ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ከሌላው የዓለም ክፍል በተለየ እንዴት የከፍተኛ ነዳጅ እና ጋዝ ሀብት ባለፀጋ ሆነ?
የፋርስ ባሕረ ሰላጤ አገራት ከሰፊው የነዳጅ እና የጋዝ ክምችታቸው ጋር በተያያዘ ፀጋ እና መጥፎ ነገር እየገጠማቸው እኩል እንደሆነ ተደጋግሞ ይነገራል።
በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲካሄድ በቆየ ተፈጥሯዊ ክስተት የተነሳ ቀጣናው ዓለም አቀፍ የነዳጅ እና የጋዝ ማዕከል ሆኗል፣። ለዚህም ነው አሁን ያጋጠመው ዓይነት ጦርነት እና ቀውስ በመካከኛው ምሥራቅ ሲከሰት በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ችግር የኃይል ቀውስ የሚፈጥሩት።
የአካባቢው ለነዳጅ ምርት አስፈላጊ የሆነው የሃይድሮካርቦን ክምችቶች መጠን አስገራሚ መሆኑ ይነገራል። ለምሳሌ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ዙሪያ ከ30 በላይ በጣም ግዙፍ የነዳጅ ክምችቶች ያሉ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 5 ቢሊዮን በርሜል ወይም ከዚያ በላይ ድፍድፍ ነዳጅ ይይዛሉ።
በአካባቢው ያሉት ጉድጓዶች በሰሜን ባሕር እና በሩሲያ ውስጥ ካሉት ምርጥ ጉድጓዶች አንጻር ሲታዩ በቀን ከሁለት እስከ አምስት እጥፍ የሚበልጥ ነዳጅ ዘይት ያመርታሉ።
ዘመናዊው የጂኦሳይንስ ጥናት አንድን ክልል በነዳጅ የበለፀገ እንዲሆን የሚያደርጉ በርካታ ቁልፍ ነገሮችን ለይቶ ያሳውቃል። ከእነዚህም መካከል ሃይድሮካርቦኖችን ማመንጨት እና የማቆየት ችሎታን ያካትታል።
በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ክልል ውስጥ እነዚህ ቁልፍ ምክንያቶች በጣም ጥሩ ወይም በከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በከፍተኛ ክምችት እና ለማምረት ቀላል በመሆኑ ምክንያት የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ክልል ቀዳሚው ሆኗል።
አጭር ታሪክ
ሰዎች በአካባቢው የሃይድሮካርቦን መኖሩን ያውቁ የነበረው ከ14 ሺህ እስከ 6 ሺህ ዓመታት በፊት ነበር።
በብዙ አካባቢዎች በወንዞች እና በሸለቆዎች ላይ የተፈጥሮ ዘይት እና ጋዝ መፍሰሱ የተለመደ ነው።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ሰዎች ለመርከቦች የውሃ መከላከያ እና ሌሎችንም ነገሮች ለመሥራት የከባድ ነዳጅ ዓይነት የሆነውን ሬንጅን ይጠቀሙ ነበር።
የመጀመሪያው ዘመናዊ ነዳጅ የተገኘው በ1908 በምዕራብ ኢራን በሚገኝ ታዋቂ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦታ ላይ ነው።
የነዳጅ እና የጋዝ ፍለጋ ፈጣን በሆነ ሁኔታ በተስፋፋበት በ1950ዎቹ እና 1960ዎቹ በዓለም ላይ ከፍተኛው ነዳጅ እና ጋዝ በአካባቢው እንደሚኖር ግልጽ መሆን ጀመረ።
እንደ ሩሲያዋ ምዕራባዊ ሳይቤሪያ እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንደሚገኘው የፐርሚያን ተፋሰስ ባሉ አካባቢዎችም ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እና ጋዝ ቢገኝም ግን በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ ካለው የክምችት መጠን ጋር አይወዳደርም። በምርት ደረጃም የሚወዳደር አይደለም።
ሥነ ምድራዊ አቀማመጥ
የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ክልል ሁለት የቴክቶኒክ አለቶች የሚገናኙበት ቦታ ነው። እነዚህም በደቡብ ምሥራቅ ያለው የአረብ አለት እና በምሥራቅ እና በሰሜን ያለው የዩሪኤሺያ አለት ናቸው።
ይህ ግጭት ለ35 ሚሊዮን ዓመታት ያህል ሲከሰት የቆየ ሲሆን የድንጋይ ንብርብሮቹ ታጥፈው በመሰባበር እና በጥልቀት በሚከሰቱ የሙቀት እና ግፊት የሚለዋወጡበት ሁኔታ ተከስቷል።
የጂኦሎጂካል (ሥነ ምድራዊ) ባህሪያቱ በባሕረ ሰላጤው ሁለት ጎኖች መካከል በእጅጉ ይለያያሉ። በኢራን በኩል የዛግሮስ የተራራ ክልል ከኦማን ባሕረ ሰላጤ እስከ ቱርክ ድንበር ድረስ አንድ ሺህ 800 ኪሎ ሜትር ይረዝማል።
በባሕረ ሰላጤው የአረቢያ የባሕር ዳርቻ ላይ ተመሳሳይ ዓይነት መተጣጠፍ እና መሰባበር አልተከሰተም።
በአንጻሩ የግጭቱ ኃይል "ቤዝመንት ሮክ" በመባል የሚታወቀውን ጠንካራ እና ጥልቅ ድንጋይ ፈጠሯል። ይህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ካሬ ኪሎ ሜትሮች የሚዘልቁ ግዙፍ የአለት መዋቅሮችን ፈጥሯል።
ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ በታች ከዛግሮስ ተራሮች በተሸረሸረ ደለል የተሞላ ነው። በጥልቀትም ለነዳጅ እና ጋዝ መፈጠር አስፈላጊ ለሆኑ ከፍተኛ ሙቀት እና ጫና አለ።
በአጭሩ የሃይድሮካርቦኖችን በሰፊው ለማምረት እና ለማከማቸት በጣም ጥሩ አካባቢ ነው።
ድፍድፍ ነዳጅ የሚያመርቱት አለቶች
ድፍድፍ ነዳጅ እና ጋዝ የሚሠሩት የባሕር ዞፕላንክተን እና ፊቶፕላንክተን ካሉ ተፈጥሯዊ ቁሶች ነው።
መጀመሪያ ላይ የሚገኙት በሼል፣ በጭቃ ውስጥ ባለው የኖራ ድንጋይ እና ለከፍተኛ ሙቀት እና ግፊት በተጋለጡ ሌሎች አለቶች ላይ ነው።
አለቶቹ ቢያንስ ሁለት በመቶ ተፈጥሯዊ ቁሶችን ሲይዙ ለነዳጅ እና ለጋዝ ምርት ከፍተኛ ጥራት እንዳላቸው ይገመታል።
የባሕር ሰላጤው ክልል ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው በእነዚህ የአለት ንብርብሮች የታደለ ነው። አንዳንዶቹ ወፍራም እና በተፈጥሯዊ የበለፀጉ ናቸው።
ከ200 እስከ 145 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በጁራሲክ ዘመን የተፈጠሩት በአረቢያ ባሕረ ሰላጤ ዳርቻ ላይ የሚገኙት የሃኒፋ እና የቱዋይቅ ተራራ መሠረቶች እና ከ145 እስከ 66 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በክሪታሲየስ ዘመን የተፈጠረው በኢራን የሚገኘው የካዝዱሚ መሠረት ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።
እነዚህ አለቶች ከአንድ በመቶ እስከ 13 በመቶ ተፈጥሯዊ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ቁጥሩ ከፍ ይላል።
የነዳጅ እና የጋዝ መዋቅሮች
የክልሉ የታጠፉ እና የተሰበሩ የአለት ንብርብሮች ሃይድሮካርቦኖችን ለመያዝ ተመቹ ናቸው።
በጂኦሎጂስቶች ዘንድ ታዋቂ ከሆኑት ተራሮች አንዱ በሆነው በዛግሮስ በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር በርሜል ነዳጅ እና ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ ይዟል።
የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ክልል የነዳጅ እና የጋዝ ካርታን ብንመለከት ከሰሜን ምዕራብ እስከ ደቡብ ምሥራቅ የሚሄዱ እና ዋና ዋና መዋቅሮችን የሚያንፀባርቁ የቱቦ ቅርጽ ያላቸው መስኮችን ያሳያሉ።
እነዚህ ደግሞ ከደቡብ ኢራን እስከ ሰሜን ምሥራቅ ኢራቅ የሚዘልቁ የተለያዩ መጠኖች ያላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ክምችቶችን ያካትታሉ።
በአረቢያ አለት ላይ ትላልቅ ጉልላት መሰል መዋቅሮች መፈጠሩ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ እና የጋዝ ክምችትን ፈጥሯል።
ከእነዚህ አንዱ በዓለም ላይ ትልቁ የሆነውን የነዳጅ ክምችት የያዘውን እና ከ70 ቢሊዮን በርሜል በላይ ድፍድፍ ነዳጅ የሚያመርተውን ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ያለውን የጋዋር የነዳጅ መስክ ያካትታል።
የደቡብ ፓርስ-ሰሜን ዶም የተፈጥሮ ጋዝ መስክ በበኩሉ በኢራን እና በኳታር መካከል የሚገኝ ሲሆን፣ በትንሹ 46 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ ሊያመነጭ ይችላል። ይህም ከ200 ቢሊዮን በርሜል በላይ ነዳጅ ጋር እኩል ነው።
በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ድንጋዮች መካከል የኖራ ድንጋይ ተጠቃሽ ነው። አንዳንድ ክፍሎቹ በከፊል በመሟሟት የነዳጅ እና የጋዝ ፍሰትን ያመቻቻል።
በዛግሮስ በፈሳሽ አለት ግጭት ምክንያት በሚከሰቱ እጥፋቶች እና ክፍተቶች ምክንያት በሚፈጠሩ ቀዳዳዎች ውስጥ ይፈሳል።
በሳዑዲ አረቢያ በጋዋር መስክ ውስጥ ባለው የአረብ-ዲ ማጠራቀሚያ እና በበርካታ የዛግሮስ አካባቢዎች የአስማሪ የኖራ ድንጋይ ባሉ ቦታዎች፣ እነዚህ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የነዳጅ ማከማቻ ድንጋዮች በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ካሬ ኪሎ ሜትሮች ሰፊ ቦታዎችን ይሸፍናሉ።
በዓለም ላይ እንደዚህ ያለ መጠን ያለው ቦታ የለም። ይህም የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ያለውን ልዩ የፔትሮሊየም ጂኦሎጂ ያሳያል።
መጻኢ ዕድሎች
በእነዚህ ምክንያቶች ግማሽ ያህሉ የዓለም የነዳጅ ክምችት እና 40 በመቶው የሚሆነው ጋዝ 3 በመቶ በሚሆነው በዚህ የምድራችን ክፍል ውስጥ እንዲገኝ አድርጎታል።
የዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ግምገማዎች እንደሚያሳዩት፤ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ከዘለቀው የቁፋሮ እና የምርት ሂደት በኋላም በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ክልል ውስጥ አሁንም ትላልቅ የነዳጅ እና የጋዝ ክምችቶች አሉ።
ኤጀንሲው ቀደም ሲል በአውሮፓውያኑ 2012 የአረቢያ ባሕረ ገብ መሬት እና የዛግሮስ ተራሮችን ባጠናበት ሪፖርቱ፤ አሁን ከተገኙት በተጨማሪ እስከ 86 ቢሊዮን በርሜል ዘይት እና 9.5 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ በድንጋዮቹ ውስጥ ሊኖር እንደሚችል ገምቷል።
በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ እና 2010ዎቹ በአሜሪካ በተዋወቁት አዳዲስ ነዳጅ የማውጫ ቴክኒኮች (የአግድም ቁፋሮ እና የፍራኪንግ/ሃይድሮሊክ ፍራክቸር) ተጨማሪ ድፍድፍ ዘይት እና ጋዝ ማምረት ይቻላል።
ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (ዩኤኢ) እነዚህን ቴክኒኮች እየሞከሩ ነው። ምን ያህል ስኬታማ እንደሚሆኑ ለማወቅ ጊዜው ገና ቢሆንም ግን ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ቴክኒኩ የበለጠ ምርት ማመንጨት ያስችላል።