ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"በልጄ ላይ የደረሰ ነገር ዛሬ እኔ ላይ ተፈጽሟል" - ባሌ ውስጥ ድብደባ የደረሰባቸው የጤና ባለሙያ
ለ40 ዓመታት የጤና ባለሙያ ሆነው ያገለገሉት ዋቆ ከድር አርብ ሚያዝያ 2/2018 ዓ.ም. በንጋት የተነሱት ከኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ዋና ከተማ ባሌ ሮቤ ተነስተው ወደ ትውልደ አካባቢያቸው አጋርፋ ከተማ ለመጓዝ ነበር።
ከ1978 ዓ.ም. ጀምሮ ከጤና ረዳትነት እስከ ነርስነት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሠሩት የጤና ባለሙያው ጡረታቸውን ለማስከበር ወዲህ ወዲያ እያሉ ነበር። ቦርሳቸው ውስጥም ሰነዶቻቸውን ይዘዋል።
የአጭር ርቀት የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ወደሚገኙበት አሮጌው መናኽሪያ እየተቃረቡ ሲመጡ አንድ ወጣት ይጠራቸው እንደጀመረ ይናገራሉ።
"ወጣት ነው፤ በሩቁ ቁም አለኝ። ዞር ብዬ ሳየው የማላውቀው ሰው ነው" ይላሉ ዋቆ ዕለቱን ሲያስታውሱ። "ይሄ ሰውዬ በበጎ እንደማይፈልገኝ ወዲያውኑ አካሄዱን ተረዳሁ" የሚሉት ጤና ባለሙያው "ፈጠን እያሉ" ወደ መናኽሪያው መግባታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሃሳባቸው፤ መናኽሪያ ውስጥ ከገቡ "የጸጥታ አስከባሪዎች ይኖራሉ" የሚል ነበር። እንዳሰቡት ግን ከለላ አልያም የሚያስጥል አላገኙም።
"ወደ መናኽሪያው ገብቼ ወደ 50 ሜትር እንደደረስኩ ደረሰብኝ። 'ሞባይሌን አምጣ' አለኝ። 'የትኛውን ሞባይል' ስል፤ 'የወሰድክብኝን ሞባይል አምጣ' አለኝ" ሲሉ በሌብነት መወንጀላቸውን ይገልጻሉ። የግለሰቡን ሞባይል አለመውሰዳቸውን ቢናገሩም አልታመኑም።
ግለሰቡ "ሊያምናቸው እና ሊያዳምጣቸው እንዳልቻለ" የሚያስረዱት ዋቆ፤ "ቦክስ ነው የጀመረው" ይላሉ።
"ደጋግሞ መታኝ። የነበሩ [የተሽከርካሪ ረዳቶች]፣ መናኽሪያ ውስጥም የነበሩ ሰዎች በቃ ግር ብለው መጡ። እነሱም 'ሌባ፣ ሌባ' ብለው መቱኝ። በኃይል ነው የመቱኝ" ሲሉ የደረሰባቸውን ያስታውሳሉ።
ይህ ድርጊት በጤና ባለሙያው ዋቆ ላይ የደረሰውን ድብደባ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተለቅቀዋል።
በአንዱ ቪዲዮ ላይ በእጃቸው ቦርሳ የያዙት ዋቆ በርካታ ሰዎች እየተከተሏቸው ለመሸሽ ሲሞክሩ ይታያል። አንድ ሰው ዘልሎ ማጅራታቸው ላይ በኃይል እጁን ጭንቅላታቸው ላይ ሲያሳርፍ ተቀርጿል። እየጮኹ ለመሸሽ በሚሞክሩት ዋቆ በግራ በኩል ያለው ግንባራቸው ላይ እብጠት ይታያል።
ሌላ ቪዲዮ የሚያሳየው ደግሞ በበርካታ ሰዎች ተከብበው እየጮኹ ነው። "ሌባ"፣ "ሌላም አውጣ"፣ "አውጣ" የሚሉ ሰዎች ድምጽ ይሰማል። ብዙ ሰዎች ከፊትም ከኋላም ያሉ ኪሶቻቸው ሲፈትሹ ይታያል። የደረት ኪሳቸውን የሚፈትሽ አንድ ሰው አንዳች ነገር ሲያወጣ ተቀርጿል።
ዋቆ ለቢቢሲ ሲናገሩ "ቦርሳዬን ፈተሹ፣ ኪሴን ፈተሹ፣ አንዱ ይደበድበኛል፣ ሌላው ይረግጠኛል" ብለዋል። "ለትራንስፖርት" ብለው "በተለያዩ ኪሶቻቸው" ይዘውት የነበረ "አራት ሺህ ብር" ገደማ መወሰዱንም ገልጸዋል።
ከብዙ ድብደባ በኋላ በመጨረሻ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን ያስታውሳሉ። ፖሊሶች "እርሱንም እኔንም ጠየቁ። በጣም ስለመታኝ፣ ፌቴ ሁሉ ስላበጠ እርሱን አስገብተው፣ ጣብያ ታስሮ፤ እኔን ደግሞ 'ሂድ እና ታከም' ነው ያሉኝ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያው ላይ የደረሰውን ድብደባ የሚያሳዩ ቪዲዮች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት መሰራጨታቸውን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ቁጣቸውን ገልጸዋል።
የባሌ ሮቤ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መመሪያ ባወጣው መግለጫ አቶ ዋቆን በመደብደብ የተጠረጠሩ ሰባት ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። በተጠርጣሪዎቹ ላይ "ሕጋዊ እርምጃ" ለመውሰድ "ጉዳዩን እያጣራ" መሆኑንም ገልጿል።
የጤና ባለሙያው ዋቆ በተፈጸመባቸው ድብደባ "ከፍተኛ ቁስለት" ደርሶባቸዋል። የግራ እጃቸው ትንሿ ጣት ላይ "ስብራት ነገር" እንደደረሰባቸውም ይናገራሉ።
"ቁስል ሊድን ይችላል፤ ስጋዬን ነው የመቱኝ፤ ምንም ችግር አይደለም" የሚሉት ዋቆ፤ ከአዕምሯቸው የማይጠፋው ግን በልጃቸው ላይ የተፈጸመ ተግባር እርሳቸውም ላይ መድረሱ እንደሆነ ያስረዳሉ።
የ25 ዓመቱ ልጃቸው ረመዳንን ያጡት በሐምሌ 2010 ዓ.ም. ነበር።
ወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከተሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች የበረከቱበት ነበር። በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎችም ግጭት ተነስቶ ነዋሪዎች መገደላቸው ይታወሳል።
የጤና ባለሙያው ዋቆ እንደሚናገሩት ልጃቸው ረመዳን የመኪና ረዳት ነበር። "የመኪና ረዳት ስለነበረ ከሮቤ ወደ ሶማሌ ክልል ሄደ። እዛ ደርሶ በሶማሌ ልዩ ኃይል በዱላ፣ በአሰቃቂ [ሁኔታ] ተገድሏል" ይላሉ።
የልጃቸው ሞት ሐዘን ውስጥ ከትቷቸው እንደነበር የሚናገሩት ዋቆ፤ ከቢቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ በሚያደርጉበት ወቅት መናገር ከብዷቸው ለሴኮንዶች ዝም ይሉ ነበር።
ሐዘን በተጫነው ድምጽ "በልጄ ላይ ደረሰ ነገር ዛሬም በእኔ ላይ ተፈጽሟል" ብለዋል።
"ከአዕምሮዬ የማይጠፋው ሁለት ነገር ነው። አንደኛ በልጄ ላይ የደረሰው ነገር የአዕምሮ ቁስለት ሆኖብኛል። ደግሞ እንዲዚህ ዓይነት ነገር በእኔ ላይ ሲደርስ ተጨማሪ ቁስለት ነው" ሲሉ ተናገረዋል።
"ስልክ ሰርቆኛል" በሚል የወነጀላቸው ወጣት "እኔን ሳይረዳ፣ ነገሩን ሳይረዳ ለቦክስ መሮጡ ጥሩ አይደለም። መታኝ፣ ጎዳኝ። ለሌሎችም ደግሞ አጋልጦኛል" ሲሉ በደቦ የደረሰባቸውን ድርጊት እንዳሳዘናቸው አንስተዋል።
ግለሰቡ ቦርሳቸው ውስጥ ያሉትን ሰነዶች ከተመለከተ በኋላ "እንደተደናገጠ"፣ "መሳሳቱ እንደገባው" እና "እንደተጸጸተ" ገልጸዋል። "በተለይ ወጣቶች ነገሩን ሳያጣሩ" ለድብደባ መጣደፋቸውን አንስተው ወቅሰዋል።
ዋቆ በባሌ ሮቤ ከተማ መናኽሪያ ውስጥ የደረሰባቸው ድብደባ ተቀርጾ በማኅበራዊ ሚዲያ መሠራጨቱም ስጋት ላይ ጥሏቸዋል። "እያንዳንዱ ሰው ጋር ሲደርስ፣ ብዙ ሰው ነው የሚያየው። ለእኔ ጥሩ እንዳልሆነ አውቃለሁ" ብለዋል።
ዋቆ ላይ የተፈጸመውን ድብደባ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ከተለቀቁ በኋላ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እርዳታ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
ቅዳሜ ዕለት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሽልማት እና የምስጋና ስነ-ስርዓት ሲያካሂድ የነበረው አዋሽ ባንክ፤ ለአቶ ዋቆ "የ500 ሺህ ብር የክብር ሽልማት" ማበርከቱን አስታውቋል። የባሌ ሮቤ ከተማ አስተዳደርም ለጤና ባለሙያው ቤት መስሪያ መሬት እንዳበረከተላቸው የሚገልጹ መረጃዎች በስፋት ተሰራጭተዋል።
ስለ እነዚህ ስጦታዎች ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው ዋቆ የተለያዩ ሰዎች ወደ ባንክ አካውንታቸው ካስገቡት "የተወሰነ ገንዘብ ውጪ እጃቸው ላይ የገባ ነገር እንደሌለ" ተናግረዋል።