በሉዓላዊት የተመድ አባል ላይ የምትፈጽመውን ጦርነት ምክንያታዊ ለማድረግ እየሞከረች ነው ስትል ከሰሰች።
በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ መስከረም 30/2019 ዓ. ም. በተጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ የኢትዮጵያ "የማታለል ሙከራ ጭብጥ አልባ እና የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የማገናዘብ አቅም የናቀ ነው" ስትል አሥመራ ወንጅላለች።
ኢትዮጵያ በኤርትራ ወረራ እንደተፈጸመባት እና ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት በመግለጽ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በደብዳቤ ማሳወቋ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በጻፉት ደብዳቤ የኤርትራ ሠራዊት ድንበር አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ደብዳቤውን የጻፈችው በትግራይ ጦርነት ዳግም ከተጀመረ ከሁለት ሳምንት በኋላ ረቡዕ ዕለት መስከረም 27/2019 ዓ. ም. የኤርትራ ወታደሮች በብዛት በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች መታየታቸው በስፋት ከተዘገበ በኋላ ነው።
ኤርትራ በጻፈችው ደብዳቤ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የተላከውን ደብዳቤ ጠቅሳለች።
ኢትዮጵያ በደብዳቤዋ "እርምጃ እየወሰደች" እንደሆነ ማሳወቋን የጠቀሰችው ኤርትራ፣ "ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ጦርነት ማወጇን" አስታውቃለች።
ቢቢሲን ጨምሮ የተለያዩ የዜና ምንጮች የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባታቸውን በተመለከተ ነዋሪዎችን ዋቢ አድርገው ቢዘግቡም፣ ኤርትራ ግን ኢትዮጵያ ልትከፍተው ለምትፈልገው ወረራ "ሰበብ እየፈለገች ነው" በማለት ክሱን ውድቅ አድርጋዋለች።
ቢቢሲ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጭ እንደተረዳው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን በጻፉት ደብዳቤ በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ለፀጥታው ምክር ቤት አባላት በላከችው ደብዳቤ "ኤርትራ በተደጋጋሚ በፈጸመችው ጸብ አጫሪነት እና ድንበር ጥሶ የመግባት እርምጃ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ አደጋ መደቀኑን" በመጥቀስ ትኩረት እንዲሰጠው መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።
"ኤርትራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን በመጣስ ወረራ ፈጽማለች፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የወረራው ሰለባ ናት" በማለትም ከስሰዋል።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ በደብዳቤው በሰጡት ምላሽ፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት "ሉዓላዊ ጥያቄን" በኃይል ለማስፈጸም ኤርትራ ላይ "ጦርነት ማወጇን" በመጥቀስ ይህም "የኤርትራን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጻረር" እንደሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ ማስታወቋን ጠቁማለች።
"የኢትዮጵያ ሕገ ወጥ ዛቻ እና ኤርትራ ላይ ጦርነት የመክፈት ዕቅድ የተመድን መሠረታዊ መርኅ እና ደንብ የሚጥስ፣ የኤርትራን በትግል የተገኘ ነጻነት እና የማይሻር ሉዓላዊነት የሚንድ ነው" ስትልም ወንጅላለች።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግም ከተነሳ በኋላ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን በይፋ አቋርጠዋል። ጦርነቱ ተባብሶ ቀጣናዊ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማትም አስጠንቅቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን በደብዳቤያቸው፣ ኤርትራ የፀብ አጫሪነት ድርጊቷን በአሁኑ ጊዜ ከፍ ወዳለ ደረጃ አሸጋግራ "ሜካናይዝድ ክፍሎችን ጨምሮ ወታደሮቿን በጥልቀት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት አሰማርታለች። ሦስት የትግራይ ዞኖችን በማካተት በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ከ30 አስከ 60 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ርቀት ወደ ውስጥ ገብተዋል" ብለዋል።
ሚኒስትሩ የኤርትራ ድርጊት የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት ውስጥ የሰፈሩትን መሠረታዊ መርሆዎች በግልጽ የሚጥስ ነው በማለት "ይህም ኢትዮጵያ ራሷን የመከላከል ሕጋዊ መብት እንድትጠቀም የሚያስገድድ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።
ኤርትራ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ፣ ምክር ቤቱ ኤርትራ ላይ የተከፈተውን "አሳዛኝ ጦርነት በጽኑ እንዲያወግዝ" ጠይቃለች።
"ጦርነቱ በሁለቱም አገራት ዜጎች ከፍተኛ ቀውስ ያስከትላል፤ መላው ቀጣናውን ያውካል" ያለችው ኤርትራ "በተመድ ቻርተር ምዕራፍ 7 መሠረት እርምጃ እንዲወሰድ" ጠይቃለች።
የኢትዮጵያ "ጸብ አጫሪ የጦርነት ድርጊቶች እና ቀጣናውን ማወክ" ታኅሣሥ ላይ የአልጀርስ ስምምነት 25ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲደረግ የፀጥታዊ ምክር ቤት እና በርካታ የተባበሩት መንግሥታት አባላት የጋራ መግለጫ እንዲያወጡ ያደረገ መሆኑን ኤርትራ ገልጻለች።
ይህም "የኤርትራን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር ያለውን አስፈላጊነት ያሳየ" እንደሆነ ጠቅሳለች።
ደብዳቤው ኢትዮጵያ ይህንን ማስጠንቀቂያ "ለማክበር ካለመቻሏ በተጨማሪ ኤርትራን የመውረር የረዥም ጊዜ ዕቅዷን በሰሜን ኢትዮጵያ የከፈተችው ሰፊ ወረራ አካል አድርጋዋለች" ይላል።
ኤርትራ በደብዳቤዋ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ "ባለፈው ወር መስከረም 27 [እአአ] የጦርነቱ የመጨረሻ ግብ አሰብን መውረር ነው፤ የትግራይ መዲና መቀለ ኤርትራን ለመውረር እንደ መሸጋገገሪያ ናት ብለዋል" ስትልም ከስሳለች።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከ25 ዓመታት በፊት በድንበር ይገባኛል ሰበብ ለሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት ካደረጉ በኋላ ከስምንት ዓመት በፊት ግንኙነታቸው ቢታደስም በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ካበቃ በኋላ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለይ ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ካስታወቀች በኋላ ውዝግቡ የበረታ ሲሆን ወደ ግጭት ይገባሉ ተብሎ ሲነገር ቆይቷል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ከህወሓት ኃይሎች ጋር በአማራ እና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ ስፍራዎች ላይ ወደ ግጭት ከገባ በኋላ የኤርትራ ኃይሎች በግጭቶቹ ተሳታፊ ናቸው የሚል ክስ ቢቀርብም ኤርትራ ስታስተባብል ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ለፀጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ተፈጸመ ያለችውን ወረራ ከማሳወቅ ባለፈ አገሪቱ ለምትወስደው የመከላከል እርምጃ ድጋፍ ጠይቃለች።
"በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ኢትዮጵያ ራሷን ከመከላከል በቀር ሌላ አማራጭ የላትም" በማለት ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ የገጠማትን ሁኔታ በመረዳት ድጋፍ እንዲደያርግላት እና ከጎኗ እንዲቆም አሳስባለች።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ በኩል ለረዥም ጊዜ ሲፈጸሙ ለነበሩ ትንኮሳዎች በትዕግሥት እና ራስን በመቆጠብ መቆየቷንም ደብዳቤው ያትታል።




































